ትራምፕ መርከቦች ከአሜሪካ ነዳጅ ለመጫን እየመጡ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እና ሙሉ በሙሉ ባዶ የሆኑ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ከአሜሪካ ነዳጅ እና ጋዝ ለመጫን እየመጡ አሉ።
ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ ወደ አሜሪካ እየተጓዙ ያሉት “እጅግ ከፍተኛ ቁጥር” ያላቸው ባዶ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።
“በዓለም የትኛውም ቦታ ከሚገኘው [ነዳጅ] ምርጥ እና ‘ጣፋጭ’ የሆነውን የነዳጅ ዘይት (እና ጋዝ!)” ይጭናሉ ሲሉም ተናግረዋል።
አሜሪካ “ቀጣዮቹ ሁለት ትላልቅ የነዳጅ ባለቤት አገራት ተደምረው ካላቸው በላይ የሆነ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ አላት” በማለት ጽፈዋል። “እየጠበቅናችሁ ነው” ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በጦርነቱ ምክንያት ለተቃወሰው የነዳጅ አቅርቦት መፍትሔ የሚመስሉ ዜናዎች ሲሰሙ ደግሞ ዋጋው ሲቀነስ ተስተውሏል።
የነዳጅ ዋጋን ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውለው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ የአንድ ቤርሜል ዋጋው በሳምንቱ መጀመሪያ ከነበረበት 111 ዶላር በ15 በመቶ በመቀነስ 92 ዶላር ገብቷል።
የነዳጅ ዋጋ የቀነሰው የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን የሚያካትተው የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም በመደረጉ ነው።
ኢራን ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ የሆነውን ሆርሙዝ መዝጋቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ የጨመረ ሲሆን ይህ ጭማሪም የምግብ ዋጋን አንሯል።
በዚህ ሳምንት የነዳጅ ዋጋ ላይ ቅናሽ ቢታይም አሁንም ከጦርነቱ በፊት ከነበረው አንጻር ከፍተኛ ነው። ከኢራን ጦርነት በፊት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 70 ዶላር ገደማ ነበር።



















