በፈረንሳይ የፒኤስጂ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልጹ ባስነሱት ሁከት ከ400 በላይ ሰዎች ታሰሩ

የፒኤስጂ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፒኤስጂ ቻምፒዮንስ ሊግን ማሸነፉን ተከትሎ በመላው ፈረንሳይ ደጋፊዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ከ400 በላይ ሰዎች ታሰሩ።

የፒኤስጂ ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተው ያስነሱትን ሁከት ለመቆጣጠር በፓሪስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ተሰማርተዋል። ደጋፊዎቹ የአውቶብስ እና ባቡር እንቅስቃሴን አስተጓጉለዋል።

በየአካባቢው በበተኮሰ ርችት እና ሌሎችም ተቀጣጣዮች ሳቢያ ፖሊሶች መጎዳታቸው ተገልጿል። ፖሊሶችም አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ሰዎችን ከከተማው ማዕከል ለመበተን ሞክረዋል።

አምና ፒኤስጂ ቻምፒዮንስ ሊግን ሲያሸንፍም ተመሳሳይ ሁከት ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል።

በፓሪስ የተቀረጹ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ተቀጣጣዮች ሲተኮሱ፣ የኤሌክትሪክ ሳይክሎች አውራ ጎዳና ላይ ሲቃጠሉ እና አንድ ሱቅ መስታወቱ ሲሰበር ያሳያሉ።

ፒኤስጂ እና አርሰናል በመደበኛው የጨዋታ ሰዓት አንድ አቻ ወጥተዋል። በተጨማሪ ሰዓት ምንም ጎል ስላልተቆጠረ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት አምርተዋል።

ፒኤስጂ ባሸነፈበት ቅጽበት ደጋፊዎቹ የሾንዛ ሊዜ መንገድን ከጥግ እስከ ጥግ ሞልተዋል።

የፒኤስጂ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በፒኤስጂ ስቴድየም ፓርክ ደስ ፕሪንሰስ ግጥሚያውን ለመመልከት የተሰባሰቡ ደጋፊዎች እና ፖሊሶች ተጋጭተው ነበር።

ስድስት ተሽከርካሪዎች፣ ሁለት የንግድ ሥፍራዎች እና አንድ የአውቶብስ ማቆሚያ ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳለው 416 ሰዎች ታስረዋል። ከእነዚህ መካከል 280 የሚሆኑን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ፓሪስ ውስጥ ነው።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ላውረንት ኑኔዝ እንዳሉት ሰባት ፖሊሶች ተጎድተዋል። ሚኒስትሩ ሁከቱ "ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው" ብለዋል።

አክራሪ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ ማሪ ላ ፔን "የእግር ኳስ ክለብ ድል ነውጥ የሚያስነሳው በፈረንሳይ ብቻ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

"ሰዎች ላለመጎዳት ሲሉ ከቤት የማይወጡት ፈረንሳይ ውስጥ ብቻ ነው" በማለትም አክለዋል።

የፒኤስጂ ተጫዋቾች ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ደስታውን ከደጋፊዎቻቸው ጋር ይጋራሉ። በአይፍል ታወር አጠገብ ያለውን ቻምፕ ደ-ማርስ ከዞሩ በኋላ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አቀባበል ያደርጉላቸዋል።

አምና ፒኤስጂ ሲያሸንፍ በተነሳው ሁከት ሳቢያ የ17 ዓመት ወጣትን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ሞተዋል።