ትራምፕ የሲአይኤ ኃላፊ በሩሲያ ካደረጉት ይፋዊ ያልሆነ ጉብኝት "አንዳች ነገር ሊመጣ ይችላል" አሉ

የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ኤጀንሲ (ሲአይኤ) ኃላፊ እና በሩሲያ የስለላ አገልግሎት ባለሥልጣናት መካከል ከተደረገው በይፋ ያልተገለጸ ውይይት "አንዳች ነገር ሊመጣ ይችላል" ብለው እንደሚጠብቁ ተናገሩ።

ማክሰኞ ዕለት የሲአይኤ ኃላፊው ጆን ራትክሊፍ በወታደራዊ አውሮፕላን ወደ ሞስኮ ስለተጓዙበት እና ከጥቂት ሰዓታት ቆይታ ስለተመለሱበት ምክንያት የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰጡ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዚህ ያልተለመደ ውይይት ላይ ምን ዓይነት ንግግር እንደተደረገ ይፋ አላደረጉም። ይሁን እንጂ ስብሰባውን "ከፊል መደበኛ" ሲሉ የገለጹት ትራምፕ፣ አሜሪካ "በዩክሬን ያለው ጦርነት ተቋጭቶ መመልከት ትፈልጋለች" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ውይይት የተካሄደው፣ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከመክፈቷ ጥቂት ወራት በፊት ነበር።

የሩሲያው ቤተ መንግሥት 'ክሬምሊን' ባለሥልጣናት የሲአይኤው ኃላፊ ራትክሊፍ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንዳልተገናኙ ገልጸዋል። የክሬምሊን ፕሬስ ሴክሬታሪ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "ከስለላ ተቋማት ጋር ግንኙነቶች ተደርገዋል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ጋር ስብሰባ አልተካሄደም። በዚህ ጉዳይ ላይ መናገር የምችለው ይህንን ብቻ ነው። ፕሬዝዳንት ፑቲን ወዲያውኑ ስለ ሁሉም ነገር ገለጻ ተደርጎላቸዋል" ሲሉም አክለዋል።

ከሲአይኤ ኃላፊው ጋር የተደረገው ንግግር ምን ላይ ያተኮረ እንደነበር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "ከተናገርኩት ውጭ የምጨምረው ነገር የለም" በማለት ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ረቡዕ ጥዋት ከወግ አጥባቂው የቶክ ሾው አቅራቢ ግሌን ቤክ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ውይይቱ ስለሚነሱ መላ ምቶች ተጠይቀዋል።

ትራምፕ ጉብኝቱን "ከፊል መደበኛ" በማለት ጠርተውታል። ፕሬዝዳንቱ "ሰዎችን ማሳዘን" እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ ነገር ግን ስለ ጉብኝቱ የሚሠራጩ መላምቶች በሙሉ ትክክል እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

የማክሰኞ ዕለቱ ስብሰባ የአሜሪካ እና የሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማስተካከል አስተዋጽኦ ይኖረው እንደሆነ ለመናገር ጊዜው እጅግ ገና መሆኑን ገልጸዋል።

"የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን አሁን ካለበት ጥልቅ ቀውስ ለማውጣት ምን ያህል ተፅዕኖ ያደርጋል የሚለውን ለመናገር ጊዜው ገና ነው" ብለዋል።

የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባዩ ቤስኮቭ በበኩላቸው በስለላ ተቋማት መካከል የሚደረጉ ግንኙነቶች "አዎንታዊ ክስተት፣ አዎንታዊ ሂደት" መሆናቸውን ተናግረዋል። ብዙውን ጊዜ ሁለቱ አገራት "እጅግ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥም ሆነውም እንኳ" እንዲህ ዓይነት ግንኙነቶች እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል።

ይህ ጉብኝት ከመደረጉ አስቀድሞ፣ አሜሪካ ከፍተኛ ልዑኳ ወደ ሞስኮ እንደሚጓዝ ለዩክሬን እንዳሳወቀች እንዲሁም፣ የስለላ አመራሮቹ ሩሲያን ለቅቀው እስኪወጡ ድረስ ጥቃት መፈጸም እንድታቆም መጠየቋን አንድ የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

የራትክሊፍን ጉብኝት በተመለከተ ከሲአይኤም ሆነ ከመከላከያ መሥሪያ ቤቱ 'ፔንታጎን' ይፋዊ አስተያየት አልተሰጠም።

ተንታኞች፣ ጉብኝቱ የተደረገው ሩሲያ በኔቶ አገራት ላይ የምታካሂደውን መደበኛ ያልሆነ የውጊያ ዘመቻ እንድታቆም በግልጽ ለማስጠንቀቅ ይሆናል የሚል ግምታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። የሩሲያ ባለሙያዎች ግን፣ ሞስኮ እንዲህ ዓይነቱን ማስጠንቀቂያ የመቀበሏ ነገር ግልፅ እንዳልሆነ አስረድተዋል።