ጋናዊው ቶማስ ፓርቲይ ለዓለም ዋንጫ ካናዳ እንዳይገባ ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋናዊው የመካከለኛ መስመር ተጨዋች ቶማስ ፓርቲይ ካናዳ ለመግባት መከልከሉን ተከትሎ አገሩ ከፓናማ ጋር የምታደርገው የመክፈቻ ጨዋታ ላይ አይሳተፍም።
የ32 ዓመቱ ተጨዋች እ.አ.አ ከ2020 እስከ 2022 ድረስ በአራት ሴቶች ሰባት የአስገድዶ መድፈር እና አንድ ከወሲባዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ክሶች ቀርበውበታል።
ተጨዋቹ በሚቀጥለው ዓመት ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሲሆን፤ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።
ፊፋ ባወጣው መግለጫ የቀድሞው የአርሰናል ተጨዋች እና የአሁኑ የስፔኑ ቪሪየል ተጨዋች የጋና ቡድን ስልጠና ማዕከል ከነበረው ቦስተን ወደ ካናዳ ለመግባት የቪዛ ማመልከቻው በካናዳ መንግሥት ውድቅ እንደተደረገበት አረጋግጧል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ መሪ ድርጅት "ፊፋ የቪዛ አሰጣጥን ጨምሮ በአስተናጋጅ አገራት የኢሚግሬሽን ሂደት ተሳትፎ የለውም።
"የአስተናጋጅ አገሩ መንግሥት ማን ቪዛ ማግኘት እንዳለበት እና ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ማን እንደሚፈቀድለት የመጨረሻውን ውሳኔ ይወስናል" ሲል አክሏል።
በካናዳ መንግሥት ድረ ገፅ የጉብኝት ሕግ ዝርዝር ላይ "ወንጀል ሰርተው ወይንም በወንጀል ፍርድ ተሰጥቶብዎ ከሆነ ወደ ካናዳ መግባት ላይፈቀድልዎ ይችላል" ይላል።
ቶማስ ፓርቲይ ሁሉንም የቀረቡበትን ክሶች ጥፋተኛ አለመሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ እስካሁንም የጥፋተኝነት ብይን ሳይሰጠው የፍርድ ቤት ቀጠሮውን እየተጠባበቀ ነው።
የካናዳ የኢምግሬሽን፣ ስደተኞች እና ዜግነት ቢሮ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ "ካናዳ የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ በማስተናገዷ ኩራት ይሰማታል። የካናዳዊያንን ደኅንነት እና ፀጥታ በመጠበቅ የተሳካ ሁነት ለማዘጋጀት እየሰራች ነው።
"ካናዳ ትላልቅ ሁነቶችን ማዘጋጀት የካናዳን የኢምግሬሽን ሕጎች አይቀይርም የሚል ፅኑ አቋም አላት" ብሏል።
"ወደ ካናዳ የሚመጣ ማንኛውም ሰው በግለሰብ ደረጃ ይመዘናል፤ ይህም ባሉ እውነታቸው እና በሚተገበሩ ሕጎች ተመስርቶ ነው" ሲል መግለጫው አክሏል።
የአሜሪካ የጉሙሩክ እና ድንበር ጥበቃ ቢሮ በበኩሉ አሜሪካ የፓርቲይ የፍርድ ቤት ጉዳይን እንደምታውቅ፤ ነገር ግን በዚህ ጊዜ በወንጀል ብይን ስላልተሰጠው ወደ አሜሪካ እንዲገባ መደረጉን ገልጿል።
ቢሮው አክሎም አገር ውስጥ ለመግባት ማመልከቻ የሚያቀርቡ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የሕግ አስከባሪዎች በሚያደርጉት ምርመራ መሠረት ነው ብሏል።
ቢቢሲ ስፖርት የጋና እግር ኳስ ማህበር አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።
ከውድድሩ አስቀድሞ የጋና ዋና አሰልጣኝ ካርሎስ ኪሮዝ ተጨዋቹን ለመምረጥ ምንም ጥርጣሬ አልነበረኝም ብለዋል።
"ተጨዋቹ ከእኔ ጋር እዚህ ከሆነ መልሴ ግልፅ ነው" ብለዋል።
ጋና በምድቧ ሁለተኛው ጨዋታዋን ከእንግሊዝ ጋር በቦስተን ስታዲየም የምታደርግ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በፊሎዶልፊያ ክሮሺያን ታስተናግዳለች።
በሁለቱም ጨዋታዎች ቶማስ ፓርቲይ መሳተፍ ይችላል።















