ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ሰዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉበት ደረጃ" ላይ መደረሱን ኮነኑ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ "ሰዎች በነጻነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት ወደማይችሉበት ደረጃ" መደረሱን "አጠያያቂ፣ ጥዩፍ" እና "የማይገባ" ሲሉ ኮነኑ።

በታጣቂዎች ምክንያት የተፈጠሩ የእንቅስቃሴ መገደቦችን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚደረግ የመኪና ጉዞ "በኛ ጥረት መመለስ ይኖርበታል" ሲሉም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ያሉት ዛሬ እሑድ ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ንጉስ ተክለሀይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 25ተኛ የአገር ውስጥ መዳረሻ በሆነችው ደብረ ማርቆስ በተገነባው አውሮፕላን ማረፊያ የቅድመ ምረቃ በረራ አገልግሎት ያስጀመረው ከአንድ ወር በፊት ሰኔ 6 ቀን ነበር።

በዛሬው ይፋዊ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማዋ የሆነችውን ደብረ ማርቆስ ጥንታዊነት አንስተዋል። " 'አትመጣም ወይ ማርቆስ ከተድላው ከተማ፣ ቢሻህ በአውሮፕላን ቢሻህ በሎንቺና' የተባለላት ከተማ ናት" ሲሉም ገልጸዋታል።

"ባለፉት ጥቂት ዓመታት" ግን "ሎንቺናውም፣ አውሮፕላኑም ችግር ሆኖ ነበር" ሲሉ ወደ ከተማዋ የአውሮፕላን ጉዞ እንዳልነበረ እና የመኪና ጉዞ ላይ ተግዳሮት ማጋጠሙን ጠቅሰዋል።

"ዛሬ 'ቢሻህ በአውሮፕላን' ተመልሷል" ሲሉም በአየር ማረፊያ ሥራ መጀመር አንዱ ተግዳሮት መወገዱን ያነሱት ዐቢይ፤ " 'ቢሻህ በሎንቺና' ግን በኛ ጥረት መመለስ ይኖርበታል እላለሁ" ሲሉ የመኪና ጉዞ ላይ ያለው ችግር መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል።

ዐቢይ በዛሬው ንግግራቸው የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ላይ በተደጋጋሚ እገታ የሚፈጸምባትን በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደገም ወረዳ ውስጥ የምትገኘውን "አሊ ዶሮ" ቀበሌን አንስተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን 142 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘውን አሊ ዶሮን አልፈው ወደ አማራ ክልል የሚጓዙ ተሳፋሪዎች በተለያያ ጊዜ ለጅምላ እገታ እና ለግድያ ተዳርገዋል።

በእነዚህ እገታዎች እና ግድያዎች መንግሥት ሸኔ የሚለውና ራሱን የኦሮሚያ ነጻነት ሠራዊት የሚለው ታጣቂ ቡድን ይከሰሳል።

በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው ታጣቂ ቡድኑ ክሱን በተደጋጋሚ ያስተባበለ ሲሆን በምላሹ "መንግሥት ያደራጃቸው አካላት ድርጊቱን ይፈጽማሉ" ሲል ወንጅሏል።

መንግሥት ለዚህ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም በታጣቂዎቹ ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ሲገልጽ እንዲሁም ታጣቂዎቹ ለንግግር ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ባደረጉት ንግግር፤ "በአባይ ሸለቆ አካባቢ፣ አሊዶሮ አካባቢ የሸፈተውን እና ወደ አዲስ አበባ አላሻግርም ያለውን ሽፍታ በጋራ ታግለን ማስወገድ ሲገባን [ከደብረ ማርቆስ] ደጀን መሄድ እንዳንችል ተጨማሪ ሽፍቶች ማበራከታችን ተገቢ ጉዳይ አይመስለኝም" ብለዋል።

"የትም ቦታ ያለውን ሽፍታ ተሰናስለን፣ ተደማምረን በማስወገድ የሕዝባችንን ሰላምና ልማት ማረጋገጥ [አለብን]" ብለዋል። ከዚህ ተቃራኒ ግን "ሰዎች በነጻነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት ወደማይችሉበት ደረጃ" መደረሱ ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል።

"ጭራሽ ወደ ቀያችን፣ ወደ ሰፈራችን ሽፍቶች እየተበራከቱ፤ ሰዎች በነጻነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት ወደማይችሉበት ደረጃ መድረሳችን ለሁላችንም አጠያያቂ፣ ጥዩፍ፣ የማይገባ፣ ልንማርበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል" ሲሉ ኮንነዋል።

ዛሬ በይፋ የተመረቀው የደብረ ማርቆስ ከተማ "በቀን ሦስት ጊዜ" በረራ እንደሚደረግበት ዐቢይ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የበረራ አገልግሎቱ ቢኖርም ግን የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋን መክፈል የማይችሉ ሰዎች ሊቸገሩ እንደሚችሉም አንስተዋል።

"መክፈል የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ በትራንስፖርት ከዚህ ወደ ባሕር ዳር ወይም ከዚህ ወደ አዲስ አበባ መሄድ ቢፈልጉ፣ ያንን ማድረግ እንዲቻላቸው … ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ [ነው]" ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመገስን ጥሩነህ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የምስሉ መግለጫ, ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመገስን ጥሩነህ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው

ለዚህም ሲባል መንግሥታቸው "ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሊወያዩ፣ ሊነጋገሩ ለፈለጉ ማንኛውም አካል በራቸው ክፍት" መሆኑን ገልጸዋል።

"የማያግባቡን ጉዳዮች ካሉ በሰላማዊ፣ በሰለጠነ የፖለቲካ አግባብ መነጋገር ይቻላል። ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን አይጠቅምም፤ አማራን አይጠቅምም፤ ጎጃምን አይጠቅምም፤ ምሥራቅ ጎጃምን አይጠቅምም" ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን "ወቅታዊ ችግር ለመፍታት" እንዲቻልም ሕዝቡ እና መንግሥት "በጋራ እንዲቆም" ጥሪ አቅርበዋል።

ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት 2016 ዓ.ም. ክረምት ላይ የአማራ ክልል ግጭት ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ወደተለያዩ ሥፍራዎች የሚደረጉ ጉዞዎች ተስጓጉለዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች ባለፈው ሰኔ ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ የተካሄደበትን ጊዜ ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የትራንስፖርት እግዶችን ሲጥሉ ቆይተዋል። በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎችም እገታዎች አጋጥመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ክልሉ የሚደረጉ ጉዞዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የታጣቂዎች እገታ እና ጥቃት ዒላማ ሆነዋል።