ቀጥታ, አሜሪካ በሳምንታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢራን ላይ ጥቃት ስትፈጽም፤ ቴህራን የአጸፋ እርምጃ ወሰደች

የአሜሪካ ጦር ከሐምሌ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢራን በፈጸመው ጥቃት ላራክ ደሴት ላይ የሚገኙ ማስወንጨፊያዎችን መምታቱን አንድ የዋሽንግተን ባለሥልጣን ተናገሩ። የኢራን አብዮታዊ ዘቡ በበኩሉ፣ በዮርዳኖስ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ነዳጅ መቅጃ የያዘ ሰው እጅ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    አሜሪካ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ ምሽት ኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ።

    ባለፈው ሳምንት ቅናሽ ሲመዘገብበት የነበረው የነዳጅ ዋጋ ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ የሁለት በመቶ ገደማ ጭማሪ ታይቶበታል።

    የነዳጅ ዋጋ መለኪያ ተደርጎ የሚቆጠረው ብሬንት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ የ1.77 ዶላር ጭማሪ ታይቶበት በ89.87 ዶላር እየተሸጠ ነው።

    አሜሪካ ከሐምሌ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚታወቅ ደረጃ በፈጸመችው የትናንቱ ጥቃት ላራክ በተባለው የኢራን ደሴት የሚገኙ ሁለት ማስወንጨፊያዎችን መምታቷን አስታውቃለች።

    ይህንን ተከትሎም ኢራን በዮርዳኖስ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች።

    ስድስት ወራት ያስቆጠረው የኢራን ጦርነት በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከዓለም የነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ገደማው የሚተላለፍበት ሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን በመዘጋቱ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ ደርሶ ነበር።

    ሁለቱ አገራት የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ረገብ ማለታቸውን ተከትሎ ደግሞ ቅናሽ ተስተውሏል።

    ወሳኝ የባሕር መስመር የሆነው ሆርሙዝም በዛሬው ዕለት ጥቃት እንዳስተናገደ ተገልጿል። የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “በሆርሙዝ ወሽመጥ ደቡባዊ ክፍል በኩል ለማለፍ የሞከረ ሕገ ወጥ ነዳጅ ጫኝ መርከብ” ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    መርከቡ “በሁለት የተጠመዱ የባሕር ፈንጂዎች በመመታቱ በእሳት እንደተያያዘ እና ሙሉ በመሉ እንደቆመ” ገልጿል። በወሽመጡ ላይ የተጣለውን “የደኅንነት መመሪያ የሚጥሱ መርከቦች ዕጣ ከዚህ ያነሰ እንደማይሆንም” አስጠንቅቋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ግጭት ማገርሸቱ እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚታየው ሁኔታ፣ የባሕር መስመሩን ለማስከፈት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አካላትን ስጋት ላይ ጥሏል።

  2. በኔፓል የጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ከ900 በላይ ሲደርስ፤ 4,200 በላይ ጠፍተዋል

    ልጇ በአደጋ የሞተባት እናት ስታለቅስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በአደጋው የሞቱ ሰዎች እና የጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

    ባለፈው ሳምንት ኔፓል እና በቲቤት ድንበር ላይ በተከሰተው ድንገተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ እና የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

    አደጋው ከደረሰ ከስድስት ቀናት በኋላ የሚካሄደው ሰዎችን የመፈለግ ጥረት የቀጠለ ሲሆን፣ በተለይ የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    በተራራማ አካባቢው በተከሰተው በዚህ ከባድ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ150 ተነስቶ ትናንት እሁድ 781 ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ሰኞ ደግሞ ወደ 903 ተሻግሯል።

    የኔፓል ብሔራዊ የአደጋ መከላከል እና አስተዳደር ባለሥልጣን ትናንት እሁድ ባወጣው መረጃ የጠፉ ሰዎች ቁጥር 2,502 እንደሆነ አስታውቆ ነበር። ዛሬ ሰኞ ጠዋት ግን አሃዙ ወደ 4,247 ከፍ ብሏል።

    በዚህም ምክንያት አደጋው ከደረሰ ከስድስት ቀናት በኋላ የጠፉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የሞቱ ሰዎች ብዛት በቀጣይ ቀናት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

    በአደጋው የተለያዩ አገራት ዜጎች እና በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል ወይም እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።

    በዚህም መሠረት የደረሱበት ሳይታወቅ እየተፈለጉ ካሉት መካከል 3,655 ኔፓልያውያን እና 592 የውጭ አገራት ዜጎች ይገኙበታል።

    እንዲሁም 933 በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ማዕከል ውስጥ ሥራ ላይ የነበሩ እና 102 የኔፓል መንግሥት ፖሊሶች፣ ወታደሮች እና የጉምሩክ መኮንኖችም ከጠፉት መካከል ናቸው።

    የጠፉትን ሰዎች የማፈላለጉ ሥራ በቀጠለበት ጊዜ፣ በየዕለቱ የበርካታ ሰዎች አስከሬኖች እየተገኘ መሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አመልክቷል።

    በአደጋው የሞቱት እና የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች አብዛኞቹ ከኔፓል ሲሆን ከአጎራባቿ ቲቤትም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በቲቤት እስካሁንም 16 ሰዎች መሞታቸውን ሲረጋገጥ 546 ሰዎች ደግሞ መጥፋታቸውን የቻይና መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  3. ኢራን በአረብ ኤምሬት ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገለጸች

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

    ዳግም ባገረሸው የኢራን እና የአሜሪካ ግጭት የኢራን ጦር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ የሚገኝን የአሜሪካ ጦር ሰፈር ማጥቃቱን አስታወቀ።

    ሠራዊቱ እንዳለው አል-ማንሃድ በተባለው “የአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች እና ሠራዊት ጦር ሰፈር” ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።

    የኢራን ጦር ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንዳስታወቀው ጥቃቱ የተፈጸመው እሁድ ምሽት አሜሪካ በኢራኗ ላርክ ደሴት ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋ ነው።

    እሁድ ሌሊት የአሜሪካ ኃይሎች ላርክ ደሴት ላይ የሚገኙ ሁለት የኢራን ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን ዒላማ አድርገው ጥቃት ፈጽመው ነበር።

    በምላሹም ዮርዳኖስ ውስጥ ሁለት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ በማድረግ በሚሳዔል እና በድሮኖች ጥቃት መፈጸሙን የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስታውቋል።

    በአሜሪካ ጥቃት የተፈጸመበት የኢራን ደሴት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ከሚገኙ የኢራን ነዳጅ ወደ ውጭ ከሚላክባቸው ስፍራዎች ዋነኛው እና ወሳኙ ነው።

    አብዛኛው የኢራን ነዳጅ ወደ ውጪ የሚላከውም በደሴቱ ላይ ከሚገኙ የነዳጅ ማስተላለፊያ ማዕከላት ነው።

  4. አሜሪካ በሳምንታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢራን ላይ ጥቃት ስትፈጽም፤ ቴህራን የአጸፋ እርምጃ ወሰደች

    ባሕር ላይ የሚጓዙ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ጦር ከሐምሌ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢራን በፈጸመው ጥቃት ላራክ ደሴት ላይ የሚገኙ ማስወንጨፊያዎችን መምታቱን አንድ የዋሽንግተን ባለሥልጣን ተናገሩ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ቲም ሃውኪንስ “የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኃይሎች የባህር ውስጥ ፈንጂዎችን የያዙ ሮኬቶችን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመተኮስ ሲዘጋጁ ታይተዋል” ሲሉ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እሁድ ምሽት በተፈጸመው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። ለዚህ ጥቃት “ምላሽ እና ቅጣት” እንደሚሰጥም ዝቷል።

    አብዮታዊ ዘቡ ቆየት ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ በዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እንደገለጸ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ቢቢሲ ስለ ጥቃቱ አስተያየት ለማግኘት ለአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ጥያቄ አቅርቧል።

    የዮርዳኖስ ጦር ከአብዮታዊ ዘቡ መግለጫ ከአጭር ጊዜ በኋላ በሰጠው ገለጻ፣ ወደ አገሪቱ የተወነጨፉ ስምንት ሚሳዔሎችን ማክሸፉን አስታውቋል።

    የዮርዳኖስ ጦር በመግለጫው “ዛሬ ሰኞ ንጋት ላይ የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሰው የገቡ ስምንት ሚሳዔሎች በአየር መከላከያ ስርዓቶች ተጠልፈዋል” ማለቱን ‘ፔትራ' የተሰኘው የመንግሥት ዜና ወኪል ዘግቧል፥።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም አስጀምረውት የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ ሐምሌ ላይ ካስቆሙ ወዲህ በሚታወቅ ደረጃ ኢራን ላይ ጥቃት ሲፈጸም የትናንት ምሽቱ የመጀመሪያው ነው።

    ላራክ ደሴት ቁልፍ ወደብ ከሆነው ‘ባንዳር አባስ’ ፊት ለፊት የሚገኝ ደሴት ነው። ስፍራው ለዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ ወሳኝ በሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ይገኛል።

    በአሁኑ ሰዓት ኢራን በወሽመጡ እንዲያልፉ የምትፈቅድላቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ለፍተሻ በዚህ ደሴት በኩል እንዲጓዙ ታደርጋለች። መርከቦቹ ወሽመጡን ለማለፍ 2 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ እያስገደደች መሆኑም ተዘግቧል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ ሆሴን ሞሄቢ ጥቃቱን “በትራምፕ አገዛዝ የተፈጸመ ስልታዊ እና ገዳይ ስህተት” ሲሉ ጠርተውታል። “ጠላት በኢኮኖሚያዊም ሆነ በወታደራዊ መስኮች የዚህን የተሳሳተ ስሌት መዘዝ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉም ተናግረዋል።

    ደሴቱ ላይ የተካሄደው ጥቃት የተፈጸመው በድሮን መሆኑን ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቀጥሎ ባወጣው መግለጫ፣ በላራክ ደሴት ለደረሰው ምት በተወሰደ የአጸፋ እርምጃ፣ በዮርዳኖስ በሚገኙት ‘ኪንግ ሁሴን’ እና ‘አል አዝራቅ’ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    በዚህ ጥቃት “ከፍተኛ ጉዳት” ማድረሱን እና “ቴክኒካዊ መሠረተ ልማቶች፣ የጥገና ተቋማት እና የጠላት ተዋጊ ጄቶች የሚገኙባቸው ስፍራዎችን” ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት ኢራን ላይ በፈጸሙት ጥቃት የተጀመረው ይህ ጦርነት አድማሱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አስፍቷል።

    ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ እስራኤልን፣ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን እንዲሁም በባሕረ ሰላጤው የሚገኑ የአጋር አገራትን መትታለች። የሆርሙዝ ወሽመጥም ለመርከብ ጉዞ ዝግ ሆኗል። ጦርነቱ አሁን ስድስተኛ ወሩን አልፏል።