በሶማሊያ የሳውዝዌስት ግዛት ግጭት ሲቀሰቀስ፤ ቀድሞው ወታደራዊ አዛዥ የድሮን ጥቃት ተፈጸመባቸው

የቀድሞው የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዥ ማሃድ አብዲራህማን አደን

የፎቶው ባለመብት, X

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዥ ማሃድ አብዲራህማን አደን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሶማሊያ የሳውዝዌስት ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ባይዶዋ በመንግሥት እና ለቀድሞው የግዛቱ ፕሬዝዳንት ታማኝ በሆኑ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ።

በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በምትጎራበተው ጌዶ ግዛት ዶሎው አውራጃ ውስጥ ከሶማሊያ ፌደራሉ መንግሥት የተሰናበተ የቀድሞው ወታደራዊ አዛዥን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።

የሶማሊያዋን ሳውዝዌስት ግዛት ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያስተዳድሩ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዲአዚዝ ሀሰን መሀመድ ላፍታጋሪን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ከሥልጣን ለቅቀዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ኃይሎች የግዛቲቱን ዋና ከተማዋ ባይዶዋን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

ከዚያ ወዲህ ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ታማኝ በሆኑ ኃይሎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች ተፈጥረዋል።

ትናንት ሐሙስ ጠዋት ታጣቂዎች ባይዶዋ ውስጥ እና በዙሪያዋ በሚገኙ የመንግሥት ኃይሎች የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብዲአዚዝ ላፍታጋሪን አስታውቀዋል።

አዲሱ የግዛቱ አስተዳደር መሪ አዳን ማዶቤ በበኩላቸው "በአልሸባብ እና በላፍታጋሪ ሚሊሻዎች በጋራ" የተከፈተውን ጥቃት መከላከላቸውን ገልፀዋል።

የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴርም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኃይሎች ለከፈቱት ጥቃት ምላሽ መሰጠቱት ገልጿል። በዚህ ጥቃትም ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብም በጥቃቱ ተሳትፏል የሚል ክስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማቅረቡን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

አዲሱ የደቡብ ምዕራብ አስተዳደር ቃል አቀባይ መሐመድ ሼክ አብዱላሂ ኻዮውም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተመሳሳይ ውንጀላ አቅርበዋል።

"የጠዋት ፀሎት ሰዓት አካባቢ ላይ ፀረ-ሰላም የሆነው የአልሸባብ ቡድን ከተማዋን አጥቅቷል። እንደ ልማዳቸውም ጦርነቱን የጀመሩት በሰዎች እና በመኪና ላይ በደረሰ ፍንዳታ እንዲሁም በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ነው" ብለዋል።

ጥቃቱ ከተከፈተ በኋላ የግዛቱ ኃይሎች ታጣቂዎች "ከከተማዋ እስከሚጸዱ ድረስ ግዴታቸውን ሲወጡ" እንደነበረም አክለዋል። ከተማዋ ጥቃት የተፈጸመባት በአልሸባብ እንደሆነ እና ለዚህ ማስረጃ እንዳላቸው ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኃይሎች ግን ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉን ውድቅ አድርገዋል። "እኛ እና አልሸባብ አንድ ዓይነት አጀንዳ የለንም፣ ስለ ጦርነቱ አንድ ዓይነት አመለካከት የለንም፣ በአንድ ግንባርም ተባብረን መዋጋት አንችልም" ሲሉ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስተዳደር ቃል አቀባይ ኡጋስ ሐሰን አብዲ መሐመድ ተናግረዋል።

ከግጭት ጋር ስማቸው አብሮ የሚነሳው የቀድሞው የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዥ ማሃድ አብዲራህማን አደንን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ትናንት ሐሙስ ተፈጽሟል

የፎቶው ባለመብት, x

የምስሉ መግለጫ, ከግጭት ጋር ስማቸው አብሮ የሚነሳው የቀድሞው የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዥ ማሃድ አብዲራህማን አደንን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ትናንት ሐሙስ ተፈጽሟል

"የታቀደ እና የራሱ ግብ ያለው" ሲሉ የገለጹት የትናንቱ ጥቃት "አገሪቱ ላይ ወረራ የፈጸሙ ኃይሎችን ለማዳከም" ያለመ እንደሆነ ተናገረዋል።

ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ የተሰማበት ይህ ግጭት ከሰዓት ላይ የቆመ ሲሆን፣ የደረሰው ጉዳት መጠን እስካሁን እንዳልተረጋገጠ የግዛቱ አስተዳደር አስታውቋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች ግን የሰዎች ሕይወት እንዳለፈ እና በርካቶች እንደተጎዱ ገልጸዋል።

ለባይዶዋ አጠቃላይ ሆስፒታል ቅርበት ያላቸው ምንጮች፣ የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸው 25 ገደማ ሰዎች ወደ ጤና ተቋሙ መግባቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ ግጭት ጋር ስማቸው አብሮ የሚነሳው እንዲሁም የቀድሞው የግዛቱ ፕሬዝዳንት አማች የሆኑት የቀድሞው የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዥ ማሃድ አብዲራህማን አደንን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ትናንት ሐሙስ ተፈጽሟል።

የድሮን ጥቃቱ ደረሰው ለኢትዮጵያ ድንበር ቅርብ በሆነው የጌዶ ግዛት ዶሎው አውራጃ የሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ ጥቃት የጄነራሉ፣ ባለቤታቸው እና ሁለት የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ አምስት ሰዎች እንደተጎዱ የጁባ ላንድ ዳርዊሽ ኃይሎች ምክትል አዛዥ የሆኑት አሊ ሐሰን ዴቅ ተናግረዋል።

የማረሚያ ቤቶች ዘብ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ማሃድ መጋቢት ላይ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በፌደራሉ መንግሥት እና በክልል ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ነበር።