ቀጥታ, የኢራኑ ጠቅላይ መሪ በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየም ከአገራቸው እንዳይወጣ ወሰኑ

ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የቀረበላትን በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየምን ወደ ውጭ ለመላክ የቀረበውን ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ መወሰኗን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ። ሮይተርስ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየም ከአገር እንዳይወጣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ ኩባን ‘ማስፈራራት’ እንድታቆም ቻይና አሳሰበች

    የቀድሞ የኩባ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ የኩባ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ

    አሜሪካ ኩባን “ማስፈራራት” እንዲሁም “ጫና ለማሳደር መሞከር” እንድታቆም ቻይና አሳሰበች።

    የአሜሪካ ፍርድ ቤት የ94 ዓመቱ የቀድሞ የኩባ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ ላይ ክስ መመሥረቱን ተከትሎ ነው ቻይና ማሳሰቢያ የሰጠችው።

    ከ30 ዓመት በፊት በኩባ እና በፍሎሪዳ መካከል ተመትተው ከወደቁ ሁለት አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ የቀድሞው የኩባ መሪ ላይ የተመሠረተው ክስ የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል ማሴር እና ሌሎችንም የያዘ ነው።

    አራት ሰዎች የሞቱበት ክስተት የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሻክሯል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኩባን ኮሚኒስት መንግሥት መገርሰስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጋዎ ጂያኩን “አሜሪካ በየአጋጣሚው ኩባን ማስፈራራት ማቆም አለባት” ብለዋል።

    ቻይና “በጽኑ ኩባን ትደግፋለች። በውጭ ኃይሎች በማንኛውም አውድ ኩባ ላይ የሚደርስ ጫናን ቤይጂንግ ትቃወማለች” ሲሉም ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ “አሜሪካ ማዕቀብ እና የሕግ መዋቅርን በመጠቀም ኩባን ማስፈራራት እና ጫና ማሳደር ማቆም አለባት” በማለትም አክለዋል።

    የኩባን ሉዓላዊነት እና ክብር ቻይና እንደምትደግፍ እንዲሁም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንደምትቃወም ገልጸዋል።

  2. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየም ከአገራቸው እንዳይወጣ ወሰኑ

    የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim News Agency

    ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የቀረበላትን በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየምን ወደ ውጭ ለመላክ የቀረበውን ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ መወሰኗን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሮይተርስ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በከፍተኛ ሁኔታ የተብላላ ዩራንየም ከአገር እንዳይወጣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

    አሜሪካ ለሰላም ድርድር ካቀረበቻቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ይሄው ጉዳይ ነው።

    የጠቅላይ መሪው ውሳኔ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስተዳደር ሊያስቆጣ እና የድርድር ሒደቱን ሊያወሳስብ ይችላል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው የእስራኤል ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ ኢራን ያከማቸችው የተብላላ ዩራንየም ከአገሪቱ እንደሚወጣ ለእስራኤል ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

    የሰላም ስምምነት ላይ ኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመሥራት ነጥብ ላይ የደረሰው የተብላላ ዩራንየም ከኢራን እንደሚወጣ መናገራቸው ተገልጿል።

    ስለ ጉዳዩ የኢራን መገናኛ ብዙኃን እስካሁን ድረስ ዘገባ አላወጡም።

    ኢራን ከአሜሪካ እና ከሌሎች ምዕራባውያን ጋር ለዘመናት ሲያወዛግብ የቆየው የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ሙሉ ለሙሉ እንድታቆም እና ከጥቅም ውጪ እንድታደርግ የቀረበላትን ጥያቄ ባለመቀበሏ ነው።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባትን ጦርነት ለማቆም ከቀረበላት ቅድመ ሁኔታ መካከልም እንዱ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ቢሆንም፤ ኢራን አልተቀበለችውም።

  3. ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኢቦላ ቫይረስ መቀስቀስ ምክንያት የዓለም ዋንጫ ልምምድን አቋረጠች

    የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እ.አ.አ ከ1974 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፊፋ ዓለም ዋንጫ አልፋለች

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን ኢቦላ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ሊካሄድ የነበረን የዓለም ዋንጫ ቅድመ ልምምድ መሰረዟን አስታወቀች።

    ከ130 በላይ ሰዎችን ስለመግደሉ የተነገረለት በሽታ ማገርሸቱን ተከትሎ ዝግጅቶች ወደ ቤልጂየም መዘዋወራቸው ታውቋል።

    የዓለም የጤና ድርጅት ኢቦላን “የኅብረተሰብ ጤና ስጋት” ሲል መድቦታል።

    አገሪቱ እ.አ.አ ከ1974 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ እየተዘጋጀች ሲሆን፤ ቀድመው የተያዙ የሙከራ ጨዋታዎች በአውሮፓ እንደሚካሄዱ የብሔራዊ ቡድኑ ቃል አቀባይ ጄሪ ካሊሞ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከዴንማርክ፣ ቤልጂየም፣ ችሊ እና ስፔን ጋር ትጫወታለች።

    ቃል አቀባዩ እንዳሉት ልምምዱ የተሰረዘው ከሜክሲኮ እና ከካናዳ ጋር የዓለም ዋንጫን የምታዘጋጀው አሜሪካ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ የጉዞ እግድ በመጣሏ ነው።

    ዋሽንግተን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ በሦስት አገራት ባለፉት 21 ቀናት ጉዞ ያደረጉ እና አሜሪካዊ ያልሆኑ መንገደኞች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ክልከላ ጥላለች።

    ሁሉም የአገሪቱ ተጨዋቾች እና ፈረንሳዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ሰባስቲያን ድሳብሬ መቀመጫቸው ከማዕከላዊ አፍሪካዊት አገር ውጭ በመሆኑ እና ልምምድ በመሰረዙ እግዱ ተፅዕኖ አያሳድርባቸውም።

  4. ኢራን ከታሰበው በበለጠ ፍጥነት የወታደራዊ ኢንዱስትሪዋን መልሳ እየገነባች መሆኑን ሲኤንኤን ዘገበ

    የኢራን ወታደር

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

    አሜሪካ እና እስራኤል በከፈቱት ጥቃት ወታደራዊ አቅሟ የተመታባት ኢራን፤ የተኩስ አቁም ከተደረገ ወዲህ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዋን በፍጥነት እየገነባች እንዲሁም የተወሰኑ ድሮኖችን እያመረተች መሆኑን ሲኤንኤን የአሜሪካ የስለላ መረጃን ጠቅሶ ዘገበ።

    የአሜሪካው ቴሌቪዥን ጣቢያ ያነጋገራቸው አራት ምንጮች እንደገለጹት የኢራን ጦር መጀመሪያ ላይ ሲጠበቅ ከነበረው ፍጥነት በበለጠ ሁኔታ አቅሙን እያጠናከረ መሆኑን የዋሽንግተን የስለላ መረጃ አመልክቷል።

    በአሁኑ ጦርነት ጥቃት የተፈጸመባቸው የሚሳዔል ስፍራዎች፣ ማስወንጨፊያዎች እና የመምረቻ አቅሞች እየተተተኩ መሆኑ፤ ኢራን በቀጣናው ለሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች አሁንም ትልቅ ስጋት መሆኗን ያሳያል ተብሏል።

    እንደ ሲኤንኤን ዘገባ፤ የስለላ መረጃው ስለ ኢራን ጦር እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱ አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት የሠራዊቱ አቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው የሚለውን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።

    የተለያዩ የጦር መሣሪያ ክፍሎችን ማምረት ለመጀመር የሚያስፈልገው ጊዜ የተለያየ ቢሆንም፤ ኢራን በድሮን ጥቃት የመፈጸም አቅሟን በስድስት ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ነበረበት መመለስ እንደምትችል አንድ አሜሪካ ምንጭ መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል።

    ሲኤንኤን ያነጋገራቸው ባለሥልጣን፤ “ኢራናውያን የስለላ ማኅበረሰቡ ለመልሶ ግንባታ ያስቀመጠውን የጊዜ ሰሌዳ በሙሉ አልፈዋል” ማለታቸው ተጠቅሷል።

    ዘገባው እንደሚያመለክተው፤ ኢራን ከታሰበው በበለጠ ፍጥነት መልሳ መገንባት የቻለችው በተለያዩ ምክንያቶች ነው።

    ከሩሲያ እና ቻይና ያገኘችው ድጋፍ እንዲሁም አሜሪካ እና እስራኤል ተስፋ ባደረጉት መጠን ከፍተኛ ጉዳት አለማድረሳቸው በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ አንድ ምንጭ ተናግረዋል ተብሏል።

    አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ካደረጉ ሳምንታት ቢቆጠሩም እስካሁን ድረስ ጦርነቱን በዘላቂነት የሚያስቆም ስምምነት ላይ አልደረሱም። አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የሰላም ስምምነት የማትፈጽም ከሆነ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠንቅቀዋል።

  5. የፓኪስታን ሠራዊት አዛዥ ወደ ኢራን ሊጓዙ ነው

    የፓኪስታን ሠራዊት አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ እና ኢራን ዋና አሸማጋይ የሆነችው ፓኪስታን የሠራዊት አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ዛሬ ወደ ቴህራን እንደሚገቡ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ዘገባዎቹ እንደሚያመለክቱት የወታደራዊ አዛዡ የቴህራን ጉዞ ከዚህ ቀደም ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ሲደረግ ከነበረው ንግግር እና ምክክር የቀጠለ ነው።

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ ሞህሲንም በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ረቡዕ ዕለት ቴህራን መግባታቸውን ‘ኢስና’ የተባለው ኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል። ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እና የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ እስካንዳር ሞሜኒ ጋር ተገናኝተዋል።

    የፓኪስታን እና የኢራን ባለሥልጣናት በንግግራቸው ቀጣናዊ ሁኔታዎችን እንደገመገሙ ዘገባው ጠቅሷል። በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ስላለበት ሁኔታ መነጋገራቸውም ተገልጿል።

    የፓኪስታኒ ሚኒስትር አገራቸው ድርድሩን በተመለከተ ያላትን ምልከታ ለኢራን ባለሥልጣናት እንዳስረዱ ዘገባው አስነብቧል።

    ከፓኪስታኑ ሚኒስትር ጋር የተነጋገሩት የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከዚያ በኋላ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ቴህራንን “በማስገደድ እጅ እንድትሰጥ” ለማድረግ የሚደረግ ጥረት “ቅዠት” ነው ብለዋል።

    “ኢራን ያለማቋረጥ ቃሏን ጠብቃለች፤ ጦርነትን ለመቀልበስም ሁሉንም ጎዳና አስሳለች” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “በእኛ በኩል ሁሉም መንገዶች ክፍት ናቸው” በማለት ጽፈዋል።

    “ኢራንን በማስገደድ እጅ እንድትሰጥ ማድረግ ቅዠት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። በዲፕሎማሲ ውስጥ የጋራ መከበባርን ማምጣት ከጦርነት እጅህ የላቀ ብልህ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው መንገድ ነው” ብለዋል።

  6. የአሜሪካ ጦር የሆርሙዝ እገዳን በመጣስ የተጠረጠረን በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ መርከብ አቅጣጫ ማስቀየሩን አስታወቀ

    የአሜሪካ ወታደሮች መርከቡ ላይ ሲያርፉ

    የፎቶው ባለመብት, U.S. Central Command

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ዋሽንግተን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣለችውን እገዳ ለመጣስ ሞክሯል በሚል የተጠረጠረን በኢራን ባንዲራ የሚንቀሳቀስ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ በቁጥጥር ስር አውሎ አቅጣጫውን ማስቀየሩን አስታወቀ።

    ማዕከላዊ ዕዙ የአሜሪካ ኃይሎች ወደ መርከቡ ላይ ሲወጡ እና በቁጥጥር ስር ሲያውሉት የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አጋርቷል።

    “ኤም/ቲ ሴሌስቲያል ሲ የተባለው እና የኢራን ባንዲራን የሚያውለበልብ ነዳጅ ጫኝ የንግድ መርከብ” በባሕር ኃይሉ ወታደሮች የተያዘው “አሜሪካ የጣለችውን የባሕር ጉዞ እገዳ በመጣስ ወደ ኢራን ወደብ ለመጓዝ በመሞከር ተጠርጥሮ” እንደሆነ ገልጿል።

    “የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡን ከፈተሹ እና የመርከቡ ሠራተኞች የጉዞ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ካደረጉ በኋላ መርከቡን ለቅቀውታል” ብሏል።

    የአሜሪካ ኃይሎች የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ኢራን ወደብ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለውን እገድ “ሙሉ በሙሉ እያስፈጸሙ” መሆኑን የገለጸው ዕዙ፤ “91 የንግድ መርከቦች” ለእርምጃው እንዲገዙ መደረጉን ገልጿል።

    የአሜሪካ ወታደሮች መርከቡ ላይ ሲያርፉ

    የፎቶው ባለመብት, U.S. Central Command

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ወታደሮች መርከቡ ላይ ሲያርፉ
  7. ትራምፕ እና ኔታንያሁ ስለ ኢራን ድርድር አካሄድ “በውጥረት የተሞላ” ንግግር ማድረጋቸው ተዘገበ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቤንጃሚን ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቤንጃሚን ኔታንያሁ የኢራን ጉዳይን በተመለከተ ማክሰኞ ዕለት “ከፍተኛ ውጥረት” የነበረበት እንዲሁም የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር “እጅግ ያበሳጨ” የስልክ ንግግር ማድረጋቸውን የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ዘገበ።

    እንደ አክሲዮስ ዘገባ፤ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተከናወኑ ስላሉ አዲስ ጥረቶች የተነሳበት የሁለቱ መሪዎች ንግግር ረጅም እና “አስቸጋሪ” ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን በመደበኛነት ለማቆም እና በ30 ቀናት ውስጥ ድርድር እንዲካሄድ የሚያስችል “የፍላጎት መግለጫ” በአሸማጋዮች በኩል እየተዘጋጀ መሆኑን ትራምፕ ለእስራኤሉ መሪ ተናግረዋል ተብሏል።

    ዘገባው እንደሚያመለክተው በአንድ ወር ውስጥ የሚደረገው ድርድር እንደ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት ያሉ ጉዳዮች ንግግር እንዲደረግባቸው የሚያስችል ነው።

    ዋሽንግተን እና ቴህራን እዚህ ሰነድ ላይ ፊርማቸው እንደሚያኖሩ የተነገራቸው ኔታንያሁ በአካሄዱ እንዳልተስማሙ ሁለት የእስራኤል ምንጮች ለአክሲዮን ተናግረዋል።

    ስለ ስልክ ንግግሩ ገለጻ የተደረገላቸው የአሜሪካ ምንጭ ደግሞ “ከስልክ ጥሪው በኋላ የቢቢ ጸጉር እሳት ለብሶ ነበር” ሲሉ የኔታንያሁን ስሜት መግለጻቸውን ዘገባው አስነብቧል።

    እንደ አክሲዮስ ዘገባ፤ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያላቸው ኔታንያሁ፤ ጦርነቱ እንዲጀመር እና የኢራን ወታደራዊ አቅም ይበልጥ እንዲዳከም ፍላጎት አላቸው። ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን በመምታት አገዛዙ እንዲዳከምም ይፈልጋሉ ተብሏል።

    ትራምፕ በበኩላቸው ለሚደረገው ንግግር ጥቂት ተጨማሪ ቀናትን ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው። ይሁን እንጂ “ትክክለኛውም ምላሽ ካላገኘን” ጦርነት “በጣም በፍጥነት” ሊጀመር ይችላል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

  8. ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በልጃቸው የሚመራ የፀረ ሙስና ዘመቻ በባለሥልጣናት ላይ ጀመሩ

    ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ልጃቸው ሙሁዚ ካይኔሩጋባ

    የፎቶው ባለመብት, X

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የጦሩ አዛዥ ልጃቸው ሙሁዚ ካይኔሩጋባ

    ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የኡጋንዳ ጦር ሠራዊት አዛዥ በሆነው በልጃቸው የሚመራ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የፀረ ሙስና ዘመቻ መጀመራቸው ተዘገበ።

    በዚህም የተነሳ ካምፓላ የሚገኘው የተሰናባቿ የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ መኖሪያ ቤት በኡጋንዳ የደኅንነት ኃይሎች ተፈትሾ ሮልስ ሮይስ እና ሬንጅ ሮቨርን ጨምሮ ቅንጡ መኪኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።

    የአገሪቱ ጦር አዛዥ እና የፕሬዝዳንቱ ልጅ የሆኑት ሙሁዚ ካይኔሩጋባ አባታቸው ኡጋንዳ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ሰው በቁጥጥር ስር የማዋል ሥልጣን እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

    የፀረ ሙስና ዘመቻው ለአራት አስርት ዓመታት ኡጋንዳን እየመሩ ባሉት በፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ትዕዛዝ የሚካሄድ ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።

    ቤታቸው የተፈተሸው አፈ ጉባዔዋ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው ተደርገው ይታዩ የነበረ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ስማቸው ከሙስና ጋር ሲነሳ ቆይቷል። በዚህም በብሪታኒያ እና በአሜሪካ ማዕቀቦች ተጥሎባቸዋል።

    አሁን ከባለሥልጣኗ ቤት የተያዙት ውድ ንብረቶች በጨረታ ተሽጠው ገንዘቡ ለሕዝብ እንደሚመለስ የጦሩ አዛዥ ተናግረዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያጋሯቸው መልዕክቶች አነጋጋሪ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከሰሞኑ ባሠራጩት ጽሁፍ በዋና ከተማዋ ባሉ መንገዶች ላይ ጉድለት ከተገኘ የግንባታውን ኮንትራት የወሰዱትን ሰዎች አንገታቸውን እንደሚቀሉ አስጠንቅቀዋል።

  9. ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ከመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱን እና ካልተሳካ ግን ጥቃት እንደሚጀምሩ አስጠነቀቁ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ረቡዕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታውቀው ከስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ግን ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ‘ኦፕሬሽን ኤፒክ ፊዩሪ’ ብለው የሰየሙትን ዘመቻ በተኩስ አቁም ጋብ ካደረጉት ስድስት ሳምንታት ቢያልፉም በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ንግግር ግን እምብዛም ለውጥ እያሳየ አይደለም።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዚህ ሳምንት በኢራን ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጸም ለማዘዝ ተቃርበው እንደነበር ተናግረው ለድርድር ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት በሚል መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ዛሬ ለጋዜጠኞች “ከኢራን ጋር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ምን እንደሚሆን እናያለን። ከስምምነት ላይ እንደርሳለን ወይንም ትንሽ አስቀያሚ የሆነ ነገር እናደርጋለን። ነገር ግን ያ አይሆንም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    “ተጨማሪ ዕድል መስጠት እፈልጋለሁ፤ ምንም የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም” ብለዋል።

    አክለውም "በሀሳብ ደረጃ ከብዙ ሰዎች ይልቅ ጥቂቶች ቢሞቱ እመርጣለሁ። በማንኛውም መንገድ ልናደርገው እንችላለን።"

    ቴህራን በበኩሏ ትራምፕ ጦርነት ለመጀመር እያሴሩ ነው ስትል በመወንጀል ማንኛውም ጥቃት ቢፈጸምባት ከመካከለኛው ምሥራቅ ባሻገር አጸፋ ለመስጠት ዝታለች።

    የአገሪቱ አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ “በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት ከተፈጸመ በአካባቢው የሚታሰበው ጦርነት አሁን ከቀጣናው ያልፋል” ብሏል።

    የኢራን ፓርላማ አፈጉባዔ እና ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ባጋር ጋሊባፍ በበኩላቸው በድምጽ ባስተላለፉት መልዕከት “ጠላት በይፋም ሆነ በስውር የሚያደርገው እንቅስቃሴ” አሜሪካኖች አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በዛሬው ዕለት ቴህራን መሆናቸው ተሰምቷል። ኢራን አዲስ የሰላም ዕቅዷን በፓኪስታን በኩል ለአሜሪካ የሰጠችው በዚህ ሳምንት ነው።

    ነገር ግን የሰላም ዕቅዱ ከዚህ በፊት ካቀረበችው የሚለይ ነገር እንደሌለው ተንታኞች ተናግረዋል።

  10. የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ አሜሪካ “አዲስ ጦርነት ለመጀመር” ትፈልጋለች አሉ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ አሜሪካ አዲስ ጦርነት ለመጀመር ትፈልጋለች ሲሉ ተናገሩ። አፈጉባዔው አክለውም አሜሪካ እስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን እጅ እንደምትሰጥ ተስፋ ታደርጋለች ብለዋል።

    ጋሊባፍ በኢራን መገናኛ ብዙኃን ላይ በሰጡት የድምጽ አስተያየት “ጠላት በግልጽም ሆነ በስውር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ባሻገር ወታደራዊ ዓላማዎቹን ፈጽሞ እንዳልተዋቸው እና አዲስ ጦርነት ለመጀመር እንደሚፈልግ ያሳያል” ብለዋል።

    አፈ ጉባዔው አክለውም “ሁኔታውን በቅርበት ስንከታተለው ዩናይትድ ስቴትስ ኢራናውያን እጃቸውን ይሰጣሉ ብላ ተስፋ ታደርጋለች” ብለዋል።

    ታስኒም የዜና ወኪል ላይ በድምጽ በተላለፈ መልዕክታቸው የአገሪቱ መከላከያ በተኩስ አቁሙ ወቅት “ጥንካሬውን ዳግም መገንባቱን” ተናግረዋል።

    ጋሊባፍ “ጠላት ኢራንን ዳግም ቢያጠቃ እንዲጸጸት እናደርገዋለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ዳግመኛ ጦርነት ለመክፈት ጥቂት ሰዓት ሲቀራቸው ሃሳባቸውን መለወጣቸውን ተናግረው ነበር።

    ፕሬዚዳንቱ የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “እየለመኑ” እንደነበረም ገልጸዋል።

    ትራምፕ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊያስፈልግ ይችላል ማለታቸውም ተዘግቧል።

    ከኢራን ጋር በቀጣይ ቀናት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።

  11. 6 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫኑ መርከቦች የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋረጡ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምትቀዝፍ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ለሁለት ወራት በባሕረ ሰላጤው አገራት ቆመው የነበሩ ሦስት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ረቡዕ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥን ማቋረጣቸው ተገለጸ።

    ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ የሚጓጓዝ 6 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ ናቸው የተባሉት እነዚህ መርከቦች ወደ እስያ ጉዞ መጀመራቸውን ኤልኤስኢጂ እና ኬፕለር የተባሉ የመርከብ እንቅስቃሴን የሚከታተሉ ተቋማት አስታውቀዋል።

    እነዚህ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በዚህ ወር ኢራን እንዲያልፉ ከፈቀደችላቸው እና ባሕረ ሰላጤውን ለቅቀው ከወጡ በጣት የሚቆጠሩ መርከቦች መካከል መሆናቸው ተገልጿል።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት ሆርሙዝ በመዘጋቱ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።

    የደቡብ ኮሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እና 2 ሚሊዮን በርሜል የኩዌት ድፍድፍ ነዳጅን የጫነው ግዙፍ መርከብ ሁለት የቻይና መርከቦችን ተከትሎ ወሽመጡን ረቡዕ ዕለት አቋርጧል።

    የኬፕለር መረጃ እንደሚያሳየው መርከቡ ጭነቱን ለማራገፍ የአገሪቱ የነዳጅ ማጣሪያ ወደሚገኝበት ኡስላን እያመራ ነው።

    የደቡብ ኮሪያ ኤነርጂ ኩባንያ ኤስኬ ኢነርጂ በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

  12. የዓለም ጤና ድርጅት በኢቦላ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በላይ እንደሚጨምር አስታወቀ

    የዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለሥልጣናት 51 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን አስታውቀዋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለሥልጣናት 51 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን አስታውቀዋል

    የዓለም ጤና ድርጅት በኢቦላ መያዛቸው የተጠረጠረ ሰዎች 600 መድረሳቸውን እና በቫይረሱ ምክንያቱ እንደሞቱ የሚገመቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 139 መድረሱን አስታወቀ።

    ድርጅቱ አክሎም ቫይረሱን ለመመርመር ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰዱ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ተናግሯል።

    በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ 51 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው ሲረጋገጥ በጎረቤት ኡጋንዳ ደግሞ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ በምርመራ ተደርሶበታል ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

    በጄኔቫ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ኃላፊው በአሁን ሰዓት የተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ቡንዲቡግዮ የተባለው ዝርያ ሲሆን “ከሁለት ወራት በፊት” መሰራጨት እንደጀመረ ይገመታል ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የዓለም ጤና ድርጀት ባይረሱ ወረርሽኝ የሚባል ደረጃ ላይ አለመድረሱን በመግለጽ የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ነው ሲል አውጇል።

    ዶ/ር ቴድሮስ የድርጅቱ ጤና ባለሙያዎች ማክሰኞ ዕለት ተሰብስበው “የወረርሽኝ አደጋ” አለመሆኑ ላይ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

    "ድርጅቱ የጤና ስጋቱን በብሔራዊ እና ቀጣናው ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን አነስተኛ መሆኑን ገምግሟል” ብለዋል።

    በኢቦላ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች የሚኖሩት ቫይረሱ በጀመረበትት ኢቱሪ ነው። በኡጋንዳ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሁለት ሕሙማን ደግሞ ከኮንጎ መትተው ካምፓላ ያረፉ መሆናቸው ተገልጿል።

    የድርጅቱ ኃላፊ “በኮንጎ ያለው ስርጭት ሰፊ መሆኑን እናውቃለን” ሲሉ አክለዋል።

    በኮንጎ በቫይረሱ መያዝዋ የተረጋገጠው የመጀመርያዋ ሴት ነርስ ናት።

    ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዚህ ቀደም 17 ጊዜ የኢቦላ ወረርሽኝ አጋጥሟት የሚያውቅ ቢሆንም ቡዲቡግዮ የተባለው ዝርያ ግን ላለፉት አስርት ዓመታት ተከስቶ አያውቅም።

  13. ቻይና ከዶናልድ ትራምፕ ጉብኝት በኋላ 200 ቦይንግ አውሮፕላኖችን እንደምትገዛ አረጋገጠች

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ቻይና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ ባለፈው ሳምንት በቤይጂንግ ከተገናኙ በኋላ 200 የቦይንግ አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማቷን አረጋገጠች።

    በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ ለአውሮፕላን ሞተር ክፍሎች እና መለዋወጫዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለቻይና እንደምትሰጥ የቤይጂንግ የንግድ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።

    ሁለቱ ወገኖች በጥቅምት ወር የተስማሙበትን የታሪፍ ቅነሳ ለማራዘም እና እያንዳንዳቸው 30 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከዚያ በላይ በሚያወጡ እቃዎች ላይ የታሪፍ ቅነሳ ለማድረግ እንደሚሰሩ ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።

    ቻይና ይህንን ይፋ ያደረገችው ትራምፕ ቤይጂንግን ከጎበኙ ከጥቂት ቀናት በኋላ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ አገሪቱ መጥተው ከፕሬዚዳንቱ ጋር ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ በቻይና በነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል በርካታ የንግድ ስምምነቶች ተደርሷል። ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ ገበሬዎች ወደ ቻይና ገበያ በቀላሉ እንዲገቡ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል።

    ትራምፕ አርብ ዕለት የቻይና ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለጋዜጠኞች "ከቦይንግ ከ200 በላይ አውሮፕላኖችን መግዛትን ጨምሮ ብዙ ጥሩ የሚባሉ የንግድ ስምምነቶችን አድርገናል፤ 750 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል። ይህም እስካሁን ድረስ ከነበረው ትልቁ ትዕዛዝ ይሆናል" ብለዋል።

    ከትራምፕ ጋር ወደ ቻይና ከተጓዙት የንግድ ልዑካን መካከል የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኬሊ ኦርትበርግ እንዲሁም የቴስላ ኃላፊ ኤለን መስክ እና የግዙፉ ናቪዲያ የአይአይ ቺፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጄንሰን ሁዋንግም ይገኙበታል።

    ቦይንግ ከጉብኝቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ "ወደ ቻይና በጣም የተሳካ ጉዞ አድርገናል እናም የቻይና ገበያን ለቦይንግ አውሮፕላኖች እንደገና የማስከፈት ዋና ግባችንን አሳክተናል" ብሏል።

    "ይህም መጀመሪያ 200 አውሮፕላኖችን ለመግዛት የተደረሰ ስምምነትን ያካትታል፤ ከዚህ የመጀመሪያ ስምምነት በኋላም ተጨማሪ ትዕዛዞች እንደሚመጡ እንጠብቃለን" ሲል አክሏል።

    የቻይና እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት እአአ በጥቅምት 2025 በደቡብ ኮሪያ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ እስከ ኅዳር ወር ድረስ የታሪፉን ገደብ ለማራዘም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    ይህ ስምምነት የአሜሪካን የቻይና እቃዎች ላይ የሚጣሉትን ታሪፍ መቀነስ እና ቤይጂንግ ብርቅዬ ማዕድናት እና ማግኔቶችን ወደ ውጭ መላክ ላይ የጣለችውን ገደብ ማንሳትን ያካትታል።

  14. ሩሲያ እና ቻይና የአሜሪካን “ወታደራዊ ጀብዱዎች” አወገዙ

    የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሩሲያ እና ቻይና በጋራ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ የምትፈጽማቸውን “ወታደራዊ ጀብዱዎች” አወገዙ።

    አሜሪካ “በመላው ዓለም የምታካሂዳቸውን ወታደራዊ ጀብዱዎች” እንደሚያወግዙ የሁለቱ አገራት ፕሬዝዳንቶች ገልጸዋል።

    የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቤጂንግ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ “በሌሎች አገራት የሚፈጸሙ ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃቶችን” ተችተዋል።

    የሁለቱ አገራት መግለጫ ኢራን እና ቬንዝዌላን እንደሚመለከት ይታመናል።

    በመግለጫቸው “ድርድርን በመጠቀም ጥቃት መፈጸምን፣ የሉዓላዊ አገራት መሪዎችን መግደልን፣ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን፣ በአደባባይ መሪዎችን ይዞ ለፍርድ ማቅረብን እና የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ መሞከርን” አውግዘዋል።

    አሜሪካ የምትወስዳቸው እርምጃዎች የመንግሥታቱ ድርጅትን ስምምነቶች እና ዓለም አቀፍ ሕግጋት “ክፉኛ” እንደሚጥሱም ገልጸዋል።

  15. ኢራን በድጋሚ ጥቃት ከተከፈተባት ግጭቱ “ቀጣናውን እንደሚሻገር” አስጠነቀቀች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ከሰነዘሩ ግጭቱ “ከቀጠናውም ያለፈ እንደሚሆን” የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስጠነቀቀ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና እስራኤል በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት ለመጀመር እየዛቱ ይገኛሉ።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “ኢራን ላይ በድጋሚ ወረራ ከተፈጸመ፤ ቀጣናውን ያዳርሳል የተባለው ጦርነት ከቀጣናውም ይሻገራል” ብሏል።

    “የምንወስደው ደምሳሽ እርምጃ አስባችሁ የማታውቁት ቦታ ሳይቀር ይደርሳል” ሲልም አብዮታዊ ዘቡ አስጠንቅቋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በድጋሚ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረች “ብዙ አዳዲስ ነገር ይጠብቃታል” በማለት ለትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።

  16. አሜሪካ እና እስራኤል ማህሙድ አህመዲነጃድን ወደ ኢራን መሪነት ለማምጣት ዕቅድ እንደነበራቸው ተዘገበ

    የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸሙት የመጀመሪያ ጥቃት ወቅት በቁም እስር ላይ ናቸው የተባሉትን የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድን ለማስለቀቅ እና የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት የተቃደ ዓላማ እንደነበረው የአሜሪካው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገበ።

    ጋዜጣው እንዳለው የእስራኤልን የመጀመሪያ ዙር ጥቃት ተከትሎ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከተገደሉ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በይፋ ሁኔታው የአገሪቱን አመራር ለመረከብ “አገር ውስጥ ላለ አንድ ሰው የተሻለ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር ሲል አስታውሷል።

    “ይህም አሜሪካ እና እስራኤል ወደ ጦርነቱ የገቡት ግልጽ የሆነ እና ያልተጠበቀ ዓላማን ይዘው እንደሆነ አሁን ግልጽ ሆኗል” በማለት “በፀረ እስራኤል እና አሜሪካ ጠንካራ አቋማቸው የሚታወቁት የቀድሞው የኢራን ፕሬዝዳንት መሐሙድ አህመዲነጃድ” ምርጫቸው እንደነበሩ ዘግቧል።

    ኒው ዮርክ ታይምስ “ስለ ዕቅዱ ገለጻ የተደረገላቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ያልተጠበቀ ሐሳብ የተዘጋጀው በእስራኤል መሆኑን እና አህመዲነጃድም እንደሚያውቁት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በፍጥነት ከታሰበው ውጪ ሆኗል” በማለት ገልጿል።

    የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ከቁም እስር ለማስለቀቅ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን ዜናውም በተነገረበት ጊዜ አህመዲነጃድ በጥቃቱ መገደላቸው ቢዘገብም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕይወት እንዳሉ የማስተባበያ ዜናዎች ወጥተዋል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባለፉት ሦስት ወራት ማህሙድ አህመዲነጃድ በጥቃቱ ስለደረሰባቸው ጥቃትም ሆነ ስላሉበት ሁኔታ ምንም የተነገረ ነገር ካለመኖሩም በተጨማሪ በይፋ ታይተው አይታወቁም።

  17. በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    በደቡብ ሊባኖስ የደረሰው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከተገደሉት መካከል ሦስት ሕጻናት እና ሦስት ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

    አሥር የሚደርሱት ሰዎች በዲር ቆኖን ከተማ አንድ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ የውጊያው አካል ሆኗል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነታቸውን በ45 ቀናት ማራዘማቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ቢናገሩም፤ ጥቃቶች መቀጠላቸው ተገልጿል።

    አብዛኛው ጥቃት እየደረሰ ያለው በደቡብ ሊባኖስ ነው። እስራኤል ሄዝቦላህን ዒላማ ማድረጓን ብትገልጽም ሕጻናትን ጨምሮ ንጹኃን ዜጎችም መገደላቸውን ሊባኖስ አስታውቃለች።

  18. የቻይናው ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ “ቁልፍ የሆነ ነጥብ ላይ” ደርሷል አሉ

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ “ቁልፍ የሆነ ነጥብ ላይ” ደርሷል ማለታቸው ተገለጸ።

    የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው አሁን ያለው ሁኔታ ከጦርነት ወደ ሰላም የሚደረግ ሽሽግር ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እያስተናገዱ የሚገኙት ጂንፒንግ “ግጭቱን በድጋሚ መጀመር ተቀባይነት የለውም” ሲሉም ተናግረዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ባለ አራት ነጥብ ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ “ዓላማዬ ዓለም አቀፍ ስምምነት መፍጠር እና ውጥረትን ማርገብ” ብለዋል።

    ባለፈው ወር ከአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼኽ ካሊድ ቢን መሐመድ ዛይን አል ናህያ ጋር በተገናኙበት ወቅት ባለ አራት ነጥብ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

    ምክረ ሐሳቡ ሰላም፣ ብሔራዊ ልዕልና፣ ዓለም አቀፍ ሕግ ማክበር እንዲሁም ለልማት እና ደኅንነት መተባበር ላይ የተመረኮዘ ነው ተብሏል።

  19. አሜሪካ በድጋሚ ጥቃት ከከፈተች “ብዙ አዳዲስ ነገር ይጠብቃታል” ስትል ኢራን አስጠነቀቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በድጋሚ ጥቃት መሰንዘር ጀመረች “ብዙ አዳዲስ ነገር ይጠብቃታል” በማለት ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጡ።

    ትራምፕ ቴህራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ለመክፈት መዛታቸውን ተከትሎ “ወደ ውጊያ አውድማ ከተመለሱ ብዙ አዳዲስ ነገር እንደሚጠብቃቸወ ላረጋግጥ እወዳለሁ” ሲሉ አራግቺ አስጠንቅቀዋል።

    አራግቺ በኤክስ ገጻቸው “የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ከወራት በኋላ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የጦር አውሮፕላን መውደሙን የአሜሪካ ምክር ቤት አምኗል” ብለዋል።

    “ኃያል የሆነው ጦራችን ኤፍ-35 ተዋጊ ጀትን መትቶ በመጣል የመጀመሪያው መሆኑ ተረጋግጧል” ሲሉም አክለዋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን ላይ ዳግመኛ ጦርነት ለመክፈት ሊወስኑ “አንድ ሰዓት ሲቀራቸው” ሐሳባቸውን መለወጣቸውን ገልጸዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “እየለመኑ” እንደነበረ ተናግረዋል። ትራምፕ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊያስፈልግ ይችላል ማለታቸውም ተዘግቧል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለትራምፕ ዛቻ በሰጡት ምላሽ “ወደ ውጊያ አውድማው ከተመለሱ፤ ባገኘነውን ትምህርት እና ተሞክሮ አማካኝነት ብዙ አዳዲስ ነገሮች እናሳያቸዋለን” ብለዋል።

    ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ሊከፍቱ ይዘውት የነበረውን ዕቅድ በባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ መሠረት መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ለድርድር ዕድል እንዲሰጥ እንደጠየቁ ተገልጿል።

  20. ትራምፕ ኢራንን ዳግም ለማጥቃት ሊወስኑ “አንድ ሰዓት ሲቀራቸው” ሐሳባቸውን እንደለወጡ ተናገሩ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ዳግመኛ ጦርነት ለመክፈት ሊወስኑ “አንድ ሰዓት ሲቀራቸው” ሐሳባቸውን መለወጣቸውን ተናገሩ።

    የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “እየለመኑ” እንደነበረም ገልጸዋል።

    ትራምፕ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊያስፈልግ ይችላል ማለታቸውም ተዘግቧል።

    ከኢራን ጋር በቀጣይ ቀናት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።

    “ሁለት ወይም ሦስት ቀን ያለው። አርብ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ ወይም ቀጣይ ሳምንት። ውስን ዕድል አለ። የኒውክሌር መሣሪያ እንዲታጠቁ መፍቀድ የለብንም” ብለዋል።

    ትራምፕ ዛሬ ማክሰኞ ኢራን ላይ ጥቃት ሊከፍቱ ይዘውት የነበረውን ዕቅድ በባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ መሠረት መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ለድርድር ዕድል እንዲሰጥ እንደጠየቁ ተገልጿል።

    ኢራን እና አሜሪካ “በጣም ተቀባይነት ያለው” ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ሦስቱ አገራት እንደገለጹላቸው ትራምፕ ጠቅሰዋል።