መከላከያ ሠራዊት "ጽምዶ"ን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ገለጻ መስጠቱን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EBC/YOUTUBE
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ጽምዶ" በሚባለው እንቅስቃሴ በኩል "በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣ" ስጋት ቢኖር ስለሚወስደው እርምጃ አገር ውስጥ ለሚገኘው ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማሳወቁን ገለጸ።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተር፤ ይህንን እንቅስቃሴ " 'ወደ መሬት እናወርዳለን' ብለው ስንዝር እንቅስቃሴ" የሚያደርጉ አካላትን አስጠንቅቀዋል።
ዳይሬክተሩ ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ይህንን ያስታወቁት ትናንት አርብ ግንቦት 14/2018 ዓ. ም. በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ላይ ነው። 21 ደቂቃ ገደማ የፈጀው ቃለ መጠይቅ በሙሉ ያተኮረው "ጽምዶ" በሚለው ስያሜ ስለሚደረገው እንቅስቃሴ ነው።
የሜጀር ጄነራል ተሾመ ቃለ መጠይቅ የተላለፈው፤ የተለያዩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ከሱዳን እና ኤርትራ እንደሆኑ የተገለጹ ግለሰቦች በሱዳኗ ፖርት ሱዳን ከተማ ስብሰባ አካሂደው እንደነበር የሚያሳይ ቪዲዮ ከተለቀቀ ከቀናት በኋላ ነው።
ዝግጅቱን የሚያሳየው ቪዲዮ የተለቀቀው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ባለው 'ህድሞና ቲቪ' የተባለ የዩቲዩብ ቻናል ላይ ነው።
ከዚህ ቀደም "ጽምዶ" የሚለው ቃል በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች እና በኤርትራ መካከል ይደረጋል የሚባለውን ግንኙነት ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውል ነበር።
እስካሁን ድረስ ሁለቱም ወገኖች በአመራሮች ደረጃ ግንኙነት ስለመፍጠራቸው በይፋ አልገለጹም።
በትናንቱ ቃለ መጠይቅ ላይ ሜጀር ጄነራል ተሾመ፤ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽምዶ የምትባል ነገር የተጀመረችበት ሒደት እንዳለ" ተጠቅሶ ስለ ጉዳዩ ምንነት ተጠይቀዋል። እንቅስቃሴውን "ፀረ ሉዓላዊነት" ሲሉ የገለጹት ሜጀር ጄነራል ተሾመ፤ "ጫንቃቸውን ለፈርኦን ቀንበር" በሰጡ የኢትዮጵያ አካላት እና "አካባቢው ላይ ባሉት ስብስብ" የተፈጠረ ነው ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት "በራሱ ቻናል" ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ "የአታሼ ማኅበረሰብ" አባላት ስለዚህ ጉዳይ "በደንብ እንዲያውቁ እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ሥራ" መከናወኑን አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ አገር ውስጥ ላሉ "አታሼዎች ስለ ሁኔታው ማስገንዘብ" ያስፈለገው "ለአምባሳደሮቻቸው ቀዳሚ ሰዎች እና አካላት ስለሆኑ" ነው።
በተጨማሪም "ነገ እንደው እቺን ሐሳብ 'ወደ መሬት እናውርድ' ብሎ የሚሠራ አካል ካለ" የሚሰጠው ምላሽ ለዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ "አስቀድሞም የተነገረ ጉዳይ" እንዲሆን በመታሰቡ መሆኑንም አስረድተዋል።
"ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነገ ትልቅ [እርምጃ] የሚያስወስድ ጉዳይ ቢነሳ የማንንም ፈቃድ መጠየቅ እንኳ ባያስፈልግ፤ ወዳጆቻችን፣ አብረውን የሚሠሩ ሰዎች የውጪ ሰዎች ይሄን ሐሳብ እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ ስለሆነ [ነው]" ሲሉም አብራርተዋል።
ሜጀር ጄነራል ተሾመ፤ የውጭ ጉዳይ ሚስቴርም በዚሁ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ሥራ ያከናውናል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል።
ይህ እንቅስቃሴ "ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት አስጊ" ተደርጎ እንደማይወሰድ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ሐሳቡን ለመተግበር የሚደረግ እርምጃን በተመለከተ ግን አስጠንቅቀዋል።
"እቺኛዋን የጽምዶ ሐሳብ በተመለከተ ግን፤ ይቺን ቅዠት 'ወደ መሬት እናወርዳታለን' ብለው ስንዝር እንቅስቃሴ ቢያደርጉ፣ እንደ ሉዓላዊ አገር ይሄ ተቋም ደግሞ በመንግሥት ግዳጅ እንደተሰጠው፣ ኃላፊነት እንደተሰጠው፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራ አካል፤ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥ ይቀልጣሉ ብለን ነው የምናስበው፣ የምናምነው" ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ገለጻ እንደሰጠበት የገለጸው "ጽምዶ" ዝግጅት በፖርት ሱዳን የተካሄደው፤ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የተፈጠረው ውጥረት ይፋ በወጣበት ወቅት ነው።
ባለፈው ሚያዝያ ላይ በጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር "ከኢትዮጵያ የተነሱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድሮኖች" ግዛቱ ውስጥ ጥቃት መፈጸማቸውን በመግለጽ ወንጅሎ ነበር።
ይህንን ክስ "መሠረተ ቢስ" በማለት ያጣጣለው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፤ ሱዳን "ለተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ማዕከል ሆና እያገለገለች" መሆኑን በማንሳት በምላሹ ከስሷል።















