በ9/11 ጥቃት ዋነኛ አቀነባባሪነት የሚጠረጠረው ግለሰብ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው

ካሊድ ሼክ መሐመድ በ1995 ዓ.ም. ቁጥጥር ስር እንደዋለ የተነሳው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, HO/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካሊድ ሼክ መሐመድ በ1995 ዓ.ም. ቁጥጥር ስር እንደዋለ የተነሳው ፎቶ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ መንግሥት "በዘመናዊ ታሪክ የአሜሪካ መሬት ላይ የተፈጸመ እጅግ አስከፊው የወንጀል ድርጊት" በሚል የሚገልጸው የ9/11 የሽብር ጥቃት ዋነኛ አቀነባባሪ በመሆን የሚጠረጠረው ካሊድ ሼክ መሐመድ፣ ክስተቱ ከተፈጸመ ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ በ2020 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው።

ጉዳዩን የሚመለከቱት ወታደራዊ ዳኛ የፍርድ ሂደቱ ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲሆን የወሰኑት፣ ዐቃብያነ ሕግ ችሎቱ በሚቀጥለው ዓመት እንዲጀመር ያቀረቡት የጊዜ ቀጠሮ እጅግ ቀርቧል በሚል ነው።

መሀመድ የሞት ቅጣት እንዳይፈረድበት ሲል ጥፋተኝነቱን ያመነበት ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት ላይ የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ስምምነቱን ውድቅ አድርጎታል።

ከ23 ዓመት በፊት በ1995 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋለው መሀመድ፣ ላለፉት 20 ዓመታት በአሜሪካው ጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ይገኛል።

ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2001 የተፈጸመውን "የ9/11 ኦፕሬሽን ከጅማሬው እስከ ፍጻሜው" የተካሄደበትን ዕቅድ ማዘጋጀቱን ተናግሮ ነበር።

የአሜሪካ አየር ኃይል ዳኛ ሌተናንት ኮሎኔል ማይክል ኤ. ሽራማ የመሀመድ እና የሌሎች ሦስት ተከሳሾች የየፍርድ ሂደት በሰኔ 2020 ዓ.ም. እንደሚጀምር ትናንት ረቡዕ አስታውቀዋል።

ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ዋሊድ ቢን አታሽ፣ አሊ አብዱል አዚዝ አሊ እና ሙስጠፋ አል ሀውሳዊ እንደሆኑ የክስ መዝገቡ ያሳያል።

የፍርድ ሂደቱ እስከሚጀምር ያለው ጊዜ የትኛዎቹ ማስረጃዎች ለችሎት መቅረብ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ላይ የሚነሱ ክርክሮችን መፍታትን ጨምሮ ተያያዥ የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ለመመልከት እንደሚውል ዳኛው ገልጸዋል።

በሚቀጥለው መስከረም ወር ላይ ይህ ጥቃት ከተፈጸመ 25 ዓመት ይሞላዋል።

በዚያ ዕለት ጠላፊዎች አውሮፕላኖችን በኒውዮርክ በሚገኘው 'ዎርልድ ትሬድ ሴንተር' እንዲሁም በቨርጂኒያ ባለው የመከላከያ መስሪያ ቤት 'ፔንታገን' ህንጻ ጋር አጋጭተዋል። ሌላ የተጠለፈ አውሮፕላን ፔንስልቬንያ ውስጥ ሜዳ ላይ ተከስክሷል።

በእነዚህ የሽብር ጥቃቶች 3,000 ገደማ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

መሀመድ የንግድ አውሮፕላኖችን ከሕንፃዎች ጋር የሚያጋጩ ፓይለቶችን የማሰልጠን ሀሳብን አመንጭቷል፤ እንዲሁም እቅዱን ለአል ቃኤዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን አቅርቧል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

አሜሪካ ውስጥ ምህንድስና ያጠናው መሀመድ በፓኪስታን ውስጥ ከአል ሀውሳዊ ጋር የተያዘው ጥቃቱ ሁለት ዓመት ሳይደፍን በመጋቢት 1995 ዓ.ም. ነበር።

በፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገው የክስ ስምምነት መሀመድ የሞት ቅጣት ሳይፈጸምበት ይቅርታ በማይሰጥበት የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ የሚያደርግ ነበር። እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰው ሁለት ዓመት ከፈጀ ድርድር በኋላ ነበር።

በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት ሎይድ ኦስቲን የተሾሙ ባለሥልጣንም ፊርማቸው አኑረውበት ነበር።

መከላከያ ሚኒስትሩ ኦስቲን ውሉ መፈረሙን ሲያውቁ መደንገጣቸውን እና ወዲያውኑ ለመሻር እንደሞከሩ ተገልጿል።

በጓንታናሞ ቤይ የሚገኘው ወታደራዊ እስር ቤት የተከፈተው ጥቃቱ ከተፈጸመ ከስድስት ወራት በኋላ ነው። አሁንም ድረስ 15 ገደማ እስረኞች ይገኙበታል።