የአውሮፓ አገራት የወርቅ ክምችታቸውን ከአሜሪካ እና ከካናዳ እያስወጡ ያሉት ለምንድን ነው?

ወርቅ ክምችት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በዚህ ሳምንት ከሰሜን አሜሪካ በቶኖች የሚቆጠር ከፍተኛ የወርቅ ክምችቱን ማስወጣቱን ያረጋገጠው የኔዘርላንድስ ማዕከላዊ ባንክ፣ ይህንን እርምጃ የወሰደው ከባድ ቀውሶች በሚከሰቱበት ጊዜ "የተሻለ ተዘጋጅቶ ለመጠብቅ" መሆኑን ገልጿል።

በአሜሪካ እና ካናዳ ከሚገኘው የኔዘርላንድስ በድምሩ 313 ቶን የሆነ የወርቅ ክምችት ውስጥ 86 ቶኑ ወደ ለንደን ተዘዋውሯል። ባንኩ እንደገለጸው፣ ይህ የተደረገው "በዓለም የፖለቲካ ውጥረት መጨመርን ከግምት ውስጥ በማስገባት" ሲሆን፣ ከአሜሪካ እንዲወጣ የተደረገው ወርቅም "ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ በፍጥነት ለመጠቀም አመቺ እንዲሆን" ነው ተብሏል።

ነገር ግን እርምጃው ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል። የኔዘርላንድስ መንግሥት ይህን ለምን አደረገ? በቅርቡ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰታል ብሎ እየጠበቀ ነውን?

ምናልባት ምክንያቶቹ እነዚህ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም እርምጃው የተወሰደው ዓለም ባለችበት ያልተረጋጋ እና ለመተንበይ አስቸጋሪ በሆነው ሁኔታ ምክንያት መሆኑ ግልጽ ነው። የንግድ ግጭቶች እና ጦርነቶች አገራትን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲወስዱ እና ወርቃቸውን በአቅራቢያቸው እንዲያስቀምጡ ምክንያት እየሆኑ ነው።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ፈረንሳይ የወርቅ ክምችቷን ከአሜሪካ ወደ አገሯ መመለሷን አስታውቃለች። በሌላ በኩል የጀርመን ማዕከላዊ ባንክ እስከ አውሮፓውያኑ 2016 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ 216 ቶን በላይ ወርቅ ከውጭ የማከማቻ ቦታዎች ወደ አገሩ አስመልሷል። ከዚህ ውስጥ 111 ቶኑ ከኒው ዮርክ እና 105 ቶኑ ከፓሪስ እንዲወጡ የተደረጉ ናቸው።

እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት በተከሰቱባቸው ወቅቶች ከዚህ ቀደምም ተተግብሯል። "በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አንዳንድ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንኮች የወርቅ ክምችታቸውን ከፊሉን ወደ ኒው ዮርክ አሻግረው ነበር" ሲሉ የጎልድማን ሳክስ ተንታኞች ሊና ቶማስ እና ዳን ስትሩይቨን ገልጸዋል።

የዓለም የወርቅ ምክር ቤት ከፍተኛ የገበያ ስትራቴጂስት ጆሴፍ ካቫቶኒ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ጦርነቶች እና የንግድ ውጥረቶች "በእነዚህ ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ ቢያሳድሩም" ዋነኛ ምክንያቶች አይደሉም።

የዋጋ ግሽበት፣ የወለድ መጠን እና ወርቅ በፍጥነት በሚገበያይበት ቦታ ማስቀመጥም ወርቅን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ለማስቀመጥ ለሚደረሰው ውሳኔ ላይ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ታላቅ አደጋ ወይም ጥፋት በቅርብ ጊዜ ይመጣል የሚል ስሜት የለኝም" ሲሉ ካቫቶኒ ተናግረዋል። "ነገር ግን አገራት የመጠባበቂያ ሀብታቸውን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ፣ እንዴት እንደሚያሳድጉ እና ከእዚህ ሀብታቸው ከፍተኛ ጥቅም እንዴት እንደሚያገኙ በበለጠ እየሠሩ ነው" ብለዋል።

የኔዘርላንድስ ማዕከላዊ ባንክ እንደገለጸው፣ በዚህ ዓመት ከመጋቢት እስከ ነሐሴ ድረስ ከአሜሪካ እና ከካናዳ ወደ አውሮፓ የተዛወረው ወርቅ አሁን በእንግሊዝ ባንክ (ባንክ ኦፍ ኢንግላንድ) የወርቅ ማከማቻ ቦታዎች ውስጥ ተቀምጧል።

የኔዘርላንድስ ማዕከላዊ ባንክ ኃላፊ ኦላፍ ስሌይፐን "ይህንን ወርቅ መጠቀም የሚያስፈልገን ሁኔታ ላይ ፈጽሞ እንደማንደርስ እንጠብቃለን፤ ሆኖም ግን ጽናታችንን እና ለድንገተኛ ሁኔታዎች ያለንን ዝግጁነት ማጠናከር ያስፈልገናል" ብለዋል።

ለንደን እንደ ዓለም ዋነኛ የወርቅ ንግድ ማዕከል ባላት ቦታ ምክንያት የበለጠ አማራጭ ተደርጋ ትታያለች። በቀውስ ወቅት ወርቅን በፍጥነት መሸጥ ወይም መግዛት ከፈለጉ፣ ለንደን ተመራጭ ስፍራ ስለሆነች የእንግሊዝ ባንክ ወርቅ ለማከማቸት በጣም ተመራጭ ቦታ ሆኗል።

የእንግሊዝ ባንክ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የወርቅ ማከማቻ ተቋማት አንዱ ነው። በመካከለኛው ለንደን የሚገኘው የ300 ዓመታት ዕድሜ ያለው ተቋም ከመሬት በታች ከ400 ሺህ በላይ የወርቅ ጥፍጥፎችን አከማችቷል፤ እነዚህም ከ200 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ዋጋ አላቸው።

በዓለም የወርቅ ምክር ቤት (ዎርልድ ጎልድ ካውንስል) በተደረጉ ጥናቶች መሠረት፣ የእንግሊዝ ባንክ አሁንም ወርቅ ለማከማቸት በጣም ተመራጭ ስፍራ ሆኖ ቢቀጥልም፣ የአገራት ማዕከላዊ ባንኮች ግን ይህን ውድ ማዕድን የሚያከማቹባቸውን ቦታዎች በተለያዩ አገራት ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

የጎልድማን ሳክስ ተመራማሪዎች ሊና ቶማስ እና ዳን ስትሩይቨን እንደሚሉት፣ "አገራት የወርቅ ክምችታቸውን የት ማስቀመጥ አለባቸው" የሚለው ጉዳይ ለመጠባበቂያ ሀብት አስተዳዳሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም ወሳኝ ጥያቄ እየሆነ መጥቷል።

የባንክ ኦፍ ኢንግላንድ ህንጻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት የሚገኝበት ባንክ ኦፍ ኢንግላንድ

በዘመናዊው ዓለም ሀብትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ለማንቀሳቀስ በርካታ መንገዶች አሉ። ኔዘርላንድስ በኒው ዮርክ ያስቀመጠችውን 59 ቶን ገደማ ወርቅ በመሸጥ በለንደን ተጨማሪ የወርቅ ክምችት ገዝታለች። በዚህም ምክንያት የዚያን ያህል መጠን ያለው ወርቅ የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ ማጓጓዝ አላስፈለገም።

ይሁን እንጂ ከ27 ቶን በላይ ወርቅ ከአሜሪካ እና ከካናዳ ወደ ኔዘርላንድስ ዛይስት ከተማ "ተጓጉዞ" ተዛውሯል። ተመሳሳይ መጠን ያለው ወርቅም ከዛይስት ወደ ለንደን ተልኳል።

ይህ ወርቅ እንዴት ተጓጓዘ የሚለውን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ወርቅን ከአንድ አገር ወደ ሌላ የሚያጓጉዙ ኩባንያዎች ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ብዙም መረጃ አይሰጡም። ሆኖም ግን "ዘ ኢታሊያን ጆብ" በተባለው ፊልም ላይ እንደሚታየው ያለ የዝርፊያ አደጋ እንዳይፈጠር ከፍተኛ የደኅንነት ጥበቃ እና ዝግጅት እንደሚደረግ መገመት ይቻላል።

የዓለም የወርቅ ምክር ቤት ባለሙያ ጆሴፍ ካቫቶኒ እንደገለጹት፣ የወርቅ ክምችትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ለማዘዋወር ከሚጠቀሙባቸው የተለመዱ መንገዶች አንዱ በአንድ ቦታ ወርቁን መሸጥ እና በሌላ ቦታ ደግሞ መግዛት ነው።

"ለምሳሌ ወርቁ ለንደን ውስጥ ቢኖር እና በኒው ዮርክ እንዲቀመጥ ብፈልግ፣ ለንደን ያለውን በመሸጥ በዚያው ቀን ኒው ዮርክ ውስጥ መግዛት እችላለሁ። በዚህ ሁኔታ የባለቤትነት ለውጥ ይደረጋል እንጂ ወርቁን በአካል ማጓጓዝ አያስፈልግም" ብለዋል።

ወርቅን ከአገር ወደ አገር የሚያጓጉዙ ጥቂት ልዩ ኩባንያዎች ብቻ አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ብሪንክስ ግሎባል ሰርቪስስ አንዱ ሲሆን፣ ኩባንያው ለቢቢሲ እንደተናገረው በቅርብ ጊዜያት ወርቅን ለማንቀሳቀስ ከአገራት ማዕከላዊ ባንኮች የሚመጣው ጥያቄ "እየጨመረ" ነው።

የብሪንክስ ምክትል ፕሬዝዳንት ናደር አንታር እንደገለጹት፣ "የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት መጨመር፣ እንዲሁም ወርቅ እንደ ወሳኝ የመጠባበቂያ ሀብት ማከማቻነት ያለው ጠቀሜታ መጨመሩ ይህንን አዝማሚያ እያጠናከረው ያለ ይመስላል።"

የአገራት ማዕከላዊ ባንኮች የወርቅ ማከማቻ ጉዳይን በተለይ መነጋገር የጀመሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወርቅን በከፍተኛ መጠን ስለሚገዙ ነው። ሆኖም ግን ወርቁን በአገር ውስጥ ማከማቸት ከፍተኛ ወጪ እንዳለው የጎልድማን ሳክስ ተመራማሪዎች ሊና ቶማስ እና ዳን ስትሩይቨን ገልጸዋል።

"በአገር ውስጥ ማከማቸት ለጥበቃ፣ ለቁጥጥር መሠረተ ልማት እና ለኢንሹራንስ ሽፋን ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ያስፈልጋል። ወጪዎች በተለይ ለአነስተኛ ማዕከላዊ ባንኮች ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።

በዓለም የወርቅ ምክር ቤት መረጃ መሠረት፣ ባለፉት አራት ዓመታት ማዕከላዊ ባንኮች በየዓመቱ በአማካይ 1,000 ቶን ወርቅ ሲገዙ ቆይተዋል። ይህም ከዚያ በፊት በነበሩት 10 ዓመታት በአማካይ ይገዙ ከነበረው 500 ቶን በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።

ይህ አዝማሚያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ቀውስ ጊዜ ጀምሮ ሲታይ የቆየ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመትም የወርቅ ግዢ የበለጠ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

ወርቅ ባለፉት በቅርብ ዓመታት ልዩ ትኩረትን ሲያገኝ ቆይቷል። ዋጋውም በተከታታይ አዳዲስ ከፍተኛ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ ሲሆን፣ በጥር ወር አንድ ወቄት ወርቅ ከ5,000 ዶላር በላይ ተሸጧል።

የወርቅ ዋጋ በፍጥነት የጨመረበት ምክንያት በርካታ ቢሆንም፣ ዋነኛው ምክንያት ግን በሰዎች አስተሳሰብ ውስጥ ወርቅ እንደ "አስተማማኝ ሀብት" የሚታይ መሆኑ ነው። በንግድ ጦርነቶች እና በወታደራዊ ግጭቶች ምክንያት የፋይናንስና የጂኦፖለቲካ አለመረጋጋት በሚፈጠርበት ጊዜ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ወደ ወርቅ መቀየር ይመርጣሉ።

የዋጋ ንረት እና የወለድ መጠኖችም የወርቅ ተፈላጊነትን ይነካሉ። ወርቅ የተወሰነ መጠን ብቻ ያለው ሀብት ሲሆን፣ ከጥንታዊው ጊዜ አንስቶ ለዘመናት ከፍተኛ ዋጋ ሲሰጠው ቆይቷል። በመሆኑም ከዋጋ ንረት አንጻር መቋቋም ይችላል ተብሎ ይታመናል፤ በዚህም የተነሳ ጥሩ የኢንቨስትመንት አማራጭ ተደርጎ ይታያል።

እንደ ኢንቨስትመንት ባንኩ ቻርለስ ሽዋብ ገለጻ "ባለፉት 50 ዓመታት የወርቅ ዋጋ ከሸማቾች የዋጋ መለኪያ ጠቋሚ (ሲፒአይ) አንጻር በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል" ጠቋሚው ደግሞ የዋጋ ንረትን ለመመዘን በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል መለኪያ ነው።

ምንም እንኳን የወርቅ ዋጋ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ ትንሽ ቢቀንስም፣ ነገር ግን ከወርቅ ታሪክ አንጻር አሁንም በጣም ከፍ ባለ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጎልድማን ሳክስ ተመራማሪዎች መሠረት፣ በ2026 መጨረሻ የአንድ ወቄት የወርቅ ዋጋ 4,900 ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል። ይህም በነሐሴ ከነበረው ዋጋ በ300 ዶላር የበለጠ ነው።

ቶማስ እና ስትሩይቨን እንደሚገልጹት፣ ማዕከላዊ ባንኮች ለወርቅ እያሳዩት ያለው ከፍተኛ ፍላጎት የወርቅ ዋጋ በፍጥነት እንዲጨምር ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።