በአሜሪካ ሚኒሶታ ከተገዛች ሦስት ወር የሆናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የደረሰባት ውድመት

ቃጠሎ የደረሰባት በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ የምትገነው ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስትያን

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ሚኒሶታ በእሳት ቃጠሎ ከባድ ጉዳት የደረሰባት የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል እና የቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰኞ ዕለት ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም. የቃጠሎ ውድመት እንደደረሰበት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መላዕከ ብስራት ቀሲስ መሪጌታ ጌታሁን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ዘጠኝ ዓመት ቢሆናትም በቃጠሎ ወደ ወደመው ቤተክርስቲያን ገዝተው ከገቡ ግን ሦስት ወር እንደሆናቸው አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ወደ አዲሱ የቤተክርስቲያን ሕንጻ የገቡት የዳግማ ትንሳዔ ዕለት ሚያዚያ 11/2018 ዓ.ም. መሆኑን ያስታወሱት የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ "ይህ ነገር የተከሰተው የሐምሌ ገብርኤልን ለማክበር እየተዘጋጀን ባለንበት ወቅት ነው" ብለዋል።

አስተዳዳሪው ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ በሮዝማውንት ሚኒሶታ የምትገኘው ይህች ቤተ ክርስቲያን "ቃጠሎው መከሰቱን የሰማነው ሰኞ ዕለት ቀድሰን ወጥተን ወደ ቤታችን እየሄድን ባለበት ወቅት ተደውሎልን ነው" ብለዋል።

እስካሁን ድረስ የቃጠሎው መንስዔን ለማወቅ የአካባቢው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው "ምክንያቱን አላወቅንም፤ እኛ ቅዳሴ ከጨረስን በኋላ በጥንቃቄ ሁሉንም ነገር አጠፋፍተን ነው የወጣነው" ሲሉ አስረድተዋል።

በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ሰኞ ረፋድ አራት ሰዓት ከ46 ደቂቃ አካባቢ የሚኒሶታ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ የበርካቶችን ልብ ሰብሯል።

የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እና ምዕመናን እንዳሉት የቤተ ክርስቲያኗ ሕንጻ ተገዝቶ በከፍተኛ ወጪ ታድሶ ከተከፈተ ከሦስት ወር በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ ዲያቆን ዳግም ጥላሁን 'ኬር11'' ለተባለው የአካባቢው የበይነ መረብ ዜና ዌብ ሳይት እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗን ባለፈው ሚያዝያ ለመክፈት "ሁሉም እንቅልፉን አጥቶ ሳምንቱን በሙሉ ለ24 ሰዓታት የሚችልውን አድርጓል" በማለት አደጋው የፈጠረውን የልብ ስብራት ገልጸዋል።

በሯን ለምዕመናን ከከፈተች ገና ሦስት ወራት የሆናት ቤተ ክርስቲያኗ ላይ ለደረሰው አደጋ መነሻ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ገና አለመታወቁን የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በእውነቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ልብ የሚሰብር ነው" ያሉት ዲያቆን ጥላሁን "በርካታ ሰዎች በአደጋው ምክንያት ሲያልቅሱ ታይተዋል" በማለት አደጋው የፈጠረውን ሐዘን ገልጸዋል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቅዳሴ ጨርሰው ከወጡ ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ ቃጠሎ መከሰቱን ተደውሎ እንደተናገራቸው አስታውሰው "ከባድ ቃጠሎ ነው የነበረው። ስንደርስ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እያጠፉ ነበር" ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኑን ብቻ ለመግዛት ብቻ 2.2 ሚሊዮን ዶላር ማውጣታቸውን የሚናገሩት አስተዳዳሪው፣ ከዚያ በኋላ ውስጡን ለማሳደስ ተጨማሪ ከፍተኛ ወጪዎችን ማውጣታቸውን ይናገራሉ።

በእሳት ቃጠሎው የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማስረዳት "የፖሊስን የምርመራ ውጤት መጠበቅ እንደሚያስፍለግ" የሚያስረዱት አስተዳዳሪው፤ እስከዚያው ድረስ በቤተክርስቲያኗ ላይ የደረሰው ውድመት ምን ያህል እንደሆነ ለመናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በቃጠሎው ምክንያት በንብረት ላይ ከደረሰው ከባድ ውድመት ውጪ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ እንደሌለ መላከ ብስራት ቀሲስ መሪጌታ ጌታሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስትያኒቱን ወደ ነበረችበት ይዞታ ለመመለስ የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ገልጸው ለጊዜው ከመጪው እሁድ ጀምሮ በስፍራው ላይ ድንኳን ጥለው የአምልኮ ሥርዓት ለማካሄድ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማሰራት ምዕመናኑ "ቤታቸውን ትተው እያደሩ ነው የሠሩት" የሚሉት አስተዳዳሪው "አንድ አባወራ እስከ ሰባት ሺህ፣ ስምንት ሺህ ዶላር ድረስ በማዋጣት ነው የተገዛው" ሲሉ ሁኔታውን አስታውሰዋል።

የቤተክርስትያኒቱ ምዕመናን ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በአካባቢው ያሉ የቤተክርስቲያኗ አባላት ከፍተኛ ወጪን ማውጣታቸውን ጠቅሰው "ሁሉም በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ናቸው" ብለዋል።

የቤተክርስቲያኒቱ አዳራሽ ከአደጋው "ሳይተርፍ አልቀረም" የሚሉት አስተዳዳሪው፤ ነገር ግን ፖሊስ የሚያካሂደው ምርመራ ባለመጠናቀቁ ይህንን ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስር ብትሆንም ታሪኳ የሚጀምረው ግን የቅዱስ ዮሐንስ ሉተራን ቤተክርስቲያን ሆና ከአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ ነው።

በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ያሳዘነው ኢትዮጵያውያን ምዕመናንን ብቻ ሳይሆን፣ ከቀድሞው ቤተ ክርስቲያን ጋር የዘመናት ታሪክ ያላቸው አሜሪካውያን የአካባቢው ነዋሪዎችን ጭምር መሆኑን ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

ከእነዚህም መካከል ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ጠብቅ ታሪክ ያላቸው ማርክ የተባሉት ግለሰብ አንዱ ናቸው።

ማርክ ባለቤታቸው በቤተክርስቲያኗ ያደጉት ሲሆን፣ ጋብቻቸውንም የፈጸሙት፣ ልጆቻቸውም ያስጠመቁት እዚያው ነበር።

በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ ውስጥ ብቻ የተቃጠለችዋን ጨምሮ አምስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ይገኛሉ።