ትራምፕ "ምርጫው ተጭበርብሯል" ላሉት ማስረጃ ሲጠየቁ በድንገት ቃለ ምልልስ አቋረጠው ወጡ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከኤንቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት በተደጋጋሚ ለሚያነሷቸው 'የምርጫው ተጭበርበብሯል' ሃሳብ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ በድንገት አቋርጠው ወጡ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት በተላለፈው የኤንቢሲ 'ሚት ዘ ፕሬስ' በተሰኘው ቃለ ምልልስ አሁን በካሊፎርኒያ የተካሄደው እና እአአ በ2020 የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ "የተጭበረበረ" መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ለማለት ያበቃቸው ምን እደሆነ እና ማስረጃ ካላቸው ሲጠየቁ "ማድረግ ያለብኝ ነገር ቢኖር ማየት እና ማዳመጥ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

ጠያቂዋ "ይህ ማስረጃ ሊሆን አይችልም" ስትላቸው የመገናኛ ብዙኃኑን "አጭበርባሪ" ሲሉ ዘልፈው ቃለ ምልልሱን ከማብቃታቸው በፊት "ይቅርታ እዚህ ላይ ይብቃን ምክንያቱም በቅቶኛል" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለእርሳቸው አሉታዊ አመለካከት አላቸው ከሚሏቸው መገናኛ ብዙኃን ጋር ያላቸው ግንኙነት የሻከረ ነው።

ቃለ መጠይቁ የተካሄደው ዶናልድ ትራምፕ በዊስኮንሲን በሚገኙ ገበሬዎች በዓል ላይ በተገኙበት ወቅት ነበር።

በአንድ የከብት እርባታ ውስጥ የተካሄደው ቃለ ምልልስ በቴክኒክ ጉዳዮች እና በዕለቱ ይጥል በነበረው ዝናብ የተነሳ በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ነበር።

ኤንቢሲ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አርብ ዕለት ለቃለ መጠይቅ ከተቀመጡ ከ50 ደቂቃ በኋላ ማቋረጣቸውን ጨምሮ ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቴሌቪዥን ጣቢያው የተላለፈው አብዛኛው ቃለ መጠይቅ የሚያተኩረው ከኢራን ገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ነው።

ትራምፕ አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ እርምጃ መውሰዷን በመግለጽ "መጨረሻ የሌለው ጦርነት" አይደለም ሲሉ ተሟግተዋል።

"እዚያ ያለነው ለጥቂት ወራት ነው፤ አብዛኛው ስጋት ተወግዷል" ሲሉ መልሰዋል።

ቃለ መጠይቁን ከማቋረጣቸው ስድስት ደቂቃ ቀደም ብሎ የትራምፕ አስተዳደር መንግሥት ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ዒላማ አድርጎናል ወይንም ምርመራ አድርጎብናል ለሚሉ ግለሰቦች ካሳ ለመፈል አዘጋጅቶት የነበረውን የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ላይ እየተነጋገሩ ነበር።

ዕቅዱ ከዲሞክራቶች እና ከሪፐብሊካን ትችትን ያስከተለ ሲሆን እንዲሰረዝ ተደርጓል።

ከዚያ በኋላ ቃለ መጠይቁ ትራምፕ እአአ በ2020 የተካሄደው ምርጫ የተጭበረበረ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ በመናገራቸው ላይ አተኩሯል።

ዶናልድ ትራምፕ ውይይቱን በካሊፎርኒያ የግዛቱን አስተዳዳሪ እና የፓርቲውን ተወካይ ለመምረጥ ስለተሰጠው ድምጽ እና አሸናፊውን ለመለየት ቆጠራ እየተደረገ ስላለበት ምርጫ ቀይረውታል።

ቆጠራው መካሄድ ከጀመረ አራት ቀን ቢሆነውም እስካሁን አሸናፊው አለመገለጹን በመጥቀስ "በምርጫው አጭበርብረዋል' ሲል ወንጅለዋል።

ጋዜጠኛዋ "ማስረጃ አለዎት" ስትላቸው "ማድረግ ያለብኝ መመልከት እና ማዳመጥ ብቻ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጋዜጠኛዋ አክላም "ያ ግን ማስረጃ አይሆንም" ስትል መልሳለች።

በአሜሪካ ምርጫ ቆጠራ ወቅት ውጤት የሚገለጽበት ቀን መዘግየት የተለመደ ነው። ፕሬዚዳንት ትራምፕ አክለውም "አጭበርባሪዎች ናቸው፤ ልክ አንቺ አጭበርባሪ እንደሆንሽው" ሲሉ ጋዜጠኛዋን ዘልፈዋል።

ጋዜጠኛዋ "እውነቱን ለመናገር እኔ እንደዚያ አይደለሁም፤ ግን እንቀጥል" ስትል መልሳለች።

ትራምፕ "ወይ ሸፍጠኛ ነሽ አልያም ደደብ ነሽ" ካሉ ቧኀላ "እዚህ ላይ ይብቃን ምንያቱም በቅቶኛል፤ አመሰግናለሁ የኔ ውድ! መልካም ጊዜ።"

ጋዜጠኛዋ ቃለ ምልልሱን ለመቀጠል ብትሞክርም ትራምፐ አቋርጠዋት "በዚህ በዝናብ ካንቺ ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል ተቀምጫለሁ። በዝናቡ የተነሳ አንዴ ሲቋረጥ አንዴ ስንቀጥል ቆይተናል። በቂ ጊዜ ሰጥቼሻለሁ። ፕሬሱን ልታስተካክሉ ይገባል። ምክንያቱም ታውቂያለሽ አንድ አገር ታማኝ ባልሆነ ፕሬስ ታላቅ ልትሆን አትችልም" ሲሉ ተናግረዋል።

ከካሜራው ጀርባ ያሉትን ሰዎች "እንሂድ፤ ካሉ በኋላ ቃለ መጠይቁን አቋርጠው ወጥተዋል።

ቃለ መጠይቁ ከተላለፈ በኋላ ጋዜጠኛዋ በወቅት በዝናብ ምክንዓት በተደጋጋሚ መቋረጥ አጋጥሞ እንደነበር በመግለጽ ለሌላ ቃለ ምልልስ ዳግመኛ ለመገናኘት ፕሬዚዳንቱ መስማማታቸውን ተናግራለች።

ቢቢሲ ዋይት ሐውስ በቃለ ምልልሱ ዙሪያ አስተያየቱን እንዲሰጥ ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።