በስፔን ከቀናት በፊት የደረሰውን የባቡር አደጋ ተከትሎ የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ከሥልጣናቸው ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የስፔን የትራንስፖርት ሚኒስትር ኦስካር ፑንቴ 69 ሰዎች የሞቱበትና በርካታ ሰዎች የቆሰሉበት የባቡር አደጋ ከተከሰተ ከስድስት ቀናት በኋላ ከሥልጣናቸው ለቀቁ።
ፑንቴ ከሥልጣን እንደሚለቅቁ ያሳወቁት ለአገሪቱ ፓርላማ ስለ ባቡር አደጋው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በፍጥነት እየተጓዘ የነበረ ባቡር ቆሞ ከነበረ ሌላ ባቡር ጋር በመጋጨቱ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
"እንደ ስፔን ባለች አገር፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ከባድ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ የትራንስፖርት ሚኒስትር በሥልጣኑ መቀጠል አይችልም" ብለዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው የጠቀሱት ባለፈው ዓመት በጥር ወር በዚሁ የባቡር መስመር ላይ በተከሰተው እና 46 ሰዎች የሞቱበትን አደጋ ነው።
ባለፈው ሳምንት የተከሰተው የባቡር አደጋ በዘመናዊ የአውሮፓ ታሪክ የደረሰ አስከፊ አደጋ የተባለ ሲሆን፣ ስፔን ደግሞ እአአ በ2013 ካጋጠማት አደጋ ወዲህ እጅግ ከባዱ መሆኑ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የስፔን የትራንስፖርት ሚኒስትር ኦስካር ፑንቴ ማክሰኞ ምሽት ከተካሄደው ረዥም የፓርላማ ውይይት ማብቂያ ላይ ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። በስብሰባው ወቅት አዳዲስ የባቡር ደኅንነት እርምጃዎችን ለመውሰድ ምክረ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከተቃዋሚዎችም ከባድ ጥያቄዎች ተቀብለዋል።
ፑንቴ በመግለጫቸው "ከትራንስፖርት ሚኒስትርነት ቦታዬ ብቻ ሳይሆን የምለቅቀው በተጨማሪም ለሕግ አውጪዎች ምርጫ ከቀረቡት የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ስሜንም እሰርዛለሁ" ብለዋል።
እአአ ጥቅምት 28 ከተከሰተው የባቡር አደጋ በኋላ፣ የፑንቴ ኃላፊነትና በሥልጣን የመቀጠላቸው ጉዳይ የሕዝብና የፖለቲከኞች የትኩረት ማዕከል ሆኖ ነበር።
የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፑንቴ ከሥልጣናቸው እንዲለቅቁ ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል።
ፓርቲዎቹ ስፔናውያን ደህንነቱ አጠራጣሪ ነው ብለው በሚያምኑት የፍጥነት ባቡር መስመር ላይ ስለደረሰው አደጋ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።
ተቃዋሚዎች በተጨማሪም ፑንቴ ለአደጋው የሰው ስህተት መንስኤ መሆኑን በመጠቆም ተጠያቂነቱን ከራሳቸው ለማራቅ እየሞከሩ ነው ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
ሆኖም፣ ከጥቂት ቀናት በፊት በሥልጣናቸው እንደሚቀጥሉ ከተናገሩ በኋላ የመልቀቂያ ውሳኔያቸውን ማስታወቃቸው ብዙ ሰዎችን አስገርሟል።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የተከሰተው አደጋ 397 ተሳፋሪዎችን አሳፍሮ እየተጓዘ የነበረው እና በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ባቡር 147 ተሳፋሪዎችን አሳፍሮ ቆሞ ከነበረ በግል ኩባንያ ከሚተዳደር ባቡር ጋር ተጋጭቷል።
አደጋው ከሰው ስህተት እና ከኮምፒውተር ደህንነት ሥርዓት ጋር የተያያዘ የደረሰ መሆኑ ተገልጿል።
አደጋው ከተከሰተ በኋላ በስፔን ሚዲያዎች የተለቀቁ የድምጽ ቅጂዎች፣ ከአደጋው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት በማድሪድ የቁጥጥር ማዕከል እና በሁለት የባቡር ሾፌሮች መካከል የተደረጉ ውይይቶችን አጋርተዋል።
በማድሪድ የቁጥጥር ማዕከል እና በሁለቱ የባቡር አሽከርካሪዎች መካከል የተደረጉት ሦስቱ የድምጽ ቅጂዎች፣ ከነሱ 25 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በባቡር መስመሩ ላይ ሌላ ባቡር የቆመ ቢሆንም ባቡሩ ግን እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ እንደተሰጠው የሚያሳዩ ናቸው
































