በጀርመን የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት እና ኔቶ በሩሲያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና ከፍ እንደሚያደርጉ ገለፁ

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን (በስተቀኝ) እና የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም በኅብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡ ሲሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን እና ማርክ ሩተ፣ ሩሲያ በአውሮፓ ላይ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ድፍረት እና ቸልተኝነት እያሳየች ነው ሲሉ ከሰዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኔቶ እና የአውሮፓ ኮሚሽን መሪዎች ሩሲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃላፊነት የጎደለው አደገኛ እና ቸልተኛ አካሄድ እየከተለች መምጣቷን አስጠንቅቀው ለ"አዲሱ ሁኔታ" ምላሽ እንደሚሰጡ አስታወቁ።

የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን "በላይፕዚግ ያጋጠመው ክስተት በቀጥታ ከሩሲያ ጋር የሚያያዝ እና በአውሮፓ ኅብረት ምድር ላይ የተፈጸመ አዲስ የግጭት ማባባስ ድርጊት ነው" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት፣ ጀርመን በለይፕዚግ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለተፈጸመው ያልተሳካ የድሮን ጥቃት ሩሲያን በወነጀለች ማግስት ነው።

አሜሪካን ጭምር በአባልነት ያካተተው የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጥምረት ከጀርመን ጋር በ"ሙሉ አጋርነት" እንደሚቆም የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ አስታውቀዋል።

ሩሲያ በነሐሴ መጀመሪያ ላይ በፈንጂዎች በተሞላ ድሮን የዩክሬን የዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላንን ዒላማ አድርጋለች የሚለውን ክስ ውድቅ አድርጋለች።

ክስተቱን ተከትሎ ጀርመን ለጣለችባት አዳዲስ ማዕቀቦች ምላሽ ለመስጠት በሩሲያ የሚገኙትን 'ጎተ ኢኒስቲትዩት' በመባል የሚታወቁ የጀርመን የባህል ማዕከላት እንደምትዘጋ አስታውቃለች።

በላይፕዚግ/ሃሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የነበረው ድሮን በስፍራው በሚገኝ ሮቦት አማካኝነት እንዳይፈነዳ የተደረገ ሲሆን፣ ሁለተኛው ድሮን ደግሞ ከሌላ የዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላን ጋር እንደተጋጨ ይታመናል።

ሌላ ሦስተኛ ድሮን ደግሞ፣ የኔቶ ዋና ማዕከል ከሆነው እና የዩክሬን የአንቶኖቭ ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በየጊዜው ከሚጠቀሙበት ከዚሁ አውሮፕላን ማረፊያ ከ10 ቀናት በኋላ መገኘቱ ተነግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፖሊስ ምርመራዎች እና የደኅንነት መረጃዎች ሩሲያ ከእነዚህ የድሮን ጥቃት ሙከራዎች ጀርባ እንዳለች ማረጋገጣቸውን የጀርመን መንግሥት ገልጿል።

የድሮኑ አወቃቀር፣ ክፍሎች፣ ፈንጂዎች እና ማቀጣጠያዎች በሌሎች የሩሲያ ድቅል ኦፐሬሽኖች የሚታወቁ መሆናቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በላይፕዚግ ጥቃት የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ተለይተዋል። አንደኛው በቱሪስት ቪዛ የገባ የሩሲያ ፓስፖርት ያለው ቤላሩሳዊ ነው። ሌላኛው የላቲቪያ እና የሩሲያ ፓስፖርት ያለው እና በአውሮፕላን በርሊን የገባ እንዲሁም ከከሸፈው ጥቃት ሁለት ቀናት በፊት ከጀርመን የወጣ ግለሰብ ነው።

በርሊን በቦን የሚገኘውን የሩሲያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እና የክሬምሊን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ እንደሆነ በሰፊው የሚታመነውን የሩሲያን የባህል ማዕከል እንደምትዘጋ አስታውቃለች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በርሊን ውንጀላውን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ አላቀረበችም ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ፣ ለበርሊን እርምጃ አገራችው በምትሰጠው አጸፋዊ ምላሽ፣ ሞስኮን ጨምሮ በሦስት የሩሲያ ከተሞች የሚገኙ የጀርመን ባህል ማዕከላት እንደሚዘጉ ተናግረዋል።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የጀርመንን እርምጃ "ከጀርመን ሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚቃረን" ትልቅ ስህተት ሲሉ ተችተዋል።

ሞስኮ ከበርሊን ጋር ያላትን ግንኙነት ልታቋርጥ ትችል እንደሆነ የተጠየቁት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሌክሳንደር ግሩሽኮ፣ "ሊሆን ይችላል" ግን ለዲፕሎማሲ ቅድሚያ እንሰጣለን ብለዋል።

ጀርመናውያን ተቺዎች፣ የአገራቸው እርምጃ በአንጻራዊነት ደካማ ነው ሲሉ መንግሥታቸውን ወቅሰዋል። ይሁን እንጂ በርሊን ከአጋሮቿ ጋር በመሆን በምትወስዳቸው የጋራ እርምጃዎች ላይ ዐይኗን ጥላለች። ይህም በአውሮፓ ኅብረት የተጣለውን ማዕቀብ ማራዘም እና ሩሲያውያን ጎብኚዎች ወደ አባል አገራት እንዳይገቡ ማገድን ያካትታል።

የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ቮን ደር ሌይን "ይህንን ስታደርጉ አንታገስም" ብለዋል።

እርሳቸው በብራሰልስ ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ሩተ ጋር ሲወያዩ፣ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደግሞ በአየርላንድ ተሰብስበዋል።

የፈረንሳዩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአውሮፓን ማዕቀቦች ለማምለጥ በድብቅ በሚደረጉ የሩሲያ የነዳጅ እና ሌሎች የጭነት መርከቦች እንቅስቃሴን ዒላማ ያደረጉ እርምጃዎች በአውሮፓ ደረጃ ይወሰዳሉ ብለዋል።

አብዛኛው የአውሮፓ ኅብረት አገራት፣ ከ193 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የሚሆኑ ታግደው የሚገኙ የሩሲያ ሀብቶች ዩክሬንን ለመርዳት እንዲውሉ ግፊት እያደረጉ ነው። ሀሳቡ መጀመሪያ የተነሳው በአውሮፓውያኑ 2025 መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፣ ገንዘቡ የሚገኝባት ቤልጂዬም ግን አልተቀበለችውም።