ኤሎን መስክ ለአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ባወጣው ከፍተኛ ገንዘብ መቆጨቱን ተናገረ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኤሎን መስክ የሪፐብሊካን ፓርቲ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ከፍተኛ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ፣ ለምርጫው ባወጣው ከፍተኛ ገንዘብ መቆጨቱን እና "እጅግ ሞኝነት" እንደነበር ተናገረ።

የቴስላ እና የስፔስኤክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው መስክ፣ በተለይም አብዛኞቹ ኩባንያዎቹ በሚገኙበት ቴክሳስ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ፓርቲ ለመደገፍ 446 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ በምርጫው ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣ ለጋሽ ነበር።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የዋይት ሐውስ ሹመትን ለማግኘት ላደረጉት ጥረት ድጋፉን የሰጠው መስክ፣ ማጋ በመባል የሚታወቀው የፕሬዝዳንቱ "አሜሪካን እንደገና ታላቅ እናድርጋት" የሚለው እንቅስቃሴ አካል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ዴሞክራቶች በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ሁለቱንም ምክር ቤቶች ተቆጣጥረው በመያዝ ለብዙ አስርት ዓመታት በሪፐብሊካኖች ቁጥጥር ስር በነበሩ ቦታዎች ታሪካዊ ለውጥ አስመዝግበዋል።

ምርጫው፣ ፖሊሲዎቻቸው በአሜሪካ የኑሮ ውድነት ላይ ባሳደሩት ተጽዕኖ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ለገጠማቸው ትራምፕ እንደ ከባድ ሽንፈት ተቆጥሯል።

መስክ ባወጣው ከፍተኛ ገንዘብ መቆጨቱን የተናገረው ታዋቂ የንግድ እና የፖለቲካ መሪዎች በሚሳተፉበት እና በኒው ዮርክ በሚዘጋጀው ዓመታዊው የኒውዮርክ ታይምስ "ዲልቡክ ሰሚት" ሁባኤ ላይ ባደረገው ንግግር ነው።

መስክ የቀኝ ዘመም የፖለቲካ እንቅስቃሴውን በመጥቀስ "እኔ የማጋ አባል አይደለሁም"ብሏል።

"ማጋ ምን ማለት እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም... ትርጉሙ የሪፐብሊካን ፓርቲን ፖሊሲዎች በጭፍን መከተል ከሆነ፣ እኔ በእርግጠኝነት የለሁበትም" ሲል ተናግሯል።

መስክ በትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይ ለበርካታ ወራት ያለክፍያ የሚያገለግል "ልዩ የመንግሥት ሠራተኛ" እና የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ በመሆን፣ የመንግሥት ወጪን ለመቀነስ የተቋቋመውን ተቋም መርቷል።

ባለፈው ጥቅምት ፔንታጎን መስክን "ፕሮጀክት ሜሪዲያን" የተሰኘ የወደፊት የጦርነት ጥናት ተባባሪ መሪ አድርጎ የሾመው ሲሆን፣ እሱም ከትራምፕ ጋር መጓዙን እና እሳቸውን ማማከሩን ቀጥሎ ነበር።

መስክ በንግግሩ ለሪፐብሊካኖች የምርጫ ዘመቻ ላወጣው ገንዘብ ብዙም ውጤት እንዳላየ ቢናገርም፣ ያ ወጪ ባይኖር ኖሮ ዕጩዎቹ የባሰ ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችሉ እንደነበር አክሎ ገልጿል።

ትራምፕ ዳግም ከተመረጡ ወዲህ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አዲስ የመንግሥት ኮንትራት ያገኘው ስፔስኤክስ ምርመራ ሊደረግበት እንደሚገባ ዴሞክራት የሕግ አውጪዎች ሐሳብ አቅርበዋል።

በአጋማሽ ዘመን ምርጫው ከተመዘገቡት አስገራሚ ድሎች አንዱ፣ በቴክሳስ የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት መቀመጫ ሪፐብሊካኑን ኬን ፓክስተንን ያሸነፈው ዴሞክራቱ ጄምስ ታላሪኮ ነው።

እንደ ቢቢሲ ትንታኔ ከሆነ፣ መስክ ፓክስተንን ለመደገፍ ቢያንስ 45 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል።