በኔፓል የጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ከ900 በላይ ሲደርስ፤ 4,200 በላይ ጠፍተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት ኔፓል እና በቲቤት ድንበር ላይ በተከሰተው ድንገተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ እና የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
አደጋው ከደረሰ ከስድስት ቀናት በኋላ የሚካሄደው ሰዎችን የመፈለግ ጥረት የቀጠለ ሲሆን፣ በተለይ የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በተራራማ አካባቢው በተከሰተው በዚህ ከባድ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ150 ተነስቶ ትናንት እሁድ 781 ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ሰኞ ደግሞ ወደ 903 ተሻግሯል።
የኔፓል ብሔራዊ የአደጋ መከላከል እና አስተዳደር ባለሥልጣን ትናንት እሁድ ባወጣው መረጃ የጠፉ ሰዎች ቁጥር 2,502 እንደሆነ አስታውቆ ነበር። ዛሬ ሰኞ ጠዋት ግን አሃዙ ወደ 4,247 ከፍ ብሏል።
በዚህም ምክንያት አደጋው ከደረሰ ከስድስት ቀናት በኋላ የጠፉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የሞቱ ሰዎች ብዛት በቀጣይ ቀናት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
በአደጋው የተለያዩ አገራት ዜጎች እና በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል ወይም እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።
በዚህም መሠረት የደረሱበት ሳይታወቅ እየተፈለጉ ካሉት መካከል 3,655 ኔፓልያውያን እና 592 የውጭ አገራት ዜጎች ይገኙበታል።
እንዲሁም 933 በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ማዕከል ውስጥ ሥራ ላይ የነበሩ እና 102 የኔፓል መንግሥት ፖሊሶች፣ ወታደሮች እና የጉምሩክ መኮንኖችም ከጠፉት መካከል ናቸው።
የጠፉትን ሰዎች የማፈላለጉ ሥራ በቀጠለበት ጊዜ፣ በየዕለቱ የበርካታ ሰዎች አስከሬኖች እየተገኘ መሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አመልክቷል።
በአደጋው የሞቱት እና የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች አብዛኞቹ ከኔፓል ሲሆን ከአጎራባቿ ቲቤትም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በቲቤት እስካሁንም 16 ሰዎች መሞታቸውን ሲረጋገጥ 546 ሰዎች ደግሞ መጥፋታቸውን የቻይና መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።


