ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "ምክክሩን ለማስጀመር እክል" ገጥሞታል መባሉን አስተባበለ

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከአራት ዓመት ሂደት በኋላ ረቡዕ ዕለት የመጨረሻውን ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ያካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ባለፉት ቀናት ውስጥ "ምክክሩን ለማስጀመር እክል" ገጥሞታል መባሉን አስተባበለ።

ባለፉት ሦስት ቀናት ለአራት ሺህዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎች ስለ ሒደቱ ገለጻዎችን መሰጠቱን እና ከነገ ሰኞ አንስቶ "መቶ በመቶ" ወደ ሥራ እንደሚገባ ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሥልጣናት በተገኙበት የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፤ ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ሊወስድ የሚችል ሂደት እንደሆነ ተገልጿል። የዚህ ጉባኤ ተሳታፊ የሆኑት 4,000 ተመካካሪዎች፤ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረጋቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ።

ረቡዕ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. ዕለት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ከተካሄደ በኋላ በነበሩት ቀናት ምክክሩ አለመጀመሩ ከተዘገበ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል።

የተመረጡት አጀንዳዎች ላይ ምክክር የሚካሄድበት መንገድ ተሳታፊዎች ባለማግባባቱ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች ምክክሩን ለማስጀመር አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን የሚገልጹ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ታይተዋል።

ምክክሩ የሚካሄደው፤ በስምንት ቡድኖች የሚከፋፈሉት ተሳታፊዎች እያንዳንዳቸው በእጣ የሚደርሳቸውን አጀንዳ ከያዙ በኋላ ነው።

ቀጥሎም የእያንዳንዱ ቡድን ተወካዮች በጋራ በተሰጧቸው አጀንዳዎች ላይ የደረሰቡባቸውን ድምዳሜዎች ይመካከራሉ። በመጨረሻም አራት ሺህዎቹ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ጉባኤ ይደረጋል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ እሁድ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በዚህ ሒደት ላይ የተፈጠረው ቅሬታ ምክክር እንዳይጀር አድርጓል የሚለውን መረጃ አስተባብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"አንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኮሚሽኑ ምክክሩን ለመጀመር እክል እንደገጠመው የተሳሳተ መረጃ ሲያሰራጩ ተመልክተናል" ብሏል።

ኮሚሽኑ፤ "አንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች በማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች አማካኝነት" ምክክሩን በተመለከተ "ከእውነታ የራቁ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን እንደደረሰበት" አስታውቋል። "የራሳቸው ዓላማ ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች" የሚደረግ ይህ ዓይነት "የተሳሳቱ መረጃዎች" ስርጭቶች "ተጠናክረው ሊቀጥሉ" እንደሚችሉም አስጠንቅቋል።

የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ከተካሄደበት ረቡዕ ዕለት አንስቶ ተሳታፊዎች "ለሒደቱ ጠቃሚ የሆኑ የእውቀት እና የሥነ-ልቦና ዝግጅቶች እንዲያደርጉ" ማድረጉን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ይህ ሂደት "የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አንድ አካል" መሆኑን አስረድቷል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን፤ ትናንት ጉባኤው ከሚካሄድበት አዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም፤ ባለፊት ቀናት ተሳታፊዎች አጀንዳዎች እንዲከፋፈሉ መደረጉን ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹ "ስምንት ቦታ ላይ ተከፋፍለው፤ እያንዳንዳቸው በተሰጣቸው አጀንዳ ላይ፣ ከእነ ንዑሳን ርዕሶች ጨምሮ ዝርዝር የሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተደርጓል" ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ በዚህ ሒደት ውስጥ "ቀላል" ሲሉ የገለጿቸው "አንዳንድ ችግሮች" ማጋጠማቸውን አንስተዋል። "ለምሳሌ [የተሳታፊዎች መግቢያ] ባጅ ስናድል ብዙ ሰዎች በርካታ ሰዎች መጨረሻ ላይ ፍላጎት አሳይተዋል" ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ከዚህ ቀደም በሒደቱ ውስጥ ያልነበሩ "ፖለቲካ ፓርቲዎች መጥተዋል፤ በጣም ደስ ብሎናል" ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፤ ከነገ ሰኞ ሐምሌ 13 ጀምሮ "ሙሉ በሙሉ ከጠዋት እስከ ማታ ሥራዎቻችንን በየቦታው ተከፋፍለን የምንሠራበት ጊዜ መቶ በመቶ ይጀምራል" ብለዋል።

"ከሰኞ ጀምሮ እንግዲህ ሁላቸውም የተሰጣቸውን ሀገራዊ አደራ በትክክል የሚወጡበትን መድረክ ሂደቱን መቶ መቶ ይገቡበታል ማለት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።