ሰው የበላውን አዞ ለመያዝ በተካሄደው ዘመቻ ላይ የተሳተፈው የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አባል ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, Johan Potgieter
በደቡብ አፍሪካ በአዞ እንደተበላ የተጠረጠረን ግለሰብ አስከሬን ለማግኘት በተካሄደው ዘመቻ ወቅት በጉማሬ እና በአዞዎች ወደ ተሞላው ወንዝ በሂሊኮፕተር ያደረገውን ጉዞ ያስታውሳል።
ካፒቴን ጆሃን ፖትጌይተር በጎርፍ ከተወሰደ በኋላ በአዞ እንደተበላ የሚታመነውን ነጋዴ አስከሬን ለመፈለግ በተደረገው ዘመቻ ላይ ተመድቦ እየሠራ ነበር።
"አዞው በደሴቲቱ ላይ ተኝቶ ነበር. . . ከአየር ላይ ካልሆነ በስተቀር ማግኘት የሚቻልበት ዕድል አልነበረም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ግለሰቡን እንደበላ የታመነው አዞ ርዝመቱ 4.5 ሜትር ሲሆን ክብደቱ ደግሞ 500 ኪሎ ግራም ይመዝናል።
በፖሊስ ከተተኮሰበት በኋላ ተይዞ ሆድ እቃው ሲከፈት የሰው አስከሬን ተገኝቷል።
የግሰለቡን ማንነት ለመለየት የዲኤንኤ ምርመራ እየተደረገ ነው።
ነጋዴው የካማቲ ወንዝን ለማቋረጥ ሲሞክር አነስተኛ ድልድይ ላይ መኪናው መንቀሳቀስ ሳትችል በመቅረቷ በጎርፍ መወሰዷን የአካባቢው ፖሊስ ይናገራል።
ፖሊስ በስፍራው ሲደርስ መኪናው ባዶ የነበረ ሲሆን ይህም በጎርፍ ተወስዶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል።
የግለሰቡን አስከሬን ለመፈለግ ሂሊኮፕተሮች እና ድሮኖች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን በርካታ አዞዎች ፀሐይ የሚሞቁበት ደሴት መመልከታቸውን ተናገረዋል።
ከእነርሱ መካከል አንዱ ግለሰቡን እንደበላው የፖሊስ ባልደረቦቹ ግምታቸውን አሳድረዋል።
ነጋዴውን እንደበላ የተጠረጠረው አዞን ፖትጌይተር ከመድረሱ በፊት ባልደረቦች በጥይት መትተው ገድለውታል።
"በጥይት የተመታው አዞ የሞተ መስሎ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በሕይወት ነበር። ከዚያም ተንቀሳቅሶ ወደ ወንዙ መዋኘት ጀመረ። በሕይወት ነበር" ሲል ፖትጌይተር ለቢቢሲ አስረድቷል።
ወንዙ በአዞዎች እና በጉማሬዎች እንዲሁም በድንጋይ የተሞላ መሆኑ ጀልባ ተጠቅሞ የሟችን አስከሬን ማውጣት መሞከር አስቸጋሪ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
"ከአጠገቡ ሌሎች አዞዎች ነበሩ። ምናልባት ወንዙ በደም ስለተበከለ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እንደ ዕድል ሆኖ በሂሊኮፕተሩ ድምጽ በመሸሻቸው ምንም አላስቸገሩኝም" ሲል አስረድቷል።
ፖትጌይተር ግለሰቡን እንደበላ የተጠረጠረውን አዞ ይዞ ለማውጣት ከተስማማ በኋላ መመለስ የማይታሰብ ነበር።
"እዚያ ተንጠልጥዬ ሳለሁ ከአብራሪው ጋር የምነጋገርበት ዕድል አልነበረም፤ ድንገት እንኳ ሃሳቤን ቀይሬ ላለማውጣት ብወስን ያ ሊሆን የሚችልበት ዕደል አልነበረም" ሲል አክሏል።
"ዕቅዱ ላይ ማተኮር እና እንደተነጋገርነው ማድረግ ነው የነበረብኝ. . . አለበለዚያ ነገሮች ባልተፈለጉበት መንገድ ይሄዳሉ።"
እሁድ ዕለት የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ተጠባባቂ አዛዥ የግለሰቡን "የተለየ ብቃት" አድንቀው ዘመቻውን "በጣም አደገኛ እና ውስብስብ" ሲሉ ገልጸውታል።
የአገሪቱ ፖሊስ ለረዥም ዓመታት ያገለገለው ፖትጌይተር በሂሊኮፕተር እንዲወረድ ሲደረግ አዞው መሞቱን እርግጠኛ ሆኖ የነበረ ሲሆን በገመድ አስሮት ማውጣት ችሏል።
"100 ፐርሰንት እንደሞተ እርግጠኛ ሆንኩ። ምክንያቱም ያ ባይሆን ኖሮ ያጠቃኝ ነበር" ሲል አክሏል።
ፖትጌይተር ኒውስ24 ለተባለ የደቡብ አፍሪካ ሚዲያ በአዞው ሆድ ውስጥ ጫማዎች እና ሰው ስጋ መገኘቱን ተናግሯል። በአዞው ሆድ ውስጥ የተገኘው አስከሬን የማን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው።
ፖትጌይተር ላለፉት 38 ዓመታት የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ውስጥ ያገለገለ ቢሆንም ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት አደገኛ ተልዕኮ ላይ ተሳትፎ አያውቅም።
"ይህ የመጀመሪያዬ ነው፤ የመጨረሻዬም እንደሚሆን ተስፋ አለኝ. . . ወደ ኋላ ለመመለስ ምንም ዕድል አልነበረም።"
ቤተሰቡ ምንም እንኳን ቪዲዮውን በዜና ድረ ገጾች ላይ እስከሚያዩት ድረስ ምን ያህል አደገኛ እንደነበር ባያውቁም በሕይወት ተመልሶ በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጿል።
ፖትጌይተር ሥራው አደጋ ያለበት ቢሆንም የቤተሰብ አባላቸው የጠፉባቸው እና የሞተባቸውን ሲያስብ ግን አደጋውን እንደረሳው ተናግሯል።
"ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ሰዎች እጅግ የበዛ ሃዘኔታ አለኝ። የሚወዱትን አጥተው በሐዘን ውስጥ ናቸው። የሚወዱትን ማጣት እና በተለይ ደግሞ ምን እንዳጋጠመው፣ የት እንዳለ አለማወቅ የበለጠ ስሜቱ ከባድ ነው" ብሏል።
"እናም ዋናው የእኔ ገፊ ምክንያት እነዚህ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን እንዲወጡ መርዳት ነው።"














