የእስራኤል መሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ያወጡት የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ በወሲባዊ ክስ ከኃላፊነታቸው ተነሱ

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ ካሪም ኻን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በጋዛ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን ሲመረምሩ የነበሩት የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና ዐቃቤ ሕግ ካሪም ኻን፣ በቀረቡባቸው የወሲባዊ ጥፋት ውንጀላዎች ከኃላፊነታቸው ተነሱ።

በአውሮፓውያኑ 2021ፍርድ ቤቱ ሦስተኛ ዐቃቤ ሕግ ተደርገው የተመረጡት ኻን፣ ካለፈው ወር አንስቶ እግድ ላይ ነበሩ። ዐቃቤ ሕጉን ለማንሳት የተሰጠው ድምጽ በ82 ድጋፍ ጸድቋል።

የፍርድ ቤቱ ተቆጣጣሪ አካል ዐቃቤ ሕጉን የከሰሳቸው የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አዲስ ሠራተኛ ጋር ተገቢ ያልሆነ የወሲባዊ ግንኙነት ውስጥ ተሳትፈዋል እንዲሁም ሠራተኛዋ ያቀረበችውን አቤቱታ እንድታቆም ለማድረግ ሞክረዋል በሚል ነው።

በእነዚህን ድርጊቶች "ከባድ የኃላፊነት ጥሰት እና ከባድ የሥነ ምግባር ጥፋት" መፈጸማቸውን እንደደረሰበት ሰኔ ላይ አስታውቋል።

ኻን የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች እንዳልፈጸሙ በመግለጽ ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል። የአሁኑ ውሳኔን "ሕጋዊነት እና ፍትሐዊነት ባሉት ሕጋዊ መንገዶች በሙሉ" እንደሚሞግቱም ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕጉ የተላለፈባቸውን ውሳኔ በየትኛዎቹ ሕጋዊ መንገዶች መሞገት እንደሚችሉ እስካሁን ግልፅ አይደለም።

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከድምፅ መስጠት ሒደቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ኻንን ከኃላፊነት ለማንሳት 125 አባል አገራት ድምፅ በሰጡበት ልዩ ስብሰባ የተላለፈውን ውሳኔ "መገንዘቡን" ገልጿል።

"ፍርድ ቤቱ ለሁሉም ሠራተኞች ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ አካታች እና መከባበር ያለበት የሥራ ከባቢ እንዲኖር ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱት ይቀጥላል" ሲል አቋሙን አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዚህ ውሳኔ አጠቃላይ ሒደት ግን የአንድ ዐቃቤ ሕግን እጣ ፈንታ ከመወሰን የሚሻገር እና የዓለምን ብቸኛ ቋሚ የጦር ወንጀሎች ችሎት ቅርጽ ሊቀይር የሚችል ነው።

ይህ የሥነ ምግባር ጥሰት ምርመራ ተቋሙን ዐይን ውስጥ ከትቶታል፤ በውስጡ ያለውን ክፍፍልም አጠናክሮታል። የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ሙሉ በሙሉ ለማዳከም እና ለማፍረስ የሚካሄድ ከዚህ ቀደም ያልታየ ዘመቻም ተከፍቷል።

የፍርድ ቤቱ ደጋፊ አካላት ተቋሙ ይዳከማል እንዲሁም እጅግ ከባድ የዓለም ስጋቶችን ለመጋፈጥ የማይችል ይሆናል የሚል ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

ታዋቂው እንግሊዛዊ የሕግ ባለሙያ ኻን፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት አንስቶ የቀረቡባቸውን ክሶች ለመከላከል የሥራ ፈቃድ ላይ ነበሩ። የዩናይትድ ኪንግደም የጠበቆች የደረጃ ቦርድም በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን የራሱን ምርመራ እስከሚያጠናቅቅ ድረስ እገዳ ጥሎባቸዋል።

በተጨማሪም ኻን በፕሬዝዳንት ዶናልፕ ትራምፕ አስተዳደር ማዕቀብ ተጥሎባቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ስለተከለከሉ፤ በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዋና መሥሪያ ቤት በቀረበቸባው ክስ ላይ ድምፅ ሲሰጥ መገኘት አልቻሉም።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዐቃቤ ሕጉ ላይ ማዕቀብ የጣሉት፤ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ ፈጽመውታል የተባለውን የጦር ወንጀል በተመለከተ በሚያደርገው ምርመራ ምክንያት ነው።

ዐቃቤ ሕጉ ከኃላፊነታቸውን ቢነሱም ውዝግቡ እዚህ ጋር የሚያበቃ አይመስልም።

እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው እጅግ ስሱ የሆነ እና ፍርድ ቤቱን ለከፍተኛ ትችት የዳረገው ሒደት ታልፎ ነው። በፖለቲካዊ ውጥረቶች ምክንያትም ምርመራው ከፍተኛ ጫና ነበረበት።

ኻን በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው፣ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በጋዛ ጦርነት ፈጽመዋቸዋል በተባሉ ወንጀሎች የተነሳ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ከጠየቁ በኋላ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሜሪካ ለፍርድ ቤቱ ያላት ምልከታ የከፋ እየሆነ መጥቷል።

የትራምፕ አስተዳደር በዚህ ወር መጀመሪያ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን "ደረጃ በደረጃ" ለማፍረስ ያለመ "ሙሉ የመንግሥት" ዘመቻ ከፍቷል።

ፍርድ ቤቱን ለአሜሪካ ሉዓላዊነት ስጋት ሲል የሚጠራው የትራምፕ አስተዳደር፣ የቪዛ እና ንብረት እገዳዎችን እንደሚጥል ገልጿል።

አጋር አገራት ከፍርድ ቤቱ አባልነት እንዲወጡ ወይም በዜጎቻቸው ላይ የሚኖረውን ሥልጣን ውድቅ እንዲያደርጉ ለማስገደድ ጫና እንደሚያደርግም አስታውቋል።