በአውሮፓ የቦምብ ጥቃት በመሰንዘሩ ሰባት አውሮፕላኖች ላይ ምርመራ ተደረገ

የራየንኤር አውሮፕላን ላይ ፍተሻ ሲካሄድ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአውሮፓ በበርካታ አውሮፕላኖች ላይ የቦምብ ጥቃት ይፈጸማል የሚሉ ዛቻዎችን መሰንዘራቸውን ተከትሎ በተፈጠሩ ጥርጣሬዎች ሰባት የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላኖች ላይ ምርመራ ተካሄደ።

ምርመራ ከተደረገላቸው አውሮፕላኖች መካከል ሁለቱ ከዩናይትድ ኪንግደም የተነሱ መሆናቸው ታውቋል።

አንዱ ከደብሊን ሌላው ደግሞ ከሊዝበን የተነሳ የራየንኤር አውሮፕላኖች፣ ሮም ላይ ካረፉ በኋላ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተሰጡ ጥቆማዎች መሠረት ፍተሻ ተደርጎላቸዋል። ሆኖም በአውሮፕላኖቹ ውስጥ የፈንጂ ቁሳቁስ አልተገኘም ሲሉ በሮም ፊዩሚቺኖ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከደብሊን የተነሳው አውሮፕላን እስከ ማረፊያው ድረስ በጣሊያን አየር ኃይል ታጅቦ መጓዙ ተገልጿል። በተጨማሪም በፖላንድ፣ በስፔን እና በቡልጋሪያ ያሉ አውሮፕላኖችም ፍተሻ ተደርጎባቸዋል።

ምንም እንኳን ባለሥልጣናት እስካሁን እነዚህን ክስተቶች በይፋ ትስስር እንዳላቸው ባይገልጹም፣ ከበርካታ አገራት የተውጣጡ ኃላፊዎች እነዚህ ድርጊቶች የአየር ክልል እና የአየር ትራፊክ ሥርዓትን ለማወክ ታስቦ በተቀናጀ መልኩ የተፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ለማጣራት በጋራ እንደሚሰሩ ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እነዚህን ክስተቶች "በተንኮል የተፈጸሙ የሐሰት የቦምብ ማስፈራሪያዎች" ሲል ገልጿቸዋል።

መንግሥት ባወጣው መግለጫ "ብሪታኒያ በዓለም ካሉት ሁሉ በጣም ጠንካራ የአቪዬሽን ደኅንነት ሥርዓቶች አንዱ አላት። ማንኛውንም ሊኖር የሚችል አደጋ እና እንደ ዛሬው ያሉ በተንኮል የተፈጸሙ የሐሰት ማስፈራሪያዎችን ለመቋቋም በደንብ የተፈተኑ ሂደቶች አሉን" ብሏል።

የአቪዬሽን ደኅንነት ባለሙያው ፖል ሜሰን በበኩላቸው፣ በመንገደኞች አውሮፕላኖች ላይ የቦምብ ማስፈራሪያዎች "በተደጋጋሚ የሚከሰቱ አይደሉም" በማለት፣ የቅርብ ጊዜዎቹ ክስተቶች "ያልተለመዱ" መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሜሰን ለቢቢሲ ሬዲዮ 5 ላይቭ "ይህ ማስፈራሪያ ለብዙ የአየር መንገድ ኩባንያዎች በአሳማኝ መልኩ የተሰጠ ጥቆማ ይመስላል። ይህም በእኔ እይታ በአጋጣሚ የተፈጸሙ ተንኮለኛ ጥቆማዎች ሳይሆኑ፣ ሆን ተብሎ በአንድ አካል የተቀናጀ ድርጊት መሆኑን ያመለክታል።"

በተጨማሪም በአውሮፕላኑ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችና በመሬት ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች የማስፈራሪያውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ "በርካታ ሂደቶችን" ማለፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

"ማስፈራሪያው የተወሰነ ተዓማኒነት ካለው፣ አውሮፕላኑ አቅጣጫውን ቀይሮ በሌላ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፍ ሊጠየቅ ይችላል" ሲሉ አክለዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለው ሠራተኞች በመሬት ላይ ያሉ ባለሥልጣናት እየተከታተሉት ስላለው ጉዳይ ሙሉ መረጃ ላይደርሳቸው እንደሚችልም ገልጸዋል።

በፖላንድ ዋርሶው ቾፒን አውሮእፐላን ማረፊያ የቆመ አውሮፕላን
የምስሉ መግለጫ, በፖላንድ ዋርሶው ቾፒን አውሮእፐላን ማረፊያ የቆመ አውሮፕላን
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሮም የሚገኘው ፊዩሚቺኖ አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎች የተሳፋሪዎችንና የአውሮፕላን ሠራተኞችን ደኅንነት ለማረጋገጥ መደበኛ የደኅንነት ሂደቶችን ተግባራዊ አድርገዋል።

ተሳፋሪዎች፣ ሻንጣዎች እና አውሮፕላኑ ላይ የተደረገው ፍተሻ ምንም የፈንጂ አሻራ አለመኖሩን ያረጋገጠ ሲሆን፣ የደህንነት ማስጠንቀቂያውም ከዚያ በኋላ ተነስቷል።

በደቡባዊ ስፔን ሙርሺያ ያረፈ ከማንቸስተር የመጣ የራየንኤር አውሮፕላንም ተፈትሾ፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ ምንም የፈንጂ ቁሳቁስ አለመገኘቱን የስፔን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከተሳፋሪዎቹ አንዷ የሆነችው ሳራ፣ አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ብቻ የቦምብ ማስፈራሪያውን እንዳወቀች ተናግራለች።

"በበረራው ወቅት ምንም አልተነገረንም። አውሮፕላኑ በድንገት አረፈ። ከዚያም ለ30 ደቂቃ ያህል በመንደርደሪያው ላይ ቆይተናል" ስትል ለቢቢሲ ሬዲዮ 5 ላይቭ ተናግራለች።

"ከዚያ በኋላ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች፣ የፈንጂ አምካኝ ቡድኖች መጡ፤ ከአውሮፕላኑም እንድንወርድ ተጠየቅን" ብላለች።

ሳራ አውሮፕላኑ እንዳረፈ "በእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች፣ በፖሊስ እና በፈንጂ አምካኝ ቡድኖች" ተከቦ ነበር። ከዚያም ሁሉም ተሳፋሪዎች የግል ንብረቶቻቸውን በአውሮፕላኑ ውስጥ ትተው በፖሊስ ታጅበው ወጥተዋል።

"ከጊዜ በኋላ ብቻ ይህ ማስፈራሪያ እንደነበር፣ በአውሮፕላኑ ላይ የተነጣጠረ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ እንደነበር ተነገረን" ብላለች።

ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ ያቀኑ ሁለት በረራዎችም ተመሳሳይ የጥቃት ዛቻ ደርሶባቸዋል፤ ከእነዚህም አንዱ ከለንደን ሂትሮው አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳ ነበር።

ይህ በረራ በመጀመሪያ ወደ ዋርሶ ቾፒን ዋና አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፍ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ወደ ትንሹ ሞድሊን አውሮፕላን ማረፊያ አምርቷል። በዚህም የተነሳ አውሮፕላን ማረፊያው ለአጭር ጊዜ ተዘግቷል።

ከኮፐንሃገን ወደ ዋርሶ-ቾፒን የተጓዘው የስካንዴኒቪያን አየር መንገድ አውሮፕላን ን በታቀደለት ሰዓት በመደበኛው ሁኔታ ማረፉ ተገልጿል።