ቀጥታ , የሁቲዎች እና ሳዑዲ ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል

የየመን ሁቲዎች ረቡዕ ዕለት ራስ ታኑራ በተባለው የሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ እና በሪያድ የፋይናንስ ቀጣና ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ። ሳዑዲ አረቢያ፣ ሁቲዎች ራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የሰነዘሩትን የድሮን ጥቃት ማክሸፏን ተናግራለች። የሳተላይት ምስሎች ግን ከዚህ ነዳጅ ማጣሪያ ስፍራ ላይ ትልቅ ጭስ ወደላይ እየወጣ መሆኑን አሳይተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩክሬን ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አምስት የሩሲያ የጦር ጄቶች መመታታቸውን ገለጸች

    ዩክሬን ከሞስኮ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሩሲያ ሳቫስሌይካ የአየር ኃይል ማረፊያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት አምስት የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ላይ ጉዳት ማድረሷን አስታወቀች።

    ሦስት ሚግ-31 እና ሁለት ሱ-34 ተዋጊ አውሮፕላኖች መመታታቸውን የዩክሬን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

    የደረሰው ጉዳት መጠን ገና እየተገመገመ መሆኑን የጠቀሰው ጽሕፈት ቤቱ፣ “ከዚህም የተሻለም ዜና ሊሰማ ይችላል” ብሏል።

    የአየር ኃይል ማረፊያው ለመምታት ምን ዓይነት የጦር መሣሪያዎችን እንደተጠቀመ ግን አላብራራም።

    ሩሲያ እስካሁን ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት አስተያየት አልሰጠችም።

    በሩሲያ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ክልል የሚገኘው ሳቫስሌይካ የአየር ኃይል አውሮፕላን ማረፊያ ለበርካታ ዓመታት በዩክሬን ዒላማ ሲደረግ ቆይቷል። አየር ማረፊያው የሩሲያን ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች እና ተንሸራታች ቦምቦችን ለማስወንጨፍ የምትጠቀምባቸውን አውሮፕላኖች ያስተናግዳል።

    ከስፍራው የሚነሱት በተለይም የሩሲያ ሚግ-31 ጄቶች የሚሸከሟቸው ኪንዣል ሚሳዔሎች ትላልቅ መሠረተ ልማቶችን እና ወታደራዊ ዒላማዎችን በመምታት የሚታወቁ ሲሆን መትቶ ለመጣልም አስቸጋሪ ናቸው።

    በዚህም የተነሳ ሚግ-31 ጄቶች እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በመላው ዩክሬን በተደጋጋሚ አገር አቀፍ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሎች እንዲጮሁ ይደረጋል።

    በተጨማሪም ዩክሬን ሌሊቱን በፈጸመችው ጥቃት፣ ከጦር ግንባር 800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኘው የሩሲያ ሳማራ ክልል ሁለት የነዳጅ ማጣሪያዎችን መምታቷን ገልጻለች። ኪዬቭ የሞስኮን ነዳጅ ማጣራት አቅም ያዳከሙ ተከታታይ የረጅም ርቀት ጥቃቶች መፈጸሟ ይታወሳል።

    የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር፣ “ጠገናችኋቸው? እንደገና እንመታቸዋለን” የሚል ዛቻ አስተላልፏል።

    የሳማራ ክልል አስተዳዳሪ ቭያቼስላቭ ፌዶሪሽቼቭ ሌሊቱን የተፈጸሙትን ጥቃቶች “ትክክለኛ መከራ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። ከ145 በላይ ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውንም ተናግረዋል።

    አስተዳዳሪው እንደሚናገሩት፣ በጥቃቶቹ አንድ ሰው ሲገደልም፣ በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።

    በተጨማሪም ኪዬቭ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ የዩክሬን ግዛቶች ውስጥ አንድ የራዳር ሥርዓት እንዲሁም የነዳጅ እና የሎጂስቲክስ ማከማቻዎችን መምታቷን አስታውቃለች።

    የኪዬቭ የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ በፍጥነት እያደረገ ነው። ሞስኮ ሙሉ ወረራ ከጀመረች ወዲህ ባሉት ዓመታት ዩክሬን ከጦር ግንባር በብዙ ርቀው በሚገኙ የሩሲያ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟል የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

    የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአገሪቱ የኃይል ማመንጫ እና ነዳጅ ተቋማት ዙሪያ የሚወሰዱ የደኅንነት እርምጃዎች እንዲጠናከሩ ማክሰኞ ዕለት ጥሪ አቅርበዋል።

    ሩሲያ “ወሳኝ ጉዳት” ሳይደርስባት የአገር ውስጥ የነዳጅ ገበያዋን ማረጋጋት መቻሏን የሚናገሩት ፑቲን፣ ሞስኮ በኪዬቭ ላይ “አይቀሬ” የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ዝተዋል።

  2. የየመን ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገለጹ

    የየመን ሁቲዎች ረቡዕ ዕለት ራስ ታኑራ በተባለው የሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያ እና በሪያድ የፋይናንስ ቀጣና ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ ሁቲዎች ራስ ታኑራ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ የሰነዘሩትን የድሮን ጥቃት ማክሸፏን ተናግራለች። የሳተላይት ምስሎች ግን ከዚህ ነዳጅ ማጣሪያ ስፍራ ላይ ትልቅ ጭስ ወደላይ እየወጣ መሆኑን አሳይተዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ጥቃት እንደፈጸሙበት የገለጹት ራስ ታኑራ፣ ከዓለም ትላልቅ የድፍድፍ ነዳጅ ኤክስፖርት ወደቦች አንዱ አጠገብ የሚገኝ የሳዑዲ አረቢያ ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ነው።

    600 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ገደማ ስፋት እንዳለው የሚገመተው የነዳጅ ማጣሪያ ስፋቱ ከአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ ጋር እንደሚቀራረብ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭን ጠቅሶ ዘገቧል።

    በሌላ በኩል፣ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር ረቡዕ ዕለት በአገሪቱ የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ጂዳ ወደብ አቅራቢያ አንድ የሁቲ ድሮንን ጠልፎ ማውደሙን አስታውቋል።

    የየመን ሁቲዎችም ይህ ከተገለጸ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ሳዑዲአረቢያ በየመን ወደብ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ መውሰዳቸውን ተናግረዋል። በዚህ የአጸፋ ጥቃት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን ሁለቱን የጂዳ እና የጃዛን ወደቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    የሁቲዎች እና የሳዑዲ መራሹ ጥምር ጦር ግጭት ባለፉት ቀናት ይበልጥ ተባብሶ ታይቷል።

    የትናንቶቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከሁቲዎች ጋር የሚዋጋው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት፣ በየመን የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘውን የሆዴይዳ ወደብን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው።

    የሁቲዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ “ሁለቱም ዘመቻዎች ዒላማዎቻቸው ላይ ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል።

    ከዚህ አስቀድሞ፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በሁቲዎች የተወነጨፈ ተተኳሽ ጃዛን ወደብ ላይ ማረፉን አስታውቆ ነበር።

    የሳዑዲ መራሹ ጥምረት ቃል አቀባይ ቱርኪ አል ማሊኪ “ቀላል ጉዳት የደረሰ ሲሆን የተገደለ ወይም የቆሰለ ሲቪል የለም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

    አክለውም «የተተኳሹን ዓይነት ለመለየት ጥረቶች ቀጥለዋል” ብለዋል።

    ዋና ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ አብዛኛውን የምዕራብ የመን ክፍል የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች፣ ረግቦ የነበረው የመን ግጭት በኢራን ጦርነትን ምክንያት ባለፈው ሐምሌ ላይ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሳዑዲ አየር ማረፊያዎች፣ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች እና የመስሪያ ቤት ሕንፃዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

    ከዚህ ቀደም በግዙፉ የሳዑዲ የነዳጅ አምራች አራምኮ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ተቋሙ በጊዜያዊነት ሥራ እንዲያቆም አስገድደው ነበር። አየር ማረፊያዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶችም ወደ ሪያድ የሚደረጉ አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆነዋል።

  3. የኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባ ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።