ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ አዘዙ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች እንቅስቃሴን እንዲያግድ ማዘዛቸውን አስታወቁ። በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለረጅም ሰዓታት ፓኪስታን ውስጥ የተካሄደው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ ላይ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሰበር, ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ አዘዙ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች እንቅስቃሴን እንዲያግድ ማዘዛቸውን አስታወቁ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለረጅም ሰዓታት ፓኪስታን ውስጥ የተካሄደው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ ላይ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።

    "ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ ተከናውኖ በአብዛኞቹ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ በሆነው በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ግን መስማማት አልተደረሰም” ብለዋል።

    ጨምረውም በሆርሙዝ በኩል የሚደረግ ነጻ እንቅስቃሴን በሚመለከት ከስምምነት ሊደረስ እንሚችል አመልክተው፤ ነገር ግን “ኢራኖች ከእነሱ ውጪ ማንም የማያውቃቸው ‘በባሕሩ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ፈንጂዎች ሊኖሩ ይችላሉ’ በማለት ፈቃደኛ አልሆኑም” ሲሉ አስፍረዋል።

    ስለዚህም ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ባሕር ኃይላችን በዓለም አቀፍ የውሃ አካል ላይ ለኢራን የመተላለፊያ ገንዘብ የከፍሉ መርከቦችን እንዲያስቆም” ማዘዛቸውን እና ባሕር ኃይላቸው “በኢራን የተጠመዱ የባሕር ላይ ፈንጂዎችን ማስወገድ ይጀምራል” ብለዋል።

    “ሕገወጥ የመተላለፊያ ክፍያውን የፈጸመ የትኛውም መርከብ እንዲያልፍ አይፈቀድለትም” በማለት “በእኛ ላይ ወይም በሰላማዊ መርከቦች ላይ የሚተኩስ ማንኛውም ኢራናዊ መአት ይወርድበታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ ባሕር ኃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚዘጋም ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።

  2. ከአሜሪካ ጋር በተደረገው ንግግር የኢራን ልዑክ የመሩት አፈጉባኤ ማን ናቸው?

    ወግ አጥባቂው እና ወታደራዊ ዳራ ያላቸው ፖለቲከኛ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ ነበሩ ወደ ኢዝላማባድ ከአሜሪካ ገር ለመደራደር ያቀናውን ልዑክ የመሩት።

    ባለቤትነቱ የኢራን መንግሥታዊ ብሮድካስተር የሆነው አል ዓላም የአረብኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጋሊባፍ ከሃይማኖተኛ እና ሠራተኛ ቤተሰብ የተወለዱት በሰሜን ምሥራቅ ቶርጋቤህ ከተማ ውስጥ ነው።

    የትውልድ ከተማቸው የተወሰኑ የእስላማዊ አብዮቱ ስመ ጥር ግለሰቦች ለኖሩበት ማሻድ ከተማ ይቀርባል። 16 ዓመት ሲሆናቸው ማሻድ ውስጥ ወደሚገኙ ዋና ዋና መስኪዶች በመሄድ፤ ኋላ ላይ ጠቅላይ መሪ የሆኑትን አሊ ኻሜኔን ጨምሮ የሌሎችንም አብዮታዊ የሃይማኖት መምህራን ትምህርቶች ተከታትለዋል።

    ጋሊባፍ በአውሮፓውኑ 1979 እስላማዊው አብዮት ከፈነዳ ከአጭር ጊዜ በኋላ በኢራቅ ጦርነት ተዋግተዋል። የኢራን አብዮታዊ ዘብን የተቀላቀሉትም በ20 ዓመታቸው ነው።

    ከሁለት ዓመት በኋላ የአብዮታዊ ጦሩ አንድ የውጊያ ክፍል አዛዥ ሆነዋል። ጦርነቱ በ1988 እስከሚጠናቀቅ ድረስም በዚህ የኃላፊነት ደረጃ ላይ አገልግለዋል።

    ጋሊባፍ ትዳር የመሠረቱት የአብዮታዊ ዘብ አዛዥ በሆኑበት ዓመት ነው። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የመሩት የመጀመሪያው ጠቅላይ መሪ ሩሆላ ኻሜኒ እንደሆኑ የአል ዓላም ዘገባ ያመለክታል። በዚህ ትዳራቸው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።

  3. በኢራን የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ከ3500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ለ40 ቀናት በዘለቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በኢራን ውስጥ 3753 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    የኢራን ባለሥልጣናት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተደረጉ የአስከሬን ምርመራዎችን በመጥቀስ “2875 ወንዶች እና 496 ሴቶች” በጦርነቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል።

    በኢራን ከፍተኛ የሟች ቁጥር የተመዘገበው በቴህራን፣ ሆርሞዝጋን እና ኢስፋሃን ከተማዎች መሆኑ ተገልጿል።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት የተገደሉ ሲሆን ሰባቱ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች እንደሚሆናቸው 255ቱ ደግሞ ከአንድ ዓመት እስከ 12 ዓመታቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

    121ዱ ደግሞ ከ13 እስከ 18 ዓመት ድረስ እንደሚሆናቸው መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባዎች የተገደሉት ኢራናውያን ብቻ ሳይሆኑ በአገሪቱ የሚኖሩ የአፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ ፓኪስታን፣ ቻይና፣ ኢራቅ እና ሊባኖስ ዜጎች ጭምር ናቸው ብዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነት ወቅት ስለሚሞቱ ሰዎች የሚገልጽ መረጃ ይፋ የሚያደርጉት አልፎ አልፎ ነው።

    በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን የሟቾች ቁጥርን ሲገልጹ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ብቻ ያተኩራሉ።

    ከዚህ በፊት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውስጥ የኢራን ተወካይ 1500 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረው ነበር።

    መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች አክቲቪስቶች ቡድን በበኩሉ 3400 ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ ከእነዚህ መካከል 1600 ያህሉ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው ብሎ ነበር።

  4. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር አሜሪካ እና ኢራን ‘ከስምምነት ለመድረስ እንዲሠሩ’ ጥሪ አቀረቡ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በፓኪስታን ተካሂዶ ያልተሳካውን ውይይት ተከትሎ ኢራንም ሆነች አሜሪካ “አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ’ ጥሪ አቀረቡ።

    ስታርመር ከኦማን ሱልጣን ጋር ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ስምምቱ መቀጠሉ "አስፈላጊ" እንደሆነ እና "ሁሉም ወገኖች ተጨማሪ ግጭቶች እንዲያስወገዱ" ጠይቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የዩኬ የጤና ሚኒስትር ዌስ ስትሪትይንግ እሑድ ዕለት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የተደረገው የመጀመሪያ ውይይት አለመሳካቱ “አሳዛኝ" መሆኑን ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ዩኬ በግጭቱ ላይ ላለመሳተፍ የወሰደችውን አቋም ስትራይቲንግ ተከላክለዋል።

  5. የኢራን ፓርላማ አፈጉባዔ አሜሪካ ‘የኢራናውያን ልዑክን እምነት ማግኘት አልቻለችም” አሉ

    የቴህራንን ተደራዳሪ ልዑክ የመሩት የፓርላማው አፈጉባዔ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ አሁን ጊዜው አሜሪካ “እምነታችንን ማግኘት ትችል እንደሆን ወይም እንዳልሆነ የምትወስንበት ነው” አሉ።

    ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ ከድርድሩ በፊት ኢራን “ቀና ልቦና እና ፍላጎት” ነበራት ብለዋል።

    ነገር ግን ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ሁለት ጦርነቶች ጋር በተያያዘ ባለን ልምድ የተነሳ “በተቃራኒው ወገን ላይ እምነት የለንም” ብለዋል።

    የኢራን ልዑካን ቡድን “የፊቱን የሚመለከት ጉዳዮችነ አንስቶ ነበር፤ ነገር ግን ተቃራኒው ወገን በዚህ ድርድር የኢራናውያን ልዑክ እምነት ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።”

    በመቀጠልም “በአርባ ቀናት የኢራን ብሔራዊ የመከላከያ ሰራዊት የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር የምናደርገውን ጥረት ለአፍታ ሸብረክ አንልም።

    ድርድሩ “ውጥረት የተሞላው” እንደነበር ተናግረው ፓኪስታንን ይህንን ድርድር ስላመቻቸች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

  6. ‘የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ቁጥጥር ስር ነው እናም ቀረጥ መከፈል አለበት’ የፓርላማው ምክትል አፈ ጉባዔ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በፓኪስታን የተደረገው የሰላም ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥን አላነሱም።

    የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ የሆነው ይህ የባሕር መስመር በሁሉ አገራት የሰላም ንግግር ወቅት አከራካሪ ከሆኑ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የሰላም ስምምነት ሲደዕስ ቁልፉ ሃሳብ በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ያለምንም ችግር መተላለፍ እንዲችሉ የሚል ነበር።

    ሜኸርስ የዜና ወኪል የኢራን ፓርላማ ምክትል አፈጉባዔ ሃጂ ባቤይ ወሽመጡ ለኢራን ቀይ መስመር መሆኑን መናገራቸውን ዘግቧል።

    ወሽመጡ በኢራን ሙሉ ቁጥጥር ስር ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔው “ቀረጥ በሪያል [በኢራን መገበያያ ገንዘብ] መከፈል አለበት” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ “በቅርቡ ይከፈታል” ሲሉ ጽፈው ነበር።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ሁለት ፈንጂ አምካኝ መርከቦች አካባቢውን ከፈንጂዎች ለማጽዳት “ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ተሰማርተዋል” ብሏል።

    ነገር ግን ኢራን ሁለቱ መርከቦች ወደ ወሽመጡ መምጣታቸውን አስተባብላለች።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ “በሆርሙዝ ባህር ለማለፍ ወታደራዊ መርከቦች የሚያደርጓቸው ማንኛውም ሙከራ ከባድ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል” ማለቱን ኢሪብ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  7. የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ንግግሩ የተካሄደው አለመተማመን፣ ጥርጣሬ እና ጥያቄ ባንዣበበት ሁኔታ ውስጥ ነው” አሉ

    በፓኪስታን ኢዝላማባድ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረገውን ያልተሳካ ድርድር ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየቱን ሰጥቷል።

    ኢራን ቀደም ሲል አሜሪካ “ከተለጠጠ ፍላጎቷ” መታቀብ እንዳለበት ተናግራ ነበር።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ አሜሪካ እና ኢራን ወዲያውኑ ከስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ተናግረዋል።

    ንግግሩ የተደረገው “አለመተማመን፣ ጥርጣሬ እና ጥያቄ በተሞላበት ከባቢ ውስጥ ነው” ሲሉ አክለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት 40 ቀን ከሞላው በኋላ ነው ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ የተቻለው።

    ባጌይ ለኢራን የተማሪዎች ዜና ኔትወርክ “ከመጀመርያውም በአንድ ጊዜ ከስምምነት ላይ እንደርሳለን ተብሎ መጠበቅ የለበትም። ማንም ቢሆን እንደዚያ ያለ ግምት ያለው አይስለኝም” ብለዋል።

    አክለውም አሁንም “ዲፕሎማሲ ፈጽሞ አላበቃለትም” ብለዋል።

  8. ድርድሩ አልተሳካም፡ ቀጥሎስ ምን ይሆናል?

    ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን እንዳሸነፉ በመግለጽ ወደ ድርድሩ መድረሳቸውን ተከትሎ ስምምነቱ ሁልጊዜ አስቸጋሪ እንደሚሆን የተጠበቀ ጉዳይ ነው።

    በመጨረሻም የማይቻል መስሏል። ሁለቱም ወገኖች ላለመስማማታቸው ሌላኛውን አካል ተጠያቂ አድርገዋል።

    ዋናው ጥያቄ ቀጥሎ ምን ይፈጠራል የሚለው ሆኗል?

    ረቡዕ ዕለት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የተጀመረው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ስልጣኔ እንደሚያጠፉ የሚገልጽ ዛቻ ከሰነዘሩ በኋላ ነው።

    በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንደገና ይቀጥላሉ ወይ የሚለውን በተመለከተም እስካሁን ምንም መረጃ ባይገኝም ጥቃት የመቀጠሉ ዕድሉ ጨምሯል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን በድርድር እንደገና የመከፈት ጉዳይም ከስምምነት ውጭ ይመስላል። ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች የባሕር ውስጥ ፈንጂን ለማጥራት ወደ ባሕረ ሰላጤው መሰማራታቸው አሜሪካ ሌላ መንገድ እንዳየች ያሳያል።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ላለመታጠቅ ቃል መግባት አለመቻሏን ትልቁ እንቅፋት እንደሆነ አሜሪካ ጠቅሳለች። ኢራን ሁልጊዜም የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትፈልግ ብትገልጽም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጦርነቶች ውስጥ መግባቷ መሣሪያውን እንድትታጠቅ ለሚጠይቁ ሰዎች ተጨማሪ ማበረታቻ ሆኗቸዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው የፊት ለፊት ውይይት ታሪካዊ ቢሆንም የዲፕሎማሲ ውድቀት ተደርጎ ሊታወስ ይችላል።

  9. በፓኪስታን እየተደረገ ስለነበረው እና ያለ ውጤት ስለተበተነው ድርድር አሜሪካ ምን አለች?

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በፓኪስታን የኢራንን ጦርነት ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ድርድር ለረዥም ሰዓት ከተደረገ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

    ምክትል ፕሬዚዳንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር አጅበዋቸው ነበር።

    ጄዲ ቫንስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በርካታ ነጥቦችን አንስተዋል።

    • በኢዝላማባድ ለ21 ሰዓታት ከኢራን ጋር ንግግር ቢደረግም ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።
    • "ከኢራናውያን ጋር በርካታ ተጨባጭ ውይይቶችን አድርገናል፤ ይህ ጥሩ ዜና ነው። መጥፎው ዜና ስምምነት ላይ አለመድረሳችን ነው፤ እናም ይህ ከዩናይትድ ስቴትስ የበለጠ ለኢራን መጥፎ ዜና ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ቫንስ ተናግረዋል።
    • “ኢራናውያን አቋሞቻችንን የሚቀበሉበት ሁኔታ ላይ አልደረሰንም”
    • ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ እና ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ያላቸውን አድናቆት ገልጸው በድርድሩ ላይ "ምንም ዓይነት ጉድለቶች ቢኖር ድንቅ ስራ በሰሩት ፓኪስታናውያን ምክንያት አልነበረም" ብለዋል።
    • ቫንስ ስለ ኢራን የኒውክሌር አቅም ተጠይቀው ሲመልሱ አገሪቱ አሁንም ሆነ ወደፊት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ መግታት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ዋና ግብ" ነው ሲሉ መልሰዋል።
    • ትራምፕ በድርድሩ ላይ መሳተፋቸውን ገልፀው ንግግሩ እየተደረገ ባለበት ወቅት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ከ"ግማሽ ጊዜ በላይ" ወይም “በርካታ ጊዜ" ተነጋግረናል ብለዋል።
    • “ከዚህ ስንሄድ ትተን የምንሄደው ቀላል ምክረሃሰብ ነው፤ ይህ የመጨረሻ እና ምርጡ መደራደሪያችን ነው። ኢራናውያን ይቀበሉት ከሆነ የምናየው ነው” ብለዋል።
  10. አሜሪካ የያዘቻቸውን የኢራን ሀብቶች ለመልቀቅ ተስማምታለች መባሉን የዋሽንግተን ባለሥልጣናት አስተባበሉ

    አሜሪካ ለዓመታት እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው የቆዩትን የኢራን ሀብቶች ለመልቀቅ ተስማምታለች መባሉን የዋሽንግተን ባለሥልጣን ማስተባበላቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    አንድ ኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን አሜሪካ የቴህራን ሀብቶችን የመልቀቅ እርምጃ መውሰዷ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።

    እንደ ምንጩ ገለጻ ሀብቱን የመልቀቅ እርምጃው “በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ጉዞን ደኅንነት ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ” ነው።

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍም ድርድር ከመጀመሩ በፊት ሀብቶቹ መለቀቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ጉዳዩን ለደጋፊዎቻቸው ለማብራራ ችግር ይገጥማቸዋል።

    ዘገባው ከወጣ በኋላ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ምላሽ የሰጡ የዋሽንግተን ባለሥልጣናት ግን ጉዳዩን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዲለቀቀ ያልፈቀደው 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢራን ሀብት እንደያዘች የገለጸችው ኳታርም ማስተባበሏል በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

  11. የሄዝቦላህ ባለሥልጣን ከእስራኤል ጋር ንግግር የሚያደርገውን የሊባኖስ መንግሥት ወቀሱ

    የሄዝቦላህ አባል የሆኑት ሕግ አውጪው ሀሰን ፋድላላህ ከእስራኤል ጋር ንግግር ሊያደርግ ተዘጋጀው የሊባኖስ መንግሥት ላይ ወቀሳ አቀረቡ።

    ሕግ አውጪው አስተያየት የሰጡት፤ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ ንግግር እንደሚካሄድ ካስታወቁ በኋላ ነው።

    እስራኤል በበኩሏ ከሊባኖስ ጋር በምታደርገው የተኩስ አቁም ንግግር ውስጥ ሄዝቦላህ እንደማይሳተፍ ገልጻለች።

    ሕግ አውጪው ፋድላላህ በሄዝቦላህ በሚተዳደረው አል ማናር ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በወጣው መግለጫቸው፤ የአገሪቱን መንግሥት እርምጃ “ግልጽ የሕገ መንግሥት እና የሊባኖስ ሕግጋት ጥሰት” ሲሉ ጠርተውታል።

    ድርድሩ በሊባኖስ ያለውን “የአገር ውስጥ ክፍፍል ያባብሰዋል” ሲሉም ተችተዋል።

    አክለውም፤ "ጠላት በውጊያ ሜዳ ሊያሳካ ያልቻለውን ነገር... የውሳኔ ሰጪነት አቅም በሌለው፣ መሠረታዊ ግዴታዎቹን በዘነጋ፣ ሕዝቡን መጠበቅ በተሳነው እና የሀገርን ሉዓላዊነት ያስከብራል ተብሎ ሊታመን በማይችል አካል በኩል በሚደረግ ድርድር አያገኘውም” ብለዋል።

  12. የኢራን ባለ 10 ነጥብ እቅድ - ተደራዳሪዎች ማሳካት የሚፈልጉት ምንድነው?

    ለዛሬው ድርድር ቀጠሮ ከመያዙ አስቀድሞ ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ድርድር ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ተዘግቶ በከረመው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች ለማለፍ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጾ ነበር።

    ኢራን በበኩሏ የራሷን ባለ 10 ነጥብ የድርድር እቅድ አቅርባለች። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "እቅዱ ለድርድር መነሻነት ሊያገለግል ይችላል" ብለዋል።

    በዚህ የኢራን እቅድ እና አሜሪካ ባቀረበችው ባለ 15 ነጥብ መደራደሪያ ውስጥ ምን ጉዳዮች እንደተካተቱ የሚገልጹ የተለያዩ ዘገባዎች ቢወጡም እስካሁን ድረስ የእቅዶቹ ይዘት በይፋ አልተገለጸም።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በቴህራን እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በቀጣናው የሚደረግ ጦርነት በሙሉ እንዲቆም የሚጠይቀው ነጥብ ይገኝበታል።

    ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ለማንሳት “ሙሉ ቁርጠኝነት” እንዲሰጥ እንዲሁም በአሜሪካ የተያዙት የኢራን ገንዘብ እና ሀብቶች እንዲለቀቁ ተጠይቋል። በጦርነቱ ኢራን ላይ ለደረሰው ጉዳት “መልሶ ግንባታ ወጪ መሸፈኛ የሚሆን ሙሉ የካሳ ከፍያ” እንዲፈጸም የሚለውም ቴህራን ባቀረበችው እቅድ ውስጥ ተካትቷል።

  13. የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ለኢራን ድርድር ፓኪስታን ገቡ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና ተደራዳሪ ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ድርድር ከልዑክ ቡድናቸው ጋር ፓኪስታን ገቡ።

    ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ጋር ኢስላማባድ ከተማ የገቡት ቫንስ ከሰዓታት በኋላ በሚጀምረው የንግግር ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    ለአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት አቀባበል ያደረጉት የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐማድ ኢሻቅ ዳር ዋሽንግተን ለዘላቂ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

    ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ እና ኢራን “ገንቢ በሆነ መልኩ ተሳትፎ ያደርጋሉ” የሚል ተስፋቸውን መግለጻቸውን የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። ፓኪስታን ሁለቱም ወገኖች ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ያላትን ፍላጎት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

    ጄዲ ቫን ወደ ፓኪስታን ከመጓዛቸው በፊት ባደረጉት ንግግር “ድርድሩ እንዲካሄድ እየጠበቁ” እንደሆነ ገልጸው፤ ነገር ግን ኢራን “ለመጫወት እንዳትሞክር” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራኑን ተደራዳሪ ቡድን የሚመሩት አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ በበኩላቸው “ቀና ፍላጎት አለን፤ ነገር ግን እምነታችንን አንጥልም” ሲሉ ፓኪስታን ከደረሱ በኋላ መናገራቸውን የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

    “ከአሜሪካውያን ጋር በነበረን የድርድር ልምድ ሁልጊዜም ሲያጋጥመን የነበረው ክሽፈት እና የቃል ኪዳኖች መሰበር ነው” ብለዋል።

  14. አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ የደረሰባቸው ከፍተኛ እና አካል የሚያጎድል ጉዳት እንደሆነ ሮይተርስ ዘገበ

    የኢራን ጠቅላይ መሪነት ሥልጣንን ከተረከቡ ወዲህ በአካል ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት ከደረሰባቸው የፊት እና የእግር ጉዳት እያገገሙ እንደሆነ በቅርባቸው ካሉ ምንጮች መስማቱን ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው አዲሱ ጠቅላይ መሪ በጥቃቱ ፊታቸው እንደተበላሸ እና አንድ ወይም ሁለት እግሮቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ሦስት ምንጮች ተናግረዋል።

    ይህም ቢሆን ግን የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ከጉዳታቸው እያገገሙ እንደሆነ እና አዕምሯቸው ስል ሆኖ መቀጠሉን ምንጮቹ ገልጸዋል ተብሏል።

    በድምጽ በሚደረጉ የኦንላይን ስብስብሰባዎች ላይ እየተሳተፉ እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር እንደሚሄደው ድርድር ባሉ ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

    በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት አባታቸውን ተክተው ወደ ሥልጣን የመጡት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ በዚሁ ዕለት የደረሰባቸው ጉዳት መጠን እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።

    ከዚህ ቀደም የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ጥቅም ላይ የሚውልን ቃል በመጠቀም ያሉበት ሁኔታ ጠቁሞ ነበር።

    የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በበኩላቸው ኻሜኒ “መቁሰላቸውን እና አካል መጉደል ደርሶባቸው ሊሆን እንደሚችል” ባለፈው ወር ተናግረው ነበር።

    የአሜሪካ የስለላ መረጃ ግን ኻሜኒ እግራቸውን አጥተዋል ተብሎ እንደሚታመን ማሳየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ መናገራቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።