ቀጥታ, በኢራን ጦርነት 18 የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸው እና ከ600 በላይ መቁሰላቸው ተገለጸ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ካዘዙበት ያለፈው የካቲት ወዲህ 18 የአሜሪካ ወደታሮች መገደላቸውን እና ቢያንስ 624 መቁሰላቸውን ከአገሪቱ መከላከያ መሥሪያ ቤት 'ፔንታገን' የወጣ መረጃ አመለከተ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢራን ጦርነት 18 የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸው እና ከ600 በላይ መቁሰላቸው ተገለጸ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ካዘዙበት ያለፈው የካቲት ወዲህ 18 የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውን እና ቢያንስ 624 ደግሞ መቁሰላቸውን ከአገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት 'ፔንታገን' የወጣ መረጃ አመለከተ።

    ጉዳቱ ከደረሰባቸው መካከል 417 በኢራን ላይ ከተካሄደው 'ኤፒክ ፊዩሪ’ ከተባለው ዘመቻ ጋር ሲያያዙ፣ 207 ያህሉ ደግሞ ‘በባሕር ማዶ ዘመቻዎች’ ላይ የተሳተፉ እንደሆነ ተጠቅሷል።

    ባለፈው ሳምንት ፔንታገን በጦርነቱ ውስጥ የተገደሉ እና የቆሰሉ ወታደሮችን መረጃ የከለሰ ሲሆን፣ በዚህም በኢራን ጦርነት ከተገደሉ ወታደሮች መካከል የነበሩ አራት አባላቱን ስም በባሕር ማዶ ዘመቻ ላይ ከተገደሉት ዝርዝር ውስጥ አካትቷል።

    የመከላከያ ሚኒስቴሩ የመረጃ ቋት ላይ በኢራን በተካሄደው ዘመቻ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ የተገደሉት 18 እና የቆሰሉ 482 ወታደሮች ዝርዝር ይዞ ቆይቷል። ከዚያ በኋላ ግን በተካሄደው ክለሳ ከሟቾቹ ዝርዝር ላይ አራት ወታደሮች ተቀንሰው ቁጥሩ 14 ሆኗል።

    ምንም ዓይነት ማብራሪያ ሳይሰጥ በቆሰሉት እና በሞቱት ወታደሮች ስም ዝርዝር ላይ የተደረገው ለውጥ፣ 'ግልጽነትን የሚያደናቅፍ ነው' በሚል በቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይል ከፍተኛ መኮንን ሌተናንት ቤን ሆጅስ ትችት ቀርቦበታል።

    የፔንታገን ቃል አቀባይ ሾን ፓርኔል በበኩላቸው በጦር ጉዳተኞች አሃዝ ላይ የተደረገው ለውጥ “ጊዜያዊ የመረጃ መዛባት ነው” ብለዋል።

    “የባሕር ማዶ ዘመቻዎች” የሚለው ዘርፍ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ሲሆን በመከላከያ መስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ የታየው ከእሁድ ጀምሮ መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    በዚህም ክፍል ላይ በቅርቡ ሕይወታቸውን ያጡ አራት ወታደሮችን ስም በሟች እንዲሁም 207 ደግሞ በቆሰሉ መዝግቧል። ነገር ግን የቆሰሉት ወታደሮች በኢራኑ ጦርነት የተጎዱ ስለመሆናቸው ግልጽ አይደለም።

    አራቱ ወታደሮች የተገደሉት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው ተኩስ አቁም ከፈረሰ በኋላ ነው። በድጋሚ በአሜሪካ ጥቃት የተፈጸመባት ኢራን በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ዒላማ አድርጋለች።

    ኢራን ከአስር ቀናት በፊት ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ባደረሰችው የሚሳዔል ጥቃት ሦስት ወታደሮች ተገድለዋል። አንዱ ደግሞ ኢራቅ ውስጥ የኢራን ድሮንን ለማክሸፍ በተወሰደ እርምጃ ወቅት ነበር የተገደለው።

    አሜሪካ ለ13 ተከታታይ ቀናት በኢራን ላይ ጥቃት ስትፈጽም ኢራንም በምላሹ በቀጣናው ባሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት አድርሳለች።

    ከአርብ ጀምሮ ባለፉት ሦስት ቀናት የአሜሪካ ጥቃት መቆሙን ተከትሎ ኢራንም የአጸፋ እርምጃዋን ጋብ አድርጋለች።

  2. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም በቁጥጥሯ ስር መሆኑን አስታወቀች

    ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ጦርነት ጋብ ማለቱን ተከትሎ ኢራን ወሳኝ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሯ ስር መሆኑን እንዲሁም የተቋረጠው የሰላም ንግግር እንዲጀመር አለመጠየቋን አስታወቀች።

    አሜሪካ ለ13 ተከታታይ ቀናት በኢራን ላይ ጥቃቶችን በፈጸመችበት ወቅት፤ ቴህራንም በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚሳዔል እና ድሮን ዒላማ ስታደረግ ቆይታለች።

    ትራምፕ ለሁለት ሳምንት ገደማ የቆየውን የአየር ጥቃት ያቆሙት፣ ዘመቻው ኢራን በሆርሙዝ ላይ ያላትን ቁጥጥር ለመስበር የወጠነውን ግብ እንዳላሳካ በአማካሪዎቻቸው ከተገለጸላቸው በኋላ መሆኑ ተዘግቧል።

    አሜሪካ ጥቃቱን እስካቆመች ድረስ፣ ኢራን በበኩሏ የምትወስደውን እርምጃ እንደምትገታ አስታውቃለች።

    አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደገለጹት የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዦች ዘመቻው ዓላማውን እየሳተ ነው በማለት ፕሬዝዳንቱን መክረዋቸዋል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት ጄነራል ዳን ኬይን በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የመሳሪያ ክምችታቸው እየተመናነመነ መሆኑን መናገራቸውን አመልክተዋል።

    የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲቪል እና ወታደራዊ አማካሪዎች በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ምክር መስጠታቸውን ዘግበዋል።

    በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልትዝ በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የቆመው ለድርድር በር ለመክፈት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ከአሜሪካ ጋር የሚካሄደው የሰላም ንግግር መልሶ እንዲጀመር ጥያቄ እንዳላቀረበች አሳውቋል። የአሜሪካ ጥቃት አለመሳካቱን እና ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሯ ስር መሆኑን ኢራን አስታውቃለች።

    አሜሪካ ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ በኢራን ላይ ባካሄደችው ጥቃት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር። ባለፉት ቀናት ጥቃቱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ደግሞ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱ ተዘግቧል።

  3. ከሁቲዎች ጥቃት በኋላ በቀይ ባሕር የሚደረግ የመርከቦች ጉዞ መቀዛቀዙ ተዘገበ

    የየመን ሁቲዎች በቀይ ባሕር ዳርቻ በሚገኝ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት ከፈጸሙት በኋላ፣ በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የመርከብ ጉዞ መቀዛቀዙን ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ‘ኬፕለር’ የተሰኘውን የመረጃ ምንጭ ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው እሁድ ዕለት በባብ ኤል መንደብ በኩል ያለፉ የንግድ መርከቦች 11 ናቸው። ካለፉት ወራት ጋር ሲነጻጸር ይህ ቁጥር ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

    በወሽመጡ በኩል ከተለላፉ መርከቦች ውስጥ ሰባቱ ነዳጅ ጫኝ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከልም ሦስቱ ወደ ቀይ ባሕር መግባታቸውም ዘገባው ጠቅሷል።

    የሳዑዲ አረቢያን የኤክስፖርት ምርት ጉዞ ማስተጓጎል የሚፈልጉት ሁቲዎች፤ ባለፈው ሳምንት የባሕር ጉዞ ማዕቀብ” መጣላቸውን ገልጸው ነበር። ቀጥሎም ይህንን እገዳ ጥሰዋል የተባሉ ሁለት የአገሪቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መትተዋል።

    በተጨማሪም በሳዑዲ አረቢያ በጂዛን ከተማ የሚሳዔል ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጸዋል። ሳዑዲም በወሰደችው የአጸፋ ምላሽ በየመን የወደብ ከተማ ሆዴይዳ እና በቅርብ ያለ ደሴት ላይ የሚገኙ የታጣቂ ቡድኑ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

    እነዚህ ጥቃቶች በቀይ ባሕር የሚደረግ ጉዞ ላይ መስተጓጎል ፈጥረዋል። የቀይ ባሕር መስመር በአሜሪካ እና በኢራን ጦርነት ምክንያት ሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ችግር ውስጥ ለገባው የነዳጅ ምርት ጉዞ መተንፈሻ ሆኖ ነበር።

  4. የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እና የኒው ዮርክ ከንቲባ ማምዳኒ ውዝግብ

    በኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ የእስራ ዛቻ የደረሰባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ ጷጉሜን ላይ በከተማዋ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚገኙ አስታወቁ።

    የኒው ዮርክ ከንቲባ ማንዳኒ፣ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ኔታንያሁ ላይ ያወጣውን የእስር ማዘዣ ለማስፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደሚያስሩ ተናግረው ነበር። ባለፈው ሳምንት ላይ ግን እስሩን ለመፈጸም የሚያስችል ሕጋዊ ሥልጣን እንደሌላቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።

    ሰኞ ዕለት ለሌላ ጉብኝት ወደ አሜሪካ የተጓዙት የእስራኤሉ መሪ እሁድ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ማምዳኒ እንደሚያስሯቸው መግለጻቸው እንደማያሳስባቸው ተናግረዋል። አክለውም የኒው ዮርኩን ከንቲባ “ጥላቻ በመቀስቀስ” ወንጅለዋል።

    ኔታንያኑ ነገ ማክሰⶉ በዋይት ሐውስ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚገናኙ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ሕይወታቸው ባለፈው የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ሊንዚ ግርሃም የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይም ይገኛሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ላይ ኒው ዮርክ ከተማ አልተካተተችም።

    ኔታንያሁ በቃለ መጠይቁ፣ ማንዳኒ “ጥላቻ እየቀሰቀሰ ነው። የአይሁዶች፣ የክርስቲያኖች፣ የሙስሊሞች፣ የሁሉም ኒው ዮርከሮች ከንቲባ ሊሆን ይገባው ነበር” ብለዋል።

    “ነገር ግን አንድ ቡድንን በሌላው ላይ ለማስነሳት እየሞከረ ነው። አሜሪካውያን አይሁዶችን አነጋግሬያለሁ፤ በአሁኑ ሰዓት ፍራቻ ውስጥ ናቸው” ሲሉም ከስሰዋል።

    ለፍልስጤም መብቶች ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው ከንቲባ ማምዳኒ፤ የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ የሚያካሂደው ዘመቻ ላይ ያሰሙት ተቃውሞ ባለፈው ዓመት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ዋነኛ የክርክር ርዕስ ነበር።

    ማምዳኒ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር ኔታንያሁን ‘የጦር ወንጀለኛ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

    ከንቲባ ለመሆን የምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉበት ወቅትም ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዛ ውስጥ ፈጽመውታል ባለው የጦር ወንጀል ምክንያት ያወጣውን የእስር ማዘዣ እንደሚያስፈጽሙ ገልጸው ነበር።

    እስራኤል ጋዛ ውስጥ የጦር ወጅንል ተፈጽሟል የሚለውን ክስ አትቀበለውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኔታንያሁም የቀረቡባቸውን ክሶች “ሐሰተኛ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

  5. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እያደረገች አለመሆኑን አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር መልዕክቶችን መለዋወጧን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት መደበኛ የሆነ ድርድር እየተደረገ አለመሆኑን ገለጹ።

    ኢስማኤል ባጋይ ቴህራን አሁን ቅድሚያ የምትሰጠው ሉዓላዊነቷን መከላከል፣ የግዛት አንድነቷን ማስጠበቅ እና ለሕዝቧ መብት መሆኑን ገልጸው ወደ ድርድር ፈጥነው እንደማይገቡ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ዋሺንግተን ዲፕሎማሲን በወታደራዊ እርምጃ ውድቅ ታደርጋለች ሲሉ የኮነኑ ሲሆን አሜሪካ ወደ ድርድር ለመመለስ ያለውን ሁኔታ አበላሽታዋለች ብለዋል።

    ባጋይ ከአውስትራሊያው ኦአርኤፍ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “መልዕክቶችን እየተለዋወጥን ነው፤ ነገር ግን አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ለኢራን ሉዓላዊነት፣ ለግዛት አንድነት እና ለሕዝቧ መብት መከበር ነው” ብለዋል።

    የቃል አቀባዩ አስተያየት ምንም እንኳ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል መደበኛ ድርድር ባይጀመርም ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እየተካሄደ መሆኑን ይጠቁማል።

    ከዚህ ቀደም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች ፓኪስታን እና ኳታር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የመልዕክት ልውውጥ በማቀላጠፍ ረገድ ሚና ነበራቸው።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አስተያየት የተሰማው አሜሪካ ለሁለት ሳምንት ስታካሄድ የነበረውን ጥቃት ማቆሟን ከገለጸች በኋላ ነው።

    የጥቃቶቹ መቆም ዳግም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊጀመር ይችላል የሚል ተስፋ አጭሯል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት አስተጓጉሏል።

  6. አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ማቆሟን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳየ

    የአሜሪካ እና የኢራን ግጭት ለሁለት ሳምንት ያህል ከቀጠለ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መቆሙን ተከትሎ ሰኞ ዕለት የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ በ6 በመቶ ቅናሽ አሳየ።

    አሜሪካ ለተከታታይ ሁለት ሳምንት በኢራን ላይ የፈጸመችውን ድብደባ ካቆመች በኋላ ኢራን የአጸፋ ምላሽ እንደማትሰጥ በመግለጿ ግጭቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊገኝ እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት ይችላል የሚል ተስፋ አጭሯል።

    የዓለም ነዳጅ ዋጋ ተመን የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ6.4 በመቶ ወርዶ በበርሜል 90.58 ዶላር እየተሸጠ ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና ግጭቱ ወደ ቀይ ባሕርም በመስፋፋቱ የብሬንት ዋጋ ባለፈው ሳምንት በበርሜል 100 ዶላር ደርሶ ነበር።

    በየመን የሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎች የሳዑዲ አረቢያ መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ባለፈው ሳምንት እገዳ ጥለዋል።

    ይህም የዓለም ከፍተኛ ነዳጅ ላኪ የሆነችው አገር ምርቷን ለውጭው ዓለም ገበያ እንዳታቀርብ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሯል።

    በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልዝ ለፎክስ ኒውስ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የገቱት ለዲፕሎማሲ ጥረት ዕድል ለመስጠት ነው ብለዋል።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመት ዝግ እንደሆነ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

    የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማችን ካስታወቁ በኋላም በባብ ኤል መንደብ በኩል የመርከቦች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል።

  7. አዲሱ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩክሬንን መደገፍ እንደሚቀጥሉ ተናገሩ

    አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሀም ለዩክሬን የሚያደርጉትን “ጽኑ ድጋፍ” ለመቀጠል ቃል ገቡ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ዛሬ ሰኞ ውይይት ያደርጋሉ።

    ከውይይቱ አስቀድመው እንደተናገሩትም ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከተረከቡ አንድ ሳምንታቸው ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጎብኚያቸው ዜሌንስኪ ይሆናሉ።

    ውይይቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት “እንደሚያጠናክር” ተገልጿል። መሪዎቹ የባሕር ኃይል ይጎበኛሉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንግሊዝ ከዩክሬን ጎን ትቆማለች፤ ድጋፋችን አይቋረጥም። ለዩክሬንን ዘላቂ ሰላም እና ፍትሕ ሳናሰፍን ወደኋላ አንልም” ብለዋል።

  8. ኔታንያሁ የኒው ዮርክ ከንቲባን “ጥላቻን በማነሳሳት” ወነጀሉ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኒው ዮርክ ከንቲባ በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው ቢዝቱም በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ለመታደም ማቀዳቸውን ተናገሩ።

    የኒው ዮርክ ከንቲባ የሆኑት ዞህራን ማምዳኒ ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ያወጣውን የእስር ማዘዣ ለማስፈጸም ተናግረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ የሕግ ድጋፍ እንደሌላቸው በመግለጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፎክስ ኒውስ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ማምዳኒ ቀደም ሲሉ በሰጡት አስተያየት “ስጋት እንደማይገባቸው”ተናግረው ከንቲባው “ጥላቻን ያነሳሳሉ” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

    ኔታንያሁ “እርሱ የሁሉም የኒውዮርክ ነዋሪዎች፣ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች ከንቲባ መሆን አለበት፤ ነገር ግን አንዱን ቡድን በሌላኛው ላይ ለማነሳሳት እየሞከረ ነው” ሲሉተናግረዋል።

    ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት በኒው ዮርክ የተፈፀመውን ሁለት የስለት ጥቃት ጠቅሰዋል፤ በዚህ ጥቃት አንድ ተጠርጣሪ አንድ አይሁዳዊ እና አንድ እስያዊን ወግቷል።

    ፖሊሶች ተጠርጣሪው በስለት ጥቃት ሲያደርስ "አላህ አክበር" እያለ ይጮህ ነበር። ከእያንዳንዱ ተጎጂ ጋር በተያያዘ በጥላቻ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።

    ሁለቱም ሰዎች ከጥቃቶቹ የተረፉ ሲሆን ይህም ከከተማዋ የአይሁድ እና የእስያ አሜሪካውያን መሪዎች ውግዘት አስከትሏል።

    ከዚያ በኋላ ኔታንያሁ በሰጡት ቃለ ምልልስ በኒው ዮርክ የሚኖሩ አይሁዶች "ፈርተዋል" ብለዋል።

  9. የኢራን ሕግ አውጪዎች ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዛቱ

    ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ እየቀዘፈ የነበረ የኢራን የንግድ መርከብ ላይ የድሮን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ አንድ ከፍተኛ የኢራን ሕግ አውጪ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠነቀቁ።

    በኢራን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የአጻፋ ምላሽ አለው ያሉት የሕግ አውጪው ይህንን አሜሪካ እና እስራኤል ያውቃሉ ብለዋል።

    የኢራን ፓርላማ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ኮሚሽን ሰብሳቢ የሆኑት ኢብራሂም አዚዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት አሜሪካ እና እስራኤል “ማንኛውም በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምንጊዜም ዋጋ እንደሚያስከፍል ያውቃሉ። ይህ ደግሞ ዛሬም እውነት ነው” ብለዋል።

    አክለውም “ዩክሬን በቅርቡ ኢራን ድርጊቱ ምላሽ ሳያገኝ እንደማትተወው ትማራለች” ብለዋል።

    አዚዝ “አሳንሰው የሚገምቱን ዝርዝር እየጨመረ ነው የመጣው” ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ዩክሬን በኢራን የንግድ መርከብ ላይ የፈጸመችው ጥቃት የመንግሥታቱን ድርጅት ቻርተር የጣሰ መሆኑን ተናግረዋል።

    አክለውም በጥቃቱ አንድ ባህረተኛ መገደሉን አሳውቀው “ምላሽ ሳይሰጠው አይቀርም” ብለዋል።

    የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ አገራቸው በካስፒያን ባሕር ላይ ረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ “ጠንካራ ውጤቶችን” ማግኘቷን አስታውቀዋል።

    አክለውም ጥቃቱ የተፈጸመው “ኢራን በተሳተፈችበት ወታደራዊ ጭነት በጫነች መርከብ ላይ” መሆኑን ተናግረዋል።

  10. የአሜሪካ አምባሳደር ትራምፕ ጥቃቱን ያስቆሙት ለንግግር ቦታ ለመስጠት ነው አሉ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ የሚፈጸመውን ድብደባ እንዲቆም ያደረጉት ለዲፕሎማሲ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት መሆኑን በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር አስታወቁ።

    አምባሳደር ማይክ ዋልዝ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፕሬዚዳንቱ “ለንግግር የተወሰነ ቦታ ለመስጠት” ጥቃተ እንዲቆም ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

    የኢራን ጦር ቃል አቀባይ እሁድ ዕለት ቴህራን በቀጣናው ላይ የምትፈጽመውን “የአጸፋ” ጥቃቶች ማቆሟን ተናግረዋል።

    በዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን መካከል በሰኔ ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ከፈረሰ በኋላ የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ሳምንቶች በየዕለቱ ኢራን ላይ ድብደባ ሲፈጽም ቆይቷል።

    ቴህራንም በምላሹ በጎረቤት አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን ስታስወነጭፍ ቆይታለች።

    አምባሳደሩ ትራምፕ ጥቃቱ እንዲቆም ያደረጉት ለአጭር ጊዜ ስለመሆኑ kኤንቢሲ ተጠይቀው ሲመልሱ “ለአሁኑ እዚያ ድረስ ሄጄ መመለስ አልፈልግም። ፕሬዚዳንቱ ሁሉንም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠዋል” ብለዋል።

    ኒውዮርክ ታይምስ የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ጥቃቶች እየሰፉ የሚመጡ ከሆነ የአየር መከላከያ ጦር መሣሪያዎች እየሳሱ ይመጣሉ ማለታቸውን መዘገቡን በተመለከተ ዋልዝ ሲጠየቁ አጣጥለውታል።

    “የአሜሪካ ጦር . . . ዘመቻውን በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስፈልጉት ሁሉም ነገሮች አሉት” ብለዋል።

    እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ትራምፕ ጥቃቱ ስለመቆሙ በይፋ ያሉት ነገር የለም።

    ነገር ግን ቀደም ሲል በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች የኢራንን መርከቦች እና የኻርግ ደሴቶችን ሲደበድቡ የሚያሳይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሰራ ምስል አጋርተው ነበር።