ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አራት ልጆቻቸው በእስራኤል የተገደሉባቸው ኻሊል አል ሃያ የሐማስ ጠቅላይ መሪ ሆኑ
ከእስራኤል ጋር በተደረገው የሁለት ዓመት ጦርነት አብዛኞቹ መሪዎቹ የተገደሉበት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ባወጣው መግለጫ፣ ኻሊል አል ሃያን አዲሱ መሪው አድርጎ መምረጡን አስታወቀ።
አዲሱ መሪ እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ባካሄደችበት ወቅት የተገደለውን ያህያ ሲንዋርን የሚተኩ ናቸው።
ከስደት በኋላ በጋዛ የነበረውን ንቅናቄ እየመሩ ያሉት ኻሊድ አል ሃያ፣ ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት ከእስራኤል ጋር ከተጀመረው አውዳሚ ጦርነት በኋላ ወደ መሪነት የመጡ አክራሪ አቋም ያላቸው የቡድኑን አባላት የሚወክሉ ተደርገው ይታያሉ።
ሃያ የአንዋር ሲንዋር የቅርብ አጋር የነበሩ ሲሆን፣ ኢራን ውስጥ በእስራኤል ከተገደሉት የቡድኑ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ጋር የሚያያዘውን ፖለቲካዊ መስመር የሚያስቀጥሉ ተደርገው ይታሰባሉ።
ሃይያ የሐማስ ዋነኛ ተደራዳሪ በመሆን የቡድኑ ልዑክ ያደረገውን ቀጥተኛ ያልሆነ የተኩስ አቁም ድርድር መርተዋል። በግብፅ እና በኳታር አማካኝነት ከአደራዳሪዎች ጋር በመገናኘትም ዓለም አቀፍ እውቅናን አትርፈዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሐማስን የዲፕሎማሲያዊ እና የፖለቲካ ዕቅዶችን በመምራት የበለጠ ኃላፊነትን ይዘዋል።
የ65 ዓመቱ ሃያ በዚህ ዓመት መስከረም ላይ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ የሐማስ መሪዎች ስብሰባ ላይ እያሉ ከተፈጸመው የእስራኤል የአየር ጥቃት ተርፈዋል። በጥቃቱ ወንድ ልጃቸው፣ አምስት ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የቡድኑ አባላት እና የኳታር የፀጥታ ኃይል አባል መገደላቸው ይታወሳል።
ኳታር ውስጥ የነበሩት የሐማስ መሪዎች ዒላማ የተደረጉት የጋዛ ጦርነትን የቀሰቀሰውን የቡድኑ ጥቃት በመምራታቸውን እንደሆነ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በወቅቱ አሳውቀዋል።
የእስራኤል ጥቃት የአዲሱን የሐማስ መሪ አራት ልጆች ግደሏል። ኳታር ውስጥ ከተገደለው በተጨማሪ ከዚያ ቀደም እርሳቸውን ጋዛ ውስጥ ለመግደል በተደረገ ሙከራ ሁለቱ ልጆቻቸው ተግደለዋል። ሌላኛው ደግሞ ግንቦት ወር ላይ ጋዛ ውስጥ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሕይወቱ አልፏል።
አሁን የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተመረጡት ኻሊድ አል ሃያ ወደ አመራር የመጡት በሁለት ዙር የድምጽ አሰጣጥ ሲሆን፣ የቡድኑ አባላት ለሐማስ የወደፊት አቅጣጫ የተለያዩ ዓላማዎች ባሏቸው ተፎካካሪ አመለካከቶች ምክንያት መከፋፈላቸው እየተነገረ ነው።
በመጀመሪያው ዙር ድምጽ አሰጣጥ የቀድሞው የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ ኻሊድ ሜሻል፣ ከኻሊድ አል ሃያ በጥቂት የበለጠ ድምጽ ቢሰጣቸውም፣ አሸናፊ ለመሆን የሚፈልገውን በቂ ድምጽ ባለማግኘታቸው ለሁለተኛ ዙር መካሄዱን ሂደቱን የሚያውቁተ የፍልስጤም ባለሥልጣን ተናግረዋል።
በሐማስ የውስጥ ሕግ መሠረት፣ አንድ ዕጩ በቀጥታ ለመመረጥ ድምጽ ከሚሰጡ 69 አባላት ካሉት የምርጫ ተወካዮች መካከል ቢያንስ 36 ድምጽ ማግኘት አለበት።
በዚህም ሁለተኛው ዙር ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ኻሊድ አል ሃያ አስፈላጊውን ድምጽ አግኝተው የሐማስ መሪነት ቦታን ለመያዝ ችለዋል።
ጋዛን ለረጅም ጊዜ ሲያስተዳድር የነበረው ሐማስ ከአውዳሚው የሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ በታሪኩ እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት ጊዜያት በአንዱ ውስጥ እያለፈ ነው።
በእስራኤል፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ እና በሌሎች በርካታ አገራት ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ የተሰየመው ሐማስ፣ በጋዛው ጦርነት በእጅጉ ተዳክሟል።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የቡድኑ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የፖለቲካ አመራሮች የተገደሉ ሲሆን በጋዛ ያለው የአስተዳደር መዋቅሮቹ ፈርሰዋል። የፍልስጤም ግዛት ሰፊ ክፍሎችም ወድመዋል።
በቡድኑ አመራር ውስጥ የተፈጠረው ፉክክር በሐማስ የወደፊት ሁኔታ ላይ ሰፊ የሆነ የስትራቴጂ ልዩነት እንዳለ ይፋ አውጥቷል።
ቀደም ሲል በስደት ሆነው የሐማስን እንቅስቃሴ ለአስርት ዓመታት የመሩት ኻሊድ ሜሻል ከሐማስ ቀደምት አመራር ጋር የተያያዙ ናቸው።
የሜሻል ደጋፊዎች ሐማስ በጋዛ ከተካሄደው ጦርነት ትምህርት በመውሰድ፣ በዋናነት በትጥቅ ትግል ላይ ያተኮረ ስትራቴጂን በመተው፣ የንቅናቄውን ዋና ዋና ዓላማዎች በማስጠበቅ የበለጠ ከሁኔታዎች ጋር የሚስማማ ተግባራዊ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ መከተል እንዳለበት እየተከራከሩ ነው።
ይሁን እንጂ የኻሊድ አል ሃያ ደጋፊዎች የጋዛ አመራር፣ ግጭቱ ያስከተለውን ኃላፊነት በመቀበል አሁንም ንቅናቄውን መምራት እንዳለበት በአሳማኝ ሁኔታ ተከራክረዋል። በተለይም የሐማስን የጦር መሳሪያ መፍታት የሚመለከቱ ወሳኝ ስምምነቶች እንዲፈጸሙ የሚደረገው ጫና ላይ ጽኑ አቋም መያዝ እንዳለበት ያምናሉ።
ሐማስ በጋዛ የተካሄደውን ጦርነት ያስቆመውን የተኩስ አቁም ስምምነት ከእስራኤል ጋር ከተፈራረመ ወዲህ የፍልስጤምን የራስን ዕድል በራስ መወሰን እና አገርነትን የሚያረጋግጥ የፖለቲካ መንገድ ሳይመቻች የጦር መሳሪያዎቹን ለመፍታት ፈቃደኛ አይደለም።
በተጨማሪም የጋዛን መልሶ ግንባታ ይልቅ፣ ግዛቱን በአስቸኳይ ከወታደራዊ ኃይል እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግን የሚያስቀድመው በአሜሪካ የሚመራው የሰላም ቦርድ ያወጣውን ዕቅድ ሐማስ ውድቅ አድርጎታል።
ሐማስ አሁንም በጋዛ ውስጥ የእስራኤል ጥቃቶች መቀጠላቸውን እና ተቀናቃኝ ታጣቂ ቡድኖች መፈጠራቸው የደኅንነት ዋስትና ችግር እንደፈጠረ ቅሬታ አቅርቧል።
ከሦስት ዓመት በፊት ገደማ በሐማስ መሪነት በእስራኤል ላይ በተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1,200 ሰዎች መገደላቸው እና 251 ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው ወደ ጋዛ መወሰዳቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ በጋዛ ላይ ከባድ ውድመትን ባስከተለው የእስራኤል መጠነ ሰፊ ጥቃት ከ73,280 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህም ውስጥ 1,158 ያህሉ የሞቱት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈጻሚ መሆን ከጀመረ በኋላ ነው።