“በሆርሙዝ በኩል ለማሳለፍ ገንዘብ መጠየቅ ተቀባይነት የለውም” - የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የክፍያ ሥርዓት ለመዘርጋት የምታደርገውን ጥረት "ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አጣጣሉት።
በማያሚ አውሮፕላን ማረፊያ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር በሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ ክፍያ መጠየቅ ተቀባይነት እንደሌለው “እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም ይስማማበታል” ብለዋል።
ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያላትን ይዞታ እና ቁጥጥር በማስፋት በሆርሙዝ ለሚያልፉ መርከቦች የክፍያ ሥርዓት እንደምትዘረጋ አስታውቃለች።
ይሄንን የተቃወሙት ማርኮ ሩቢዮ በጉዳዩ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ማርቀቁን ገልጸዋል።
በባህሬን የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ከ100 በላይ አገራት ደግፈዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም “በፀጥታው ምክር ቤት ታሪክ ብዙ ደጋፊ ያገኘ የውሳኔ ሐሳብ ነው” ብለዋል።
ጉዳዩን ቻይና ሳሉ እንዳነሱት ጠቅሰው “የትኛውም አገር ክፍያን አልደገፈም” ብለዋል።
ይህ አካሄድ ዲፕሎማሲያው ንግግርን እንደሚያሰናክልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “እንደዚህ ካደረጉ ለዓለም ስጋት ነው። ፍጹም ሕገ ወጥም ነው” ሲሉ አክለዋል።