14 የአፍሪካ አገራትን የሚያቋርጥ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ከስምምነት ተደረሰ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአፍሪካ ትላልቅ ከሆኑ የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች አንዱ የሆነውን የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ከስምምነት ተደረሰ።

ከናይጄሪያ እስከ ሞሮኮ የሚደርሰው ይህ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን አሁን የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች እቅዱን ተቀብለውታል።

የሴራሊዮን ፕሬዚደንት እና የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ኃላፊ ጁሊየስ ማዳ ባዮ እሁድ ምሽት በፍሪታውን ከተማ በተካሄደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ፣ " ጋዙ ወደ እናንተ አካባቢ ሲመጣ እንዳትገረሙ" ብለዋል።

ስድስት ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የጋዝ መስመር በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ 14 የአፍሪካ አገራትን ይሸፍናል።

የጋዝ ማስተላለፊያው በስፔን በኩል ከሚያልፈው የአውሮፓ የጋዝ መስመር ጋር ከመገናኘቱ በፊት የናይጄሪያን ጋዝ ወደ ሞሮኮ ያደርሳል።

የግንባታው ፕሮጀክት በናይጄሪያ የነዳጅ ኩባንያ እና በሞሮኮ ብሔራዊ ማዕድን ተቋም በጋራ እንደሚመራም ተገልጿል።

እንደ ኢኮዋስ፣ ኢስላሚክ ደቨሎፕመንት ባንክ እንዲሁም የነዳጅ አምራች እና ላኪ አገራት ኦፔክ ፈንድ ባሉ ቀጣናዊ ተቋማትም ድጋፍ ይደረግለታል።

የነዳጅ ማስተላለፊያው ግንባታ ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ይፈጃል ተብሏል።

የኤነርጅ ባለሙያ እና የቀድሞው የናይጄሪያ መንግሥት አማካሪ ቻርልስ ማጆሚ እንደሚናገሩት፣ የማስተላለፊያ መስመሩ ግንባታ ከአፍሪካ የወጣ ጋዝ በውጭ አገራት ተጣርቶ እና ተዘጋጅቶ በሦስት ወይም በአራት እጥፍ ዋጋ መልሶ ለአፍሪካ አገራት የሚሸጥበትን ሥርዓት ይቀይራል።

እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገራትን የተፈጥሮ ሃብት ሙሉ በሙሉ ዋጋ የሚያሳጣው የቀድሞ ልማድ ማብቃት አለበትም ብለዋል።

የጋዝ ማስተላለፊያው በትክክል አገልግሎት ላይ ከዋለ የቀጣናውን ኢንደስትሪ እድገት ከማነቃቃት በተጨማሪ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን አቅም እንደሚጨምር ተገልጿል።

በናይጄሪያ ናሽናል ኦፕን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጋኒያት አዲጆኬ አደሲና ኡትማን፣ "የኤነርጅ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር አፍሪካ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር እንድትገናኝ መንገድ ይከፍታል" ብለዋል።

አገራት ከተባበሩ እና አብረው መሥራት ከቻሉ አፍሪካ ትልቅ ነገር ማሳካት እንደምትችል ማሳያ እንደሚሆንም ፕሮፌሰሯ አክለዋል።

የናይጄሪያ - ሞሮኮ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እቅድ ከተሳካ በዓመት 30 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ማስተላለፍ የሚችል ሲሆን 400 ሚሊዮን ሕዝቦችን ያገለግላል።

ይህም በውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ከተዘረጉ የዓለም የጋዝ ማስተላለፊያዎች አንዱ የሚያደርገው ሲሆን የምዕራብ አፍሪካን የኤነርጂ ምሕዳር ይለውጣል።

የጋዝ ማስተላለፊያው ግንባታ ላይ ከስምምነት ከመደረሱ በፊት ለአስር ዓመት ገደማ ከ12 በላይ አገራት የተሳተፉበት ድርድር ሲደረግ ቆይቷል።