እስራኤል በዩኬ ማዕቀብ የሚጣልባት ከሆነ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ኪንግደም በዌስት ባንክ ከሚካሄደው የሰፈራ ማስፋፋት ጋር በተያያዘ በእስራኤል ላይ ማዕቀብ የምትጥል ከሆነ አገራቸው የአጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ሳር ገለፁ።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ፣ አገራቸው በእስራኤል ላይ የምትከተለውን የተሻሻለ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲ በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚያደረጉ ለፓርላማው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ከሹመታቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ በኃይል በተያዘው ዌስት ባንክ "አዳዲስ ሰፈራዎችን በፋይናንስ የሚደግፉ፣ የሚገነቡ እና የሚያስተዋውቁ" የእስራኤል ኩባንያዎችን እንዴት ማስቆም እንደሚቻል መንግሥታቸው እንደሚያጤን ገልጸዋል።

የእስራኤሉ አቻቸው ጌዲዮን ሳር በሰጡት ምላሽ "ብሪታንያ እስራኤል ላይ እርምጃ ከወሰደች እስራኤልም እርምጃ ትወስዳለች" ሲሉ ይኔት ለተባለው የእብራይስጥ ቋንቋ ድረገጽ ተናግረዋል።

"እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ፣ ትልቅ ስህተት ይሰራሉ ብዬ አስባለሁ" ሲሉም አክለዋል።

እስራኤል 'ኢ1' ተብሎ በሚጠራው የዌስት ባንክ አካባቢ 1200 የሰፈራ ቤቶችን ለመገንባት ባለፈው ወር ለኩባንያዎች ጨረታ አውጥታለች።

ለአዲስ የሰፈራ ቤቶች ግንባታ ጨረታ የወጣለት ኢ1፣ ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ቦታ ነው። ይህ እርምጃ ሰፊ ዓለም አቀፍ ውግዘት አስከትሏል።

አዲሱ ግንባታ ዌስት ባንክን ለሁለት የሚከፍል እና ምስራቅ ኢየሩሳሌምንም የሚነጥል ነው።

የዩኬው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚሊባንድ፣ እቅዱ "በዓለም-አቀፍ ሕግ መሰሸረት ሕገወጥ ነው" ካሉ በኋላ "የዌስት ባንክን ማዕከል የሚያቋርጥ እና የፍልስጤምን አገር ለመመስረት አደጋ በመሆኑ ቀይ መስመርን የሚያልፍ ነው" በማለት ተችተዋል።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃምም እንዲሁ፣ እስራኤል የያዘችው የኢ1 እቅድ የሁለት አገርነት መፍትሄን "አደጋ ላይ ሊጥል ወይም ሊያበቃ ይችላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።

ሁሉም ሰፈራዎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ሕገወጥ ናቸው። በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ምክንያት እስራኤል ለአስርት ዓመታት የሰፈራ መንደሮችን ግንባታ ሂደት አዘግይታ ቆይታለች።

ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያገኘው "የሁለት አገርነት መፍትሔ" ሀሳብ፣ ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማው ያደረገ ነጻ የፍልስጥኤም አገር በዌስት ባንክ እና በጋዛ እንዲመሰረት የሚጠይቅ ነው።

እስራኤል ይህን የሁለት አገርነት የመፍትሔ ሀሳብ አትቀበልም። የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ደግሞ ሀሳቡን የሚደግፉ ሲሆን፣ እስራኤል አገርነት የማይቀበለው ሐማስ በበኩሉ የሁለት አገርነት መፍትሔ እቅድ ተቃዋሚ ነው።