ኢራን እና አሜሪካ መልዕክት መለዋወጥ “አላቋረጡም” - የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር መልዕክት መለዋወጥ “አለማቋረጧን” ተናገሩ።
ቃል አቀባዩ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህንን ቢሉም የመልዕክት ልውውጡ እስከ ትናንት ድረስ መቀጠል አለመቀጠሉን አላረጋገጡም።
አክለውም የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሺን ናቅቪ ከሁለት ቀን በፊት ቴህራን የመጡት “ንግግሮች እንዲቀጥሉ ለማገዝ እና ከድርድር ጋር ያሉ ጉዳዮችን ለመነጋገር” ነው ብለዋል።
ፓኪስታን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በሚደረገው ድርድር ውስጥ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች።
ናቅቪ ወደ ቴህራን የሄዱት ከፓኪስታኑ መሪ ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ የተላከ ደብዳቤ ይዘው ነበር።
አንዳንድ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከሳምንት በፊት እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን ድብደባ በመቃወም ቴህራን ከዋሺንግተን ጋር የመልዕክት ልውውጧን አቋርጣለች በሚል ዘግበው ነበር።
ቴህራን አና ዋሺንግትን የተኩስ አቁም ካደረጉ እአአ ከሚያዚያ 8 ጀምሮ የመልዕክት ልውውጥ እያደረጉ መሆናቸው ሲገልጽ ቆይቷል።
ሚያዚያ 11 እና 12 የሁለቱ አገራት ልዑካን በኢዝላማባድ ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።