ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተመድ ልዑካን እና የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች መቀለ ገቡ
የተባበሩት መንግሥታት ልዑካን፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት የፌደራል መንግስት የትግራይ ዋና ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ክልሉ ተጓዙ፡፡ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ ከስምንት ሀገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የተመድ እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ጭምቅ ሃሳብ
- ኤርትራ ትራኮማን ሙሉ በሙሉ ማስወገዷን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ
- የካናዳ ፖሊስ ከቅንጡ ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ ጋር በተያያዘ 12 ተጠርጣሪዎችን ያዘ
- ዩኬ ከዌስት ባንክ ሰፈራ ጋር በተያያዘ የግንባታ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች
- ሩሲያን ከክሬሚያ የሚያገናኘው ድልድይ በከፊል ተደረመሰ
የቀጥታ ሽፋን
ሩሲያን ከክሬሚያ የሚያገናኘው ድልድይ በከፊል ተደረመሰ
ሩሲያን በይዞታ ሥር ከምትገኘው ክሬሚያ ጋር የሚያገናኘው ዋነኛ ድልድይ በዩከሬን ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጥቃቱ “ለሳምንታት ሲወጠን የነበረ ኦፕሬሽን” መሆኑን ገልጸዋል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ያጋሯቸው ምሥሎች የክሬሚያ ድልድይ ተደርምሶ፣ ውሃ ውስጥ ገብቶ ያሳያሉ። የድልድዩ መደርመስ ለሩሲያ ከፍተኛ ኪሳራ እንደሆነ ተገልጿል።
ሩሲያ ድልድዩን “ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ ሁኔታ” መልሳ እንደምትገነባ አስታውቃለች።
ድልድዩ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መረጃ እንደተሰጣቸው ቢገለጽም እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
የኪቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊስችኮ እንደተናገሩት፤ ሩሲያ መዲናዋን ዒላማ በማድረጓ ምክንያት ወደ ዲፕሮ የሚወስዱት በሰሜን እና ደቡብ አቅጣጫ የሚገኙ ድልዮች ተዘግተዋል።
ዩክሬን የክሬሚያ ድልድይን ዒላማ የምታደርገው የሩሲያ ወታደሮች ወደ ጦር ግንባር የሚጓዙበት ዋነኛ መተላለፊያ ስለሆነ ነው።
አሁን በድልድዩ የደረሰው ጉዳት ከዚህ ቀደሞቹ የከፋው ነው። የድልድዩ አብላጫው ክፍል መጎዳቱም ተገልጿል።
ዩኬ ከዌስት ባንክ ሰፈራ ጋር በተያያዘ የግንባታ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች
በይዞታ ሥር በሚገኘው ዌስት ባንክ ከተስፋፉ የሰፈራ ማዕከሎች ጋር በተያያዘ ዩናይትድ ኪንግደም የግንባታ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ከዌስት ባንክ ሰፈራ ጋር በተያያዘ የዩኬ መንግሥት ጠንካራ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል። በግንባታ ተቋማቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
ስምንት የግንባታ ተቋማት እና አልሚ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ፤ የፋይናንስ ዝውውራቸውን እንደሚገታ እና በዌስት ባንክ ግንባታ የማካሄድ አቅማቸውን እንደሚገድብ ተገልጿል።
ዓለም አቀፍ ሕግ ሰፈራን የሚከለክል ሲሆን፤ ባለፉት ወራት በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየተባባሰ መጥቷል።
በምሥራቅ እየሩሳሌም፣ ኢ1 በተባለ አካባቢ ሕንጻ ለመገንባት ጨረታ ማስገባት የሚቻልበት ቀነ ገደብ ሁለት ቀናት ይቀሩታል።
ምሥራቅ እየሩሳሌምን ነጥሎ ዌስት ባንክን ለሁለት የሚከፍለው የግንባታ ዕቅዱ ዓለም አቀፍ ውግዘት ገጥሞታል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጸሐፊ ኤድ ሚሊባንድ እንዳሉት፤ የኢ1 ግንባታ በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል “የሁለት አገራት መፍትሔ” መስጠትን ያደናቅፋል።
የግንባታ ዕቅዱ “በፍልስጤም ማዕከል” በኩል እንደሚያልፍም አክለዋል።
ዩኬ በጣለችው ማዕቀብ እስራኤላዊው የንቅናቄ ቡድን ‘ሳቭ 9’ ተካትቷል።
ቡድኑ ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ ማሰናከሉ ተገልጿል።
ባለፈው ወር የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሱ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
- ተያያዥ ዜናዎች፡
የካናዳ ፖሊስ ከቅንጡ ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ ጋር በተያያዘ 12 ተጠርጣሪዎችን ያዘ
የካናዳ ፖሊስ ከቅንጡ ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ስምንት ናይጄሪያውያንን ጨምሮ 12 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ።
ተጠርጣሪዎቹ ቅንጡ መኪኖችን ዘርፎ ወደ ምዕራብ አፍሪካ በመላክ ተወንጅለዋል።
የኦንታሪዮ፣ ፒል ፖሊስ እንዳለው 96 ቅንጡ መኪኖች በመርከብ ካርጎዎች ውስጥ ተይዘዋል።
ተሽከርካሪዎቹ 4.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ እና በካናዳ ወደብ ሊዘዋወሩ እንደነበር ተገልጿል።
ከሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ ወደ አፍሪካ አገራት በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ ተሽከርካሪዎችን ለረዥም ጊዜ ፖሊስ ሲከታተል ነበር።
ተጠርጣሪዎቹ 231 ክሶች እንደሚቀርብባቸው ይጠበቃል። ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይም የእስር ማዘዣ ወጥቷል።
የፍርድ ቤት ክሱ ሲገባደድ አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች ከካናዳ ሊባረሩ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ፖሊስ ለወራት በቅንጡ መኪኖች ምዝበራ ላይ ክትትል ማድረጉን አስታውቋል።
ያለፈው የካቲት ላይ ከካናዳ ድንበር ጥበቃ ጋር በመተባበር ክትትሉ ተካሂዷል። በክትትሉ የተሰረቁ ተሽከርካሪዎች ማቆያ የነበረ መጋዘን ተገኝቷል።
የዝርፊያ ሰንሰለቱን እንዲሁም የመኪኖቹን ዝውውር ያስተባበሩት አምስት ግለሰቦች ከሌሎች አባሪዎች ጋር እንደሆነም ተመልክቷል።
ኤርትራ ትራኮማን ሙሉ በሙሉ ማስወገዷን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ
ኤርትራ፣ ለዓይነ ስውርነት በመዳረግ በዓለም ላይ ቀዳሚ ተላላፊ በሽታ የሆነው ትራኮማን በሙሉ በሙሉ ያስወገደች 11ኛዋ አፍሪካዊት አገር መሆኗን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ይህንን “ታሪካዊ ስኬት” ማረጋገጥ ለቻሉት የኤርትራ መንግሥት እና ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ትናንት ሰኞ ኅዳር 7 ቀን 2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኤርትራ ትራኮማን “ከማኅበረሰብ ጤና ችግርነት ማስወገዷን” እንዳረጋገጠ አስታውቋል። ኤርትራ ይህንን ዋነኛ የጤና ምዕራፍ በማስመዝገብ ከአፍሪካ 11ኛ፣ ከዓለም 34ተኛ መሆኗን ገልጿል።
‘ክላሚዲያ ትራኮማቲስ’ በሚባል ባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣው ትራኮማ፣ ዓይነ ስውርነትን በማምጣት በዓለም ቀዳሚው ተላላፊ በሽታ እንደሆነ የድርጅቱ መረጃ ያሳያል። በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ዓይን እና አፍንጫ ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር በሚደረግ ንክኪም ይተላለፋል።
በተደጋጋሚ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች የዓይናቸው ሽፋሽፍቶች የሚታጠፉ ሲሆን በመጨረሻም ዓይነ ስውርነት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ኤርትራ ውስጥ በርካታ ሰዎች የጤና አገልግሎት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ውስን በሆነባቸው የገጠር አካባቢዎች ስለሚኖሩ፣ የትራኮማ ተጋላጭነት እንደነበረ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
ይሁን እንጂ ኤርትራ በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሠረት ‘ሴፍ’ (SAFE) የተባለውን ስትራቴጂ አስፈላጊውን እርምጃ ወስዳለች ተብሏል።
በስትራቴጂው አማካኝነት፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ እና የንፅህና አገልግሎቶች እንዲስፋፉ መደረጉ ተገልጿል። በሽታው በብዛት ይታይባቸው በነበሩ ዞኖች መጠነ ሰፊ የማኅበረሰብ ጤና ዘመቻዎች እንደተካሄዱም ድርጅቱ አስረድቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ “ኤርትራ፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት ቆራጥ ጥረት በኋላ ትራኮማን ከሕዝብ ጤና ችግርነት ወደ ታሪክ መዝገብ አስገብታዋለች” ብለዋል።
በኤርትራ የተገኘው ውጤት “በአገራዊ ቁርጠኝነት ምን ዓይነት ስኬት ላይ መድረስ እንደሚቻል የሚያሳይ ጠንካራ ምሳሌ” መሆኑንም ገልጸዋል። “ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ የማኅበረሰብ አመራር እና ጠንካራ አጋርነት” ለዚህ ስኬት አስተዋጾ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ተያያዥ ዜናዎች፡
የባህሬን ፍርድ ቤት ኢማሞችን ጨምሮ በ64 የሺዓ ሙስሊሞች ላይ የዕድሜ ልክ እስራት ማሳለፉን ተሟጋቾች ገለጹ
የባህሬን ፍርድ ቤት ከኢራን ጋር በተያያዘ የሽብር ክስ በአብዛኛው ኢማሞች በሆኑ በ64 የሺዓ ሙስሊሞች ላይ የእድሜ ልክ እስር ማስተላለፉን ተቀማጭነቱን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ገለጸ።
የባህሬን የመብት እና የዲሞክራሲ ተቋም እንደሚናገረው፣ በባህሬን መዲና ማናማ ከተማ የሚገኘው ከፍተኛ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ብይን የእድሜ ልክ እስራት ከተበየነባቸው ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎች አምስት ግለሰቦች የ15 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።
አቃቤ ሕግም ፍርዱ መተላለፉን ያረጋጋጠ ሲሆን የግለሰቦቹን ብዛት እና ማንነት ግን አልገለጸም።
ሆኖም የመብት ተሟጋች ቡድኑ እንደገለጸው የጁመዓ ሶላትን የሚመሩትን ሸኽ መሐመድ ሳንቁር እና ሸኽ አሊ አል ሳዳዲን ጨምሮ 47ቱ ኢማሞች ናቸው።
13 የሺዓ ሃይማኖት መሪዎችም በሌሉበት ፍርዱ ተላልፎባቸዋል።
ግለሰቦቹ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው የሽብር ቡድን በማቋቋም ክስ እንደቀረበባቸው አቃቤ ሕግ አስረድቷል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ ግን በግለሰቦቹ ላይ የተላለፈውን ፍርድ አውግዟል።
"በግለሰቦቹ ላይ ስቅይት እና የግዳጅ ኑዛዜ እንደተፈፀመባቸው እንዲሁም ክሳቸውን እንዳይከላከሉ ስለመደረጋቸው ተዓማኒ ማስረጃዎች አሉ" ብሏል።
በሱኒ ሙስሊም የምትመራው ባህሬን፣ አሜሪካ እና እስራኤል በሺዓ ሙስሊሞች በምትመራው ኢራን ላይ የካቲት ወር ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ አብዛኞቹ የሺዓ ሙስሊም የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ማሰሯ ተዘግቧል።
ግለሰቦቹ በስለላ እና በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው። አብዛኞቹም "ለኢራን የጥላቻ እና የወንጀል ድርጊቶች ርህራሄ እና አድናቆት" በማሳየት ከተከሰሱ በኋላ የባህሬን ዜግነታቸውን ተነጥቀዋል።
በጦርነቱ ኢራን ከአሜሪካ ለሚፈፀምባት ጥቃት አፀፋ ለመስጠት የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች በሚገኙባቸው በባህሬን እና ሌሎች አረብ አገራት ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎችን ተኩሳለች።
እሁድ ዕለት የባህሬን ጦር በርካታ የኢራን የአየር ጥቃቶችን ማክሸፉን ገልጿል።
የተመድ ልዑካን እና የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች መቀለ ገቡ
የተባበሩት መንግሥታት ልዑካን፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት የፌደራል መንግስት የትግራይ ዋና ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ክልሉ ተጓዙ፡፡
በልዑካን ቡድኑ ውስጥ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ ከስምንት ሀገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች፣ የተመድ እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙበት ትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የጉዞው ዓላማም በትግራይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በአካል ለመመልከት እና በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል።
ልዑካኑ ከትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ጋር ውይይት እንደጀመሩም የተገለጸ ሲሆን የሰብአዊ ዕርዳታ፣ ተፈናቃዮች፣ በትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሂደት እንዲሁም የክልሉ የሰላም ጉዳይ ውይይት የሚደረግባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ናቸው ተብሏል።
የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ጉዳዮች ዋና አስፈፃሚ አቶ አሰፋ አብርሃ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከክልል እስከ ወረዳ የዘለቀ የአስተዳደር ሥርዓት አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ለእንግዶቹ ማብራራቸውን ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑካን ከዛሬ ሕዳር 8 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በመቀለ ከተማ እንደሚያደርጉ ዘገባው አመልክቷል።
ልዑካኑ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ሁለቱ ኃይሎች ውይይት እንዲያደርጉ የሚያሳስብ መግለጫዎችን ማውጣታቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ስለተቀሰቀሰው ጦርነት ጥልቅ ስጋት እንዳለው በመግለጽ፣ ተፋላሚ ወገኖች ግጭቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ወደ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የህወሓት መሪዎች "መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመክፈት ባሳለፉት ደካማ ውሳኔ ማዘናቸውን" መግለጻቸው ይታወሳል።
አምባሳደሩ "ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ" በመምከር አሜሪካ ኢትዮጵያን ወደተሳሳተ መንገድ ለመምራት የሚሞክሩ ተጨማሪ አመራሮች ላይ ማዕቀብ ለመጣል አማራጩ እንዳላት አመልክተዋል።
ተያያዥ ዘገባዎች፦
ትራምፕ ከዢ ጂንፒንግ እና ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ወደ እስያ አቀኑ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ለመገናኘት ወደ እስያ የሚያደርጉትን ጉዞ ትናንት መጀመራቸው ተገለጸ።
ትራምፕ ከአቻዎቻቸው ዢ እና ፑቲን ጋር በሚኖራቸው ቆይታ የዩክሬንን እና የኢራንን ጦርነት ጨምሮ ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ ሰኞ እለት በዋሽንግተን ዲሲ ወደ አውሮፕላናቸው ከመግባታቸው በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ በቻይና ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ሊገናኙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ትራምፕ በደቡባዊቷ ሼንዠን ከተማ በሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን ከመሪዎቹ ጋር ለመገናኘት ማቀዳቸውን ዋይት ሃውስ አስታውቆ ነበር።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፕሬዝዳንቱ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች በተጨማሪ በዓለም ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ስለመቀነስ እንደሚወያዩ በግልጽ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።
ሞስኮ እና ቤጂንግ ስለውይይቱ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
ትናንት ሰኞ ከዋሽንግተን ዲሲ የእስያ ጉዟቸውን የጀመሩት ትራምፕ፣ በኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ 21 አባል አገራት ለሁለት ቀናት ወደሚሰበሰቡበት ሼንዠን ከተማ ረቡዕ ይደርሳሉ ተብሏል።
ትራምፕ በማግስቱ ሐሙስ ከዢ ጂንፒንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
ይህ ውይይት፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአውሮፓውያኑ 2025 በድጋሚ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከቻይናው መሪ ጋር የሚያደርጉት አራተኛው ስብሰባ ይሆናል።
ትራምፕ ወደ ቀጣናው በሚያደርጉት በዚህ ጉዟቸው፣ ዛሬ ማክሰኞ በፊሊፒንስ ማኒላ ከተማ በሚካሄደው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ማኅበር ጉባኤ ላይም እንደሚገኙ ተገልጿል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ የትራምፕ ጉዞ "ለአሜሪካ ሕዝብ ታሪካዊ ድሎችን የሚያስገኝ እና በኢንዶ ፓሲፊክ የአሜሪካን ጥቅም የሚያስከብር" ሲሉ ገልጸውታል።
- ተያያዥ ዜናዎች፡
ሩሲያ በፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት በኪየቭ የሚገኙ ሁለት ዋና ድልድዮች መመታታቸው ተገለጸ
ሩሲያ በዩክሬን መዲና ኪየቭ ላይ በፈፀመችው የባልስቲክ ሚሳዔል ጥቃት ሁለት ዋና ድልድዮች መመታታቸውን የከተማዋ ከንቲባ ተናገሩ።
ከንቲባው ቫይታሊ ክሊትሽኮ እንዳሉት በሚሳኤል ጥቃቱ የዲኒፕሮ ወንዝ ላይ የተሰሩ በከተማዋ ደቡባዊ እና ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ ድልድዮች ተመትተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ የውሃ እና የኃይል አቅርቦት ተስተጓጉሏል ብለዋል።
በኪዮቭ ከፍተኛ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የገለጹት ከንቲባው፣ ጥቃቱ የደረሰው ከተማዋ ቀድሞውኑ በወሳኝ መሠረተ ልማቶቿ ላይ በደረሰባት ጉዳት እየተፈተነች ባለችበት ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል።
ጥቅምት ወር ላይ በርካታ የከተማዋ ድልድዮች የሩሲያ ጥቃት ዒላማ ሆነዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ሩሲያና በሩሲያ የተያዘውን ክሪሚያን የሚያገናኘው ድልድይ ላይ ለተከታታይ ሁለተኛ ቀን ጥቃት መፈፀሟን በሞስኮ የተሾሙት የክልሉ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
ሁለቱ አገራት ጥቃት የተሰናዘሩት ዩክሬን፣ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ባለሥልጣናት ለዓመታት የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
የአሜሪካ መልዕክተኛ ጃረድ ኩሽነር እና የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲፍ ዊትኮፍ የተሳተፉበት በኦንላይን የተደረገው ንግግር የተካሄደው ሩሲያ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ የዩክሬን ድሮኖች ከፍተኛ ጥቃት እያደረሱባት እንደሆነ ከገለጸች በኋላ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የከፈተችው እአአ በ2022 ነበር።
ለአራት ዓመታት በቀጠለው ጦርነት አንድ አምስተኛ የሆነው የዩክሬን ግዛት በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ይገኛል።
ኪየቭ ፑቲን መጠቅለል የሚፈልጉት የዩክሬንን ምሥራቃዊ ዶንባስ ክልል አሳልፋ መስጠት ባለመፈለጓ እና ፑቲንም ክልሉ "ቀይ መስመራቸው" እንደሆነ በመግለፃቸው ጦርነቱን ለማስቆም እየተካሄደ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እስካሁን ፍሬ አላፈራም።
- ተያያዥ ዜናዎች፡
የኅዳር 8 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል
የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የማክሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።
የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።
በደቡብ አፍሪካ በሁለት የተለያዩ የጀምላ ተኩስ ጥቃቶች 17 ሰዎች ተገደሉ
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ እሁድ ምሽት 17 ሰዎች የተገደሉባቸውን ሁለት የተለያዩ የጅምላ ተኩስ ጥቃቶች እያጣራ መሆኑን አስታወቀ።
በክዋዙሉ ናታል ግዛት አንድ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ውስጥ ስምንት ሰዎች በጥይት ተመተው ተገድለዋል። በስፍራ የደረሰው ፖሊስ የስምንቱም ሕይወት ማለፉን አረጋግጧል።
ከሰዓታት በኋላ ደግሞ በምዕራብ ፕሪቶሪያ አንድ ቤት ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች በጥይት ተመተው ሞተው ተገኝተዋል።
ፖሊስ ሁለቱ ጥቃቶች ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጿል። ተኩሶቹ የተከፈቱት በምን ምክንያት ግን እስካሁን አልታወቀም።
ደቡብ አፍሪካ በወንብድና ቡድኖች የሚፈጸሙትን ግድያዎች ጨምሮ ከባድ ወንጀሎችን መቆጣጠር ቀላል አልሆነላትም። ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ የግድያ ምጣኔ ከሚመዘገብባቸው አገራት አንዷ ናት።
ፖሊስ፣ በክዋዙሉ ናታል ግዛት ከፒተርማሪትዝበርግ ከተማ ወጣ ብሎ ባለ ስፍራ የተኩስ ድምፅ መሰማቱን ተከትሎ ወደ ቦታው ሲያመራ፣ በጥይት የተበሳሳ ነጭ ባለ ሰባት መቀመጫ ተሽከርካሪ ማግኘቱን ገልጿል።
ተሽከርካሪው ውስጥም በርካታ ቦታዎች ላይ በጥይት የተመቱ ስምንት ወንዶች ተገኝተዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ሮበርት ኔትሺዩንዳ “ክስተቱ እንዴት እንደተፈጠረ እስካሁን አልታወቀም፤ ፖሊስ ግድያዎቹ የተፈጸሙበትን ምክንያት እና የተጠርጣሪዎቹን ማንነት ለማወቅ ማስረጃዎችን እየሰበሰበ ነው” ብለዋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ አሰሳ ማካሄድ ጀምሯል።
ሁለተኛው ጥቃት የተፈጸመው ከፕሪቶሪያ በስተምዕራብ አተሪጅቪል ውስጥ በሚገኝ አንድ የጨረቃ መንደር ውስጥ ነው። ፖሊስ፣ ተኩስ በተከፈተበት ስፍራ የስድስት ወንዶችን እና የሦስት ሴቶችን አስከሬን ማግኘቱን አስታውቋል።
ሟቾቹ እሁድ ከምሽቱ ባለ አራት ክፍል ቤት ውስጥ እንደተገደሉ ይታመናል። አስከሬኖቹ በክፍሎቹ ውስጥ ተበታትነው የተገኙ ሲሆን፣ ከቤቱ ውጭም በርካታ ቀለሃዎች ተገኝተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች መጀመሪያ ላይ የተኩሱን ድምፅ ሲሰሙ መብረቅ መስሏቸው ነበር ተብሏል።
በአካባቢው እንዲህ ዓይነት የጅምላ ተኩስ ሲከፈት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ባለፈው ዓመት ጥር ላይ አምስት ወንዶች በቀን አንድ መደብር ደጅ ላይ በተከፈተ ተኩስ ተገድለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በስፋት ተሰራጭተው የሚገኙ ሲሆን፣ የሚፈጸሙ የጅምላ ግድያዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው።
ከትዳር ውጭ ግንኙነት በመመስረታቸው ከኃላፊነት የለቀቁትን የኢንቪዲያ ኃላፊ ለመመለስ ኤሎን መስክ የተሳተፈበት ዘመቻ ተጀመረ
የቻይና ሰላይ እንደሆነች ከተጠረጠረች ሴት ጋር የመሠረቱትን ጨምሮ ከትዳር ውጭ የነበሯቸው የፍቅር ግንኙነቶች ባስነሱት ቅሌት ሳቢያ ባለፈው ሳምንት ሥልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞው የኢንቪዲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጄንሰን ሁዋንግን ወደ ኃላፊነት ለመመለስ አጋሮቻቸው ዘመቻ ጀመሩ።
ለቀድሞው ኃላፊ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተጀመረውን ዘመቻ ከተቀላቀሉት ታዋቂ ሰዎች መካከል የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም የሆነው ኤሎን መስክ እና የፎርትናይት ጌም አምራቹ ኤፒክ ጌምስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቲም ስዊኒ ይገኙበታል።
ታዋቂዎቹ የቴክኖሎጂ ግለሰቦች፣ የግዙፉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቺፕ አምራች ሆነው ኢንቪዲያ የዳይሬክተሮች ቦርድ “ጄንሰንን እንዲመለሱ” የሚጠይቀውን ዘመቻ ደግፈዋል።
ሁዋንግ ከኢንቪዲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሥልጣናቸው የለቀቁት ከጋብቻ ውጭ የነበሯቸው ሁለት የፍቅር ግንኙነቶች ይፋ መሆናቸውን ተከትሎ ነው።
ከእነዚህ ግንኙነቶች ውስጥ አንዱ ለቻይና ትሰልላለች ተብላ ከተጠረጠረች ሴት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከኩባንያው ሠራተኛ ጋር እንደነበር ተገልጿል።
ይህ ቅሌት፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ኢንቪዲያን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከትቶታል።
ቺፕ አምራቹ ኩባንያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንዱስትሪ እንዲሁም ዘርፉ ላይ ለሚታየው ፈጣን መስፋፋት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ኩባንያው፣ የሁዋንግን ግንኙነቶች በተመለከተ የውስጥ ምርመራ እያደረገ ነው።
ይህ ምርመራ እየተደረገም ቢሆን የኢንቪዲያ ቦርድ ሁዋንግን ወደ ሥራቸው እንዲመልስ የሚጠይቀው ይፋዊ ደብዳቤ ላይ መስክን እና ስዊኒን ጨምሮ ከ175,000 በላይ ሰዎች ፊርማቸውን ማኖራቸውን ‘ስታንድ ዊዝ ጄሰን’ የተባለው ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል።
ዘመቻውን የሚያስተባብረው ቡድን ውስጥ የአሁን እና የቀድሞ የኢንቪዲያ ሠራተኞች፣ የኩባንያው አጋሮች፣ ባለአክስዮኖች እና ደጋፊዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ዘመቻ አድራጊዎቹ በደብዳቤያቸው፣ የጄንሰን ሁዋንግ ከኃላፊነት መነሳት “ለኢንቪዲያ የተሻለ ጥቅም እንደሚያስገኝ የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ እስካላቀረባችሁ ድረስ፣ ገለልተኛ ምርመራ እውነታውን እስከሚያጣራ ጄንሰንን ወደ ኃላፊነታቸው መልሷቸው” ብለዋል።
ሁዋንግ ለቻይና ትሰልላች ከተባለችው አሊስ ሁዋንግ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ይፋ በመሆኑ የተነሳውን የቅሌት ማዕበል ተቋቁመው እንደሚያሳልፉት ተጠብቆ ነበር።
ይሁን እንጂ ባለፈው ሐሙስ ዕለት በሥራቸው ከምትገኝ የኢንቪዲያ ከፍተኛ ኃላፊ ጋር ሁለተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል።
እስራኤል ወደ ጋዛ ፈጣን የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ እንድትፈቅድ ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ ጠየቁ
እስራኤል “በመላው ጋዛ አስቸኳይ፣ ፈጣን እና ያልተቆራረጠ የሰብአዊ ርዳታ ተደራሽነትን እንድትፈቅድ" ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጣሊያን አሳሰቡ።
ሦስቱ አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጋዛ ውስጥ ላይ ያለው ሁኔታ “እጅግ አስከፊ” መሆኑን ገልጸዋል።
በጦርነት የተናጠችው ጋዛ ውስጥ በቅርቡ የተከሰተው ጎርፍ የግዛቷ ነዋሪዎች ላይ "ተጨማሪ ስቃይ" ማምጣቱን በመግለጽም አስጠንቅቀዋል።
የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መግለጫ፣ ወደ ጋዛ መግባት የነበረባቸው 150,000 ድንኳኖች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች በድንበር ላይ ተይዘው እንደሚገኙ ጠቅሷል።
የጋዛ መተላለፊያዎችን የሚቆጣጠረው የእስራኤል ጦር በበኩሉ፣ በአሜሪካ ከሚመራው የሰላም ቦርድ እና ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ይናገራል። 93,000 ድንኳኖች እና የክረምት ቁሳቁሶችን የጫኑ 8,600 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባታቸውን አስታውቋል።
አክሎም የመልሶ ግንባታ ሥራ "ሊጀመር የሚችለው ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቁን ከፈታ በኋላ ብቻ ነው" ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በበኩሉ፣ በስፋት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ እና የመሬት መንሸራተት ለበርካታ ሰዎች ሞት፣ በሺህዎች ለሚቆጠሩ መጠለያዎች መውደም እና ወሳኝ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።
የአውሮፓ ኅብረት ቅዳሜ ዕለት ተመሳሳይ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ "ቀጣይነት ያለው እና አውዳሚ የሰብአዊ ቀውስ" ሲል በጠራው ጉዳይ ላይ ያለውን "ጥልቅ ስጋት" በድጋሚ ገልጿል።
ኅብረቱ እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕግን እንድታከብርም አሳስቧል።
በመላው አሜሪካ በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ከተሰረዙ ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸውን ያዙ
የአሜሪካ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ሥርዓት ላይ ያጋጠመውን የቴክኒክ ችግር ተከትሎ በመላ አገሪቱ የተሰረዙት በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ትናንት እሑድ እና ዛሬም አለመጀመራቸው ተገለጸ።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሲን ዱፊ እስከ ሰኞ ድረስ መደበኛ በረራዎች እንደማይጀመሩ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።
በአሜሪካ እሁድ እለት ከ8 ሺህ በላይ በረራዎች መዘግየት ያጋጠማቸው ሲሆን 2 ሺህ 400 በረራዎች ተሰርዘዋል።
ይህም በአየር ማረፊያዎች ትርምስ እና መጉላላት እንዲፈጠር አድርጓል።
የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር በረራዎች መሰረዛቸውን አርብ ዕለት ባስታወቀበት ጊዜ ከ3 ሺህ 500 በላይ አውሮፕላኖች አየር ላይ ነበሩ።
አንዳንዶች ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች አቅጣጫቸውን ለመቀየር የተገደዱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ወደ መዳረሻቸው በርረዋል።
በረራዎች እንዲታገዱ የተወሰነው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከአብራሪዎች ጋር ለመነጋገር የሚያስችለው ወሳኝ የግንኙነት መሥመር ላይ ብልሽት ካጋጠመ በኋላ እንደሆነ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮችን ቀድሞ ከነበረው የመዳብ ገመድ ወደ ፋይበር ኦፕቲክስ ሲቀየር የተገጠመው 'ራውተር' የተሳሳተ መልዕክት ማስተላለፍ መጀመሩን ሚኒስትሩ አክለዋል። ይህ እስከሚስተካከል ድረስ ትንሽ ጊዜ እንደሚወስድም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
መርማሪዎች ያጋጠመው ችግር ትክክለኛ መንስኤ ለማወቅ እየሰሩ ነው።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የአየር ትራፊክ ሥርዓቱን ለማዘመን ተጨማሪ በጀት እንዲያፀድቅ አሳስበዋል።
34 ኪሎግራም የሚመዝን ካናቢስ ሲያዘዋውር የነበረ አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ናይጄሪያ ውስጥ ተያዘ
አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች 33.95 ኪሎግራም የሚመዝን ካናቢስ ይዞ በሌጎስ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጓዝ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ።
የናይጄሪያ ብሔራዊ የአደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር ተቋም እንዳለው፤ የ28 ዓመቱ ግሪን ዳሞንቴ ኪሬ፤ ከታይላንድ ተነስቶ በዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች በኩል አድርጎ ሌጎስ ገብቷል።
በአሜሪካ፣ ጆርጂያ የሚኖረው ግሪን፤ በታይላንድ ቅርጫት ኳስ እየተጫወተ እንደነበር እና “ትስስሩን ለማስፋት” ናይጄሪያን ለመጎብኘት እንደተጓዘ መናገሩ ተገልጿል።
ቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ስለቀረበበት ክስ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።
የናይጄሪያው ተቋም፤ የቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ስልክ ላይ ፍተሻ መካሄዱን አስታውቋል። በዚህም መሠረት ግሪን ስለ አደንዛዥ ዕፁ “እንደሚያውቅ” እና በዝውውሩ “እጁ እንዳለበት” ተደርሶበታል ተብሏል።
ያለፈው ሳምንት ረቡዕ ሁለት ሻንጣዎችን አውሮፕላን ላይ አስጭኖ፣ አንድ አነስተኛ ሻንጣ ይዞ አውሮፕላን ለመሳፈር ሲሞክር በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።
በስሙ አውሮፕላኑ ላይ የተጫኑት ሁለት ሻንጣዎች ውስጥ 32 እሽግ ካናቢስ ተገኝቷል። የተያዘው የካናቢስ ዓይነት ‘ላውድ’ የተሰኘው መሆኑ ተገልጿል።
ሻንጣ ውስጥ የአደንዛዥ ዕፁን እንቅስቃሴ የሚከታተል መሣሪያም ተገኝቷል።
በዴሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ አሁንም በቁጥጥር ሥር አለመዋሉን ሲዲሲ አስታወቀ
የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አሁንም በቁጥጥር ሥር አለማዋሉን አስታወቀ።
ሲዲሲ ይህን ያለው ወረርሽኙ መከሰቱን ካወጀ ከስድስት ወራት በኋላ ነው።
ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የጤና ባለሙያዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈፀም፣ ክፍያ የማያገኙ ሠራተኞች እንዳሉ እና የሕክምና ግብዓት እረጥት መኖሩን የጠቀሰው ማዕከሉ፣ አሁንም ወረርሽኙ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አልዋለም ብሏል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ጂን ካስያ ለሮይተርስ የዜና ወኪል በሰጡት ቃለ ምልልስ “ወረርሽኙ አሁንም አደገኛ መሆኑን እና በቁጥጥር ሥር አለመሆኑን ሁላችንም ተስማምተናል” ብለዋል።
እንደ የአገሪቱ መንግሥት መረጃ ከሆነ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱ ከተገለፀ ከግንቦት ወር ወዲህ ከ11 ሺህ 200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 5 ሺህ 500 ሞቶች ተመዝግበዋል።
ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ በበሽታው የተያዙት በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ከ65 በላይ ሞቶች የተመዘገቡትም ከጤና ተቋማት ውጭ ነው። ኢቦላ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ እያለ በጣም ተላላፊ ነው።
“ይህንን ወረርሽኝ ማስቆም ካልቻልን፣ ዓለም አስከፊውን የኢቦላ ወረርሽኝ ታያለች” ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ አስጠንቅቀዋል።
- ተያያዥ ዜናዎች፡
ፖሊስ በፓሪስ በሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች እና አምስት ዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ ተቃውሞ እንዳይደረግ ከለከለ
የፓሪስ ፖሊስ በአስር ትምህርት ቤቶች እና አምስት ዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ ተቃውሞ እንዳይካሄድ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ክልከላ ጣለ።
ክልከላው የተጣለው ባለሥልጣናት ለሳምንታት የዘለቀውን እና በትምህርት ተቋማት አካባቢ እየተደረገ ያለውን ተቃውሞ እና ግጭት ለመቆጣጠር እሞከሩ ባሉበት ወቅት ነው።
ገደቡ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት በትምህርት ተቋማቱ በ100 ሜትር ክልል ውስጥ ያልተፈቀደ ስብሰባም ሆነ ሰልፍ ማድረግን ይከለክላል።
የፓሪስ የፖሊስ አዛዥ ፓትሪስ ፋውር እንዳሉት ክልከላው በርካታ መስተጓጎሎች፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት እና ግጭቶች በማጋጠማቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ ተቃውሞ ማድረግ የሕዝብ ሃብት እንዲወድም፣ ከትምህርት ማኅበረሰቡ አባላት እና ከሕግ አስፈፃሚ አካላት ጋር ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል ብሏል።
በአገሪቱ መስከረም ወር ላይ ተቃውሞ መካሄድ የጀመረው የተዳከመ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሁኔታ በመቃወም ነበር። ተቃውሞው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እና የኑሮ ውድነትን ወደሚቃወሙ ሰራተኞች እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ተዛምቷል።
ተቃውሞው ከጀመረ አንስቶም 1 ሺህ 548 ሰዎች መታሰራቸውን የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።
ቅዳሜ ዕለት በፓሪስ የተሰባሰቡ 24 ሺህ ሰዎችን ጨምሮ 106 ሺህ ከተለያዩ ቡድኖች የተውጣጡ ሰዎች ወደ አደባባይ መውጣታቸውንም የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ተማሪዎች፣ ማኅበራት እና አክቲቪስቶች ለተቃውሞ ሲወጡ አምስተኛ ቅዳሜቸያው ነው።
ሆኖም የተቃዋሚዎቹም ሆነ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ቀድሞ ከነበረው ያነሰ ነው። ሚኒስቴሩ እንዳለው በቅዳሜ ዕለቱ ተቃውሞ በፓሪስ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን 45 ሰዎች ጨምሮ 219 ሰዎች ታስረዋል።
የየመን ኃይሎች በማፈግፈጋቸው የቀይ ባሕር መተላለፊያ በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር ዋለ
ሳዑዲ አረቢያ የምትደግፋቸው የየመን መንግሥት አጋር ኃይሎች ቁልፍ የሆነውን ባብ ኤል ምንዳብ ወሽመጥ ለመቃኘት ስትራቴጂክ ከሆነው ሥፍራ ለቅቀው መውጣታቸውን አስታወቁ። አካባቢው በኢራን በሚደገፈው የሁቲ አማጺያን ሥር እንደሚገኝም ይፋ አድርገዋል።
የየመን ጦር ቁልፍ ወደሆነው የመርከቦች መተላለፊያ ወታደሮችን እንደሚያሰማራ አስታውቋል። አካባቢው በደቡባዊ ቀይ ባሕር ይገኛል። የየመን ጦር መቀመጫ የሆነውን ኤደን ከተማ ለመከላከል በሚልም ወታደሮች እንደሚሰማሩ ተገልጿል።
አካባቢውን የሚቆጣጠሩት ኃይሎች የተቀየሩት ለሳምንታት ከዘለቀ ውጊያ በኋላ ነው።
ያለፈው መስከረም ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሁቲዎች መተላለፊያ መስመሩን በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ነበር። ይህም ዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።
ሁቲዎች አካባቢውን ሲቆጣጠሩት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ወጥተዋል።
በሁቲዎች የሚመራው መገናኛ ብዙኃን ትናንት እሑድ እንደዘገበው ቡድኑ አካባቢውን በቁጥጥሩ ሥር አውሏል።
ሳዑዲ አረቢያ ስለ ጉዳዩ አስተያየት አልሰጠችም።
የየመን መንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ጥቅምት ላይ አካባቢውን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።
ይህንን ከማለታቸው ከአንድ ወር አስቀድሞ ሁቲዎች የባብ ኤል መንዳብ ወሽመጥ መነሻ ላይ የሚገኘው ፔሪም ደሴትን እንዲሁም ቁልፍ የወደብ ከተማ የሆነችው ሞካህን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካለው የየመን መንግሥት ጎን የተሰለፉት እና ሳዑዲ የምትደግፋቸው ኃይሎች ትናንት እሑድ እንዳሉት፤ ወታደሮቻቸው ከአካባቢው እየወጡ ነው።
ወታደሮቹ በሌላ ሥፍራ እንደሚሰማሩ እና ቅድሚያ የሚሰጡት ለኤደን ከተማ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የደቡባዊ ቀጣና ኃይሎችን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ወታደሮቹ “ከዱሀብ አውሮፕላን ማረፊያ እና ከባብ ኤል ምንዳብ አካባቢ” ለቅቀው ይወጣሉ።
ውሳኔው የተላለፈው “የጦር ግንባርን ለማጠናከር እና አሁን ላይ የተጋረጠን ስጋት ለመቀልበስ” ነው ብለዋል።
ሁቲዎች ዓለም አቀፉን የመርከቦች መተላለፊያ ሲቆጣጠሩ በአካባቢው ለሚደረግ እንቅስቃሴ ስጋት እንደማይሆኑ እና ሳዑዲ አረቢያን ዒላማ ማድረግ ግን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ተያያዥ ዜናዎች
የኅዳር 7 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል
የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የኅዳር 7 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።
የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።