የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ጦር ያቀረበውን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ ሱዳንን "በፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ማዕከልነት" ወነጀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሱዳን ጦር መሪ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳን ጦር "ከኢትዮጵያ የተነሱ ድሮኖች ጥቃት ፈጽመዋል" በሚል ያቀረበውን ክስ "መሠረተ ቢስ" እና "በውጭ ኃይሎች ትዕዛዝ የቀረበ" ሲል ውድቅ አደረገ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በምላሹ ሱዳን "ለተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ማዕከል" መሆኗን እንዲሁም የአገሪቱ ጦር "የህወሓት ቅጥረኛ ተዋጊዎችን እየተጠቀመ" መሆኑን በመግለጽ ከስሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ እና የውጭ ጉዳይ ሚስትር ትናንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ ላይ ክስ ካቀረቡ በኋላ ነው።

የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ባሕር ዳር ከተማ የተነሳ ድሮን በትናንትናው ዕለት የኻርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት አድርሷል የሚል ክስ አቅርቧል።

የኻርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት "የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢትዮጵያ መሳተፋቸውን ማስረጃዎችን" እንዳለም ገልጿል።

ከመጋቢት ወር እነስቶ "ከኢትዮጵያ ባሕር ዳር አየር ማረፊያ የተነሱ ሦስት ድሮኖች" በአገሪቱ አራት ግዛቶች ውስጥ ጥቃቶች መፈጸማቸውንም በማንሳት ከስሷል።

በተለያዩ ማስረጃዎች "የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ንብረት መሆኑን እና በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ከባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጥቅም ላይ መዋሉን" እንዳረጋገጠ በመግለጽም ከስሷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በትናንቱ የጋራ መግለጫ የቀረበውን የሱዳን ክስ "መሠረተ ቢስ" ሲል ውድቅ አድርጎታል። ይልቁንም "ሁለቱ አገራት መካከል ላለው የወንድማማችነት ግንኙነት እውቅና" ሲል የአገሪቱ ጦር የሚፈጽማቸውን ድርጊቶች "ይፋ ከማድረግ መቆጠቡን" ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት "በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባሉ ጠብ ፈላጊ አካላት በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ የተፈጸሙ ከባድ ጥሰቶች ይፋ ከማድረግ መቆጠቡን" በመግለጫው አስፍሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተፈጽመዋል በሚል ከጠቀሳቸው "ጥሰቶች" አንዱ "ከህወሓት ቅጥረኛ ተዋጊዎች" ጋር የተገናኘ ነው። "በግጭቱ ውስጥ የህወሓት ቅጥረኛ ተዋጊዎች በስፋት የመጠቀም" ድርጊት መታየቱን አስታውቋል።

"የሱዳን ጦር ኃይሎች ለእነዚህ ቅጥረኛ ተዋጊዎች የመሣሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ አቅርቧል" ያለው ሚኒስቴሩ፤ በዚህ አማካኝነት "በኢትዮጵያ ምዕራባዊ ድንበር በኩል የሚያደርጉትን ወረራ አመቻችቷል" ሲል ከስሷል።

"ሱዳን ውስጥ የሚገኙ የህወሓት ቅጥረኛ ተዋጊዎች ጉዳይ በይፋ የተመዘገበ" ጉዳይ መሆኑንም በመግለጫው ጠቅሷል። "ሱዳን የተለያዩ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ማዕከል ሆና እያገለገለች መሆኑን የሚያሳዩ ሰፊ እና ተአማኒ ማስረጃዎች አሉ" ሲልም ክሱ በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን አረስድቷል።

"እነዚህ ጠብ ጫሪ ድርጊቶች" እንዲሁም የሱዳን ጦር ባለሥልጣናት ያቀረቧቸው ክሶች "የራሳቸውን ክፉ አጀንዳ ለማራመድ በሚፈልጉ የውጭ ደጋፊዎች ትዕዛዝ የተከናወኑ መሆናቸው ግልጽ ነው" ብሏል።

ኢትዮጵያ "ከሱዳን ሕዝብ ጎን በአጋርነት መቋሟን እንደምትቀጥል" የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ አገሪቱን ከገባችበት "ቀውስ [የሚያወጣ] ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለ" አስረድቷል።

"ኢትዮጵያ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች መካከል ንግግር እንዲደረግ" እና "አስቸኳይ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ" በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።

ቀጥሎም "ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም እና ለሲቪል አስተዳደር መመለስ መሠረት የሚጥል ነፃ፣ አካታች እና ግልጽ በሲቪል የሚመራ ንግግር እና የሽግግር ሂደት" አፈስላጊ እንደሆነም በአጽንኦት አንስቷል።

ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመቀናጀት ከሱዳን ጦር ጋር ለሚዋጋው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ለሚቀርብባት ክስ በይፋ ምላሽ ስትሰጥ ይህ የመጀመሪያው ነው። ኤምሬቶች ከዚህ ቀደም እነዚህን ክሶች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።