ዩኬ ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን የምትልክበትን ስምምነት ብታፈርስም ገንዘብ እንዳትቀጣ ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን ልትልክበት የነበረው ስምምነት ቢፈርስም በሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ እንዳትቀጣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ሥልጣን ከያዙ በኋላ ስምምነቱ መሰረዙ ይታወሳል።
የሩዋንዳ መንግሥት ዩኬ ስምምነቱን በማፍረሷ 100 ሚሊዮን ፓውንድ እንድትቀጣ በፍርድ ቤት ከስሷል።
ከሩዋንዳ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው የቀድሞው ወግ አጥባቂ መንግሥት ነበር። በሕገ ወጥ መንገድ ዩኬ የገቡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክም ተስማምተዋል።
ኔዘርላንድ በተካሄደው የሦስት ቀን የችሎት ውሎ ዩኬን የወከሉ ጠበቆች እንዳሉት ሌበር ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ ስምምነቱ መሰረዙ "ምክንያታዊ" ነው።
ስለዚህም ዩኬ ስምምነት ስላላፈረሰች ገንዘብ መቀጣት እንደሌለባትም ተከራክረዋል።
ለፍርድ ቤቱ "ሩዋንዳ የምትጠይቀውን ክፍያ የማግኘት መብት የላትም" ብለዋል።
የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩ እና ጉዳዩ አክትሟል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"ፕ/ር መሐመድ አብደል ዋሀብ ያቀረቡት አስተያየት ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ጉዳይ ውስብስብ እንደሆነ እና በተለያየ መንገድ ሊተረጎም እንደሚችል ያሳያል። ዩኬ በሁለቱ አገራት መካከል በ2024 የተደረሰውን የፋይናንስ ስምምነት አልለወጠችም" በማለትም መግለጫ አውጥቷል።
የሩዋንዳ የፍትሕ ሚኒስቴር እና ዐቃቤ ሕግ ኢማኑኤል ኡግራሻቡጃ አገሪቷ ከዩኬ ጋር የገባችውን ስምምነት ለመፈጸም ባደረገችው ዝግጅት "ከፍተኛ ኪሳራ" ቢገጥማት ዩኬ "ሕጋዊ ኃላፊነቷን እንዳልተወጣች" ከዚህ ቀደም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
"ዩኬ ስምምነቱን ልትሰርዝ እንደሆነ ለሩዋንዳ ቀድማ ማብራሪያ አልሰጠችም። መንግሥታችን ዜናውን ከመገናኛ ብዙኃን ነው የሰማው" ብለዋል።
ኢንግሊሽ ቻናልን በጀልባ የተሻገሩ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅድን ያወጡት የቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ነበሩ።
ዕቅዱ በአውሮፓውያኑ 2022 በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ይፋ ተደርጓል።
እንደ ፈረንሳይ ካሉ አገራት "በሕገ ወጥ መንገድ" ወደ ዩኬ ተሻግረው የሚገቡ ስደተኞችንም ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ታቅዶ ነበር።
የመጀመሪያው ስደተኞችን የያዘ አውሮፕላን በ2022 ወደ ሩዋንዳ ከመብረሩ ከደቂቃዎች በፊት የአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት ጣልቃ በመግባቱ ዕገዳ ተጥሎበታል።
ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ ዕቅድ ከዚያ በኋላ ተከታታይ የሕግ ጥያቄ ተነስቶበታል።
የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞች ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገራት ለመሄድ 3,000 ፓውንድ እንዲከፈላቸው የሚያደርግ አሠራርም ተዘርግቶ እንደነበር ይታወሳል።
ወደ ሩዋንዳ በፈቃደኛነት የሄዱት አራት ስደተኞች ብቻ ናቸው።
ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ የዩኬ መንግሥት "ድንበራችንን ለማስጠበቅ ቁልፍ ማሻሻያዎች እናደርጋለን። ይሄም ስደተኞች ወደ ዩኬ እንዲመጡ የሚያበረታታ አካሄድን መሰረዝን ያካትታል። በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ስደተኞችን ማስወጣትም እንቀጥላለን" ብሏል።
እንዳያመልጥዎ
ከየፈርጁ
በስፋት የተነበቡ
- 10















