በቅዳሴ ላይ ሳሉ መስቀል ወድቆባቸው የሞቱት ቄስ ምን ሲሉ ነበር?

ቄስ ፓትሪሲዮ አልፍሬዶ ሳንቼዝ ሞሊናሪ
የምስሉ መግለጫ, የ53 ዓመቱ ቄስ ፓትሪሲዮ አልፍሬዶ ሳንቼዝ ሞሊናሪ አደጋው ከመድረሱ በፊት በስብከት ላይ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢኳዶር ውስጥ አንድ የካቶሊክ ቄስ በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ሳሉ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረ ትልቅ መስቀል ራሳቸው ላይ ወድቆ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ በአገሪቱ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ሐዘን ተፈጥሯል።

አደጋው የደረሰው ቅዳሜ ዕለት በኢኳዶሯ ከተማ ጉዋያኪል ማዕከላዊ ክፍል በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን፣ ሕይወታቸው ያለፈው ቄስ ፓትሪሲዮ አልፍሬዶ ሳንቼዝ ሞሊናሪ መደበኛ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት እየመሩ ነበር።

የ53 ዓመቱ ሳንቼዝ ሞሊናሪ በመሠዊያው ፊት ሆነው ቅዳሴውን እየመሩ ሳለ፣ ከጀርባቸው የነበረ ትልቅ የእንጨት መስቀል በድንገት ከተሰቀለበት ቦታ ወድቆ ጭንቅላታቸውን መትቷል።

በከባድ ሁኔታ ጭንቅላታቸውን በመታታቸው ምክንያት ቄሱ ወዲያውኑ መሬት ላይ ሲወደቁ፤ በቅዳሴው ላይ የታደሙ ምዕመናን እንዲሁም ሥነ ሥርዓቱን በቀጥታ በማኅበራዊ ሚዲያ ይከታተሉ የነበሩትን ሰዎችን አስደንግጧል።

አደጋውን ተከትሎ የከተማዋ ሊቀ ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ቅዳሜ ምሽት የቄስ ሳንቼዝን ሞት አረጋግጦ፣ "ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለደረሱን የማጽናኛ መልዕክቶች እናመሰግናለን። በተለይም ለአባ ፓትሪሲዮ ሳንቼዝ ነፍስ ዘላለማዊ ዕረፍት እንዲሰጣት የምታደርጉትን ጸሎት እናደንቃለን" ብሏል።

የከተማዋ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ሉዊስ ካብሬራ እሑድ ዕለት አደጋው በተከሰተባት የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለቄስ ፓትሪሲዮ ሳንቼዝ መታሰቢያ ቅዳሴ መርተዋል።

መስቀሉ በቄሱ ላይ ሲወድቅ
የምስሉ መግለጫ, ትልቁ መስቀል የወደቀበት ቅጽበት

እስካሁን ድረስ ትልቁ መስቀል ከተሰቀለበት ቦታ ለቅቆ እንዲወድቅ ያደረገው ምክንያት ምን እንደሆነ አለመታወቁን እና ባለሥልጣናት ምርመራ እያደረጉ መሆኑ ተዘግቧል።

አደጋው ከመድረሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ቄሱ ባደረጉት ስብከት፣ ምዕመናን በየዕለቱ ለእግዚአብሔር የሚሰጡትን ጊዜ እንዲያስቡበት ጠይቀው ነበር።

እንዲሁም ያንን ጊዜ እንደ ሞባይል ስልክ ወይም የቴሌቪዥን ተከታታይ ፕሮግራሞች ላሉ አላፊ ነገሮች ከሚሰጡት ጊዜ ጋር እንዲያነጻጽሩት እና ራሳቸውን እንዲጠይቁ አሳስበው ነበር።

በተጨማሪም "ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ አንድ ቀን እዚህ ያለን ሁላችንም እንሞታለን" በማለት ከዚያ በፊት ግን ምዕመኑ ከእግዚአብሔር እና በዙሪያው ካሉ ሰዎች ጋር ያለውን ትስስር እንዲያጠናክር መምከራቸውን የቢቢሲ ስፓኒሽ ቋንቋ አልግሎት ቢቢሲ ሙንዶ ዘግቧል።

"አንዳንድ ጊዜ ብዙ ትርጉም በሌላቸው ነገሮች ላይ የምናጠፋው ጊዜ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከምናሳልፈው ጊዜ እኩል አይሆንም። ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ ለባሎቻችን እና ሚስቶቻችን፣ ለልጆቻችን እና ለቤተሰቦቻችን የምንሰጠው መልካም ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ነው" ብለው አክለዋል።

ስብከታቸውን ከጨረሱ በኋላ ቄሱ ወደ መሠዊያው ተመልሰው ቀጣይ የቅዳሴውን የምልጃ ክፍል ጀመሩ። ሆኖም አደጋው የተከሰተው ስብከታቸው ከተጠናቀቀ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ነበር።

አደጋው ሲከሰት በቅርብ ርቀት የነበረች አንዲት ሴት "አባታችን! አባታችን!" እያለች ቄሱን ለመርዳት ሰትሞክር እና "አምቡላንስ ጥሩ! አባታችን! አባታችን!" ስትል ተሰምታለች።

የከተማዋ ጉዋያኪል ባለሥልጣናትም ሆኑ የከተማው ሊቀ ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት፣ ከባድ የነበረው መስቀል ከተሰቀለበት ቦታ ተላቅቆ እንዲወድቅ ምን እንዳደረገው ወዲያውኑ መረጃ አልሰጡም።

የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ሰኞ ዕለት፣ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያለውን የክርስቶስ ምሥል ከመስቀሉ ጋር እንደገና በቦታው ለማስቀመጥ የሚካሄደውን ሥራ የሚያሳዩ ምሥሎችን አሳይተዋል።