ቻትጂፒቲ ሱስ በማስያዝ እና ራስን ማጥፋትን በማበረታታት ተከሰሰ

የኦፕንኤአይ ኃላፊ ሳም አልትማን

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg

የምስሉ መግለጫ, የኦፕንኤአይ ኃላፊ ሳም አልትማን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቻትጂፒቲ የተሠራበት መንገድ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም በሚል ፍሎሪዳ በኦፕንኤአይ ላይ ክስ መሠረተች።

ኦፕንኤአይ የሠራው ቻትጂፒቲ ልጆችን ለአደጋ በማጋለጥ እንዲሁም ሱስ በማስያዝ፣ የጅምላ ተኩስ አድራሾችን በመደገፍ ፣ በማበረታታት እና ተጠቃሚዎቹ ራሳቸውን እንዲያጠፉ በመገፋፋት ተከስሷል።

ፍሎሪዳ ቻትጂፒቲን በመክሰስ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ግዛት ናት። ዐቃቤ ሕግ ጄምስ ኡትሜር ክሱን ያቀረቡት በኦፕንኤአይ እና በኩባንያው ኃላፊ ሳም አልትማን ላይ ነው።

ኦፕንኤአይ ለክሱ በሰጠው ምላሽ "በኢንዱስትሪው አሉ የተባሉ የደኅንነት ጥበቃ ፖሊሲዎችን እየተገበርን ነው" ብሏል።

ባለፈው ዓመት በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ የጅምላ ተኩስ ተከፍቶ ሁለት ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ቻትጂፒቲ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳደረገ ግዛቱ ምርመራ ከፍቷል።

የቀረበው ክስ ሳም አልትማንን " ሆነ ብሎ ችላ በማለት" በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። በክሱ ላይ "የተቋሙ ድርጊት በሰዎች ላይ የጋረጠውን አደጋ ፈጽሞ ከግምት አላስገባም።" ተብሏል።

ኦፕንኤአይ አሳሳች እና ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ መንገድ በመከተል፣ በቸልተኛነት፣ የተጠያቂነት ሕግን በመጣስ፣ ራሱን በተዛባ መንገድ በማስተዋወቅ እና ሕዝብን በማወክ ተከስሷል።

ዐቃቤ ሕጉ "ሳም አልትማን እና ቻትጂፒቲ ከልጆች ደኅንነት ይልቅ የኤአይ እሽቅድድምን አስበልጠዋል። ከሕዝብ ደኅንነት በላይ ትርፋማነትን አስቀድመዋል። ፍሎሪዳ ይሄንን አትቀበልም። ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኦፕንኤአይ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "አንድ ቤተሰብ ሊገጥመው ከሚችለው የከፋ ነገር ሁሉ ልጅን ማጣት እጅግ ከባዱ ነው። ምን ያህል እንደሚጎዳም በቃላት መግለጽ አንችልም" ብሏል።

"ኤአይ አዲስ እና ኃያል ቴክኖሎጂ ነው። ታዳጊዎች ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው እናምናለን። በዘርፉ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን የምንተገብረውም ለዚህ ነው" ሲልም አክሏል።

የኦፕንኤአይ መተግበሪያዎች የልጆችን ደኅንነት ያማከሉ መሆናቸውን ኩባንያዊ ገልጿል። ከእነዚህ መካከል የልጆችን ዕድሜ መለያ መንገድ እና ወላጆች ቁጥጥር እንዲያደርጉ የተዘረጋውን አሠራር ይጠቅሳል።

የኦፕንኤአይ ቃል አቀባይ "ስለ አሠራራችን ማውራታቸውን የሞተን ልጅ እንደማይመልስ እናውቃለን። ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ግን ቁርጠኛ ነን" ብለዋል።

ቻትጂፒቲ ሰዎች እንዴት ራሳቸውን ማጥፋት እንደሚችሉ እየነገረ በማገዝ ክሶች ቀርበውበታል።

በያዝነው ዓመት ካናዳ የጅምላ ተኩስ ተከፍቶ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎችም ኦፕንኤአይን ከስሰዋል። ኩባንያው የተከሰሰው መረጃውን ለባለሥልጣኖች ባለማቀበሉ ነው።

ኦፕንኤአይ ለፖሊስ ጥቆማ ባለመስጠቱ ይቅርታ ጠይቋል። አንድ የመተግበሪያው ተጠቃሚ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ሲል ኩባንያው እርምጃ የሚወስድበት አሠራር ቢኖረውም፤ ተኩስ የከፈተው ሰው አካውንት በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተተ ገልጿል።

ከኦፕንኤአይ በተጨማሪ ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋማትም እየተከሰሱ ነው።

አንድ በፍሎሪዳ የሚኖር አባት፤ ልጁ ራሱን እንዲያጠፋ ኤአይ እንዳነሳሳው በመግለጽ ጉግልን ከስሷል።

ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ፣ ስናፕ ኢንክ፣ ቲክቶክ እና ጉግል የሚያስተዳድረው ዩቲዩብ በርካታ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

መተግበሪያቸው ሱስ እንዲያስይዝ ማድረጋቸው ከክሶቹ መካከል ይጠቀሳል።

ከሁለት ወር በፊት ሜታ እና ጉግል ሱስ በማስያዝ በ20 ዓመት ታዳጊ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለዋል።

ጥፋተኛ መባላቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለረዥም ጊዜ ከተጠያቂነት ያመልጡበት የነበረውን አካሄድ የቀለበሰ ነው ተብሏል።