የናይጄሪያ የቀድሞ ጄነራል እና ባለቤታቸው በታጣቂዎች ታገቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ የቀድሞ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን እና ባለቤታቸው በታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ።
ሜጀር ጄነራል ራቤ አቡባካር እአአ ከ2015 እስከ 2017 የናይጄሪያ መከላከያ ቃል አቀባይ የነበሩ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ካትሲና ግዛት ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እየሄዱ ባለበት ወቅት መታገታቸው ተገልጿል።
የናይጄሪያ ጦር ቃል አቀባይ ጄነራል ማይክል ኦኖጃ ለቢቢሲ ታጋቾቹን ለማስለቀቀ እና አጋቾቻቸውን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቀድሞ ጄነራሉ መታገት አሁንም በሰሜናዊ ምዕራብ ናይጄሪያ ያለውን የደህንንት ስጋት የሚያሳይ ነው ተብሏል።
በአካባቢው "ሽፍቶች" ተብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች ሰዎችን በማገት ገንዘብ የሚጠይቁ ሲሆን፣ ከብቶችን በመዝረፍ እና በገጠር በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ይታወቃሉ።
በአካባቢው ሌሎች ታጣቂ ጂሃዲስቶች ይንቀሳቀሳሉ።
በሶኮቶ ግዛት የሚገኝ የታጣቂዎች ካምፕ ላይ በታሕሳስ 25 የአሜሪካ ጦር ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።
ታጣቂዎች በተደጋጋሚ እገታዎች እና ግድያዎች ከሚፈጽሙባቸው ግዛቶች መካከል ካትሲና አንዱ ነው።
ከካትሲና እና ሶኮቶ ጋር በሚጎራበተው ዛምፋራ ግዛት የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከዚህ ቀደም ከታጣቂዎች ጋር ሰላም ለማውረድ ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም በዘላቂነት መቀጠል አልቻለም።
መንግሥት የሚፈጸሙ እገታዎችን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን የታገቱትን ለማስለቀቅ ገንዘብ መክፈልንም ሕገ ወጥ አድርጓል።
ቅዳሜ ዕለት የታገቱትን የቀድሞ ጄነራል በሚመለከት ኃላፊነት የወሰደ ቡድን የለም። ጦሩ እንደተናገረው የአጋቾቹን ማንነት ለማወቅ ከቤተሰቡ ጋር ግንኙነት እስኪመሠርቱ ድረስ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጡረታ የወጡት ጄነራል አጋቾቹ ሲይዟቸው ሰርግ ላይ ለመታደም እየሄዱ ነበር ሲሉ ዘግበዋል።
የአቡባካር ሹፌር በታጋቾቹ በተተኮሰበት ጥይት የተመታ ቢሆንም ማምለጡ የተገለጸ ሲሆን የቀድሞው ጄነራል እና ባለቤታቸው ግን በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጫካ ተወስደዋል።
እገታው የተፈጸመው በካትሲና ሌላ ጥቃት ከተፈጸመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
አርብ ዕለት ታጣቂዎች ዱትሲንማ አካባቢ ኪሊያ መንደር ላይ ጥቃት ፈጽመው 16 ሰዎች መግደላቸው ተዘግቧል።
ፖሊስ ተፈጸመ በተባለው ግድያ ዙሪያ ያለው ምንም ነገር የለም።
የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ የተፈጸመው ከአርብ ጸሎት በኋላ ሰዎች ለኢድ አል አድሃ በዓል በተሰባሰቡበት መሆኑን ተናግረዋል።
የአገሪቱ የጸጥታ ባለሥልጣናት በበዓሉ ሰሞን ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር። በዚህም የተነሳ የአካባቢ አስተዳደሮች በአንድ ስፍራ የሚሰበሰቡ ሰዎችን ቁጥር እንዲቀንሱ እና የጸጥታ ቁጥጥሩን እንዲያጠናክሩ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
- 10















