የሱዳን ጦር ከባሕር ዳር የተነሳ ድሮን የኻርቱም አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት እንደፈጸመ በመግለጽ ከሰሰ

የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል አሲም አዋድ አብዱልወሃብ

የፎቶው ባለመብት, SUNA

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል አሲም አዋድ አብዱልወሃብ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ባሕር ዳር ከተማ የተነሳ ድሮን በትናንትናው ዕለት የኻርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት አድርሷል ሲል ከሰሰ። "የተፈጸመው ቀጥተኛ ጥቃት በዝምታ አይታለፍም" ያለችው ሱዳን፤ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ለምክክር መጥራቷን አስታውቃለች።

በጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን የሚመራው የሱዳን ጦር ይህንን ክስ ያሰማው ትናንት ሰኞ ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም. በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

መግለጫውን የሰጡት የጦሩ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል አሲም አዋድ አብዱልወሃብ እና የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትሩ አምባሳደር ሙሂ ኤልዲን ሳሌም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ከጦሩ ጋር ለሚዋጋው የሱዳን ፈጥሮ ደራሽ ኃይል ድጋፍ እያደረጉ ነው የሚል ክስ አሰምተዋል።

የጋራ መግለጫውን ያነበቡት የጦሩ ቃል አቀባይ፤ የኻርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት "የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢትዮጵያ መሳተፋቸውን ማስረጃዎችን መኖራቸውን" እንደተናገሩ የሱዳኑ መንግሥት ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ሙሂ ኤልዲን ሳሌም በበኩላቸው፤ "ጥቃቱ የተፈጸመው ከኢትዮጵያ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል" ብለዋል።

የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ፤ ከአውሮፓውያኑ መጋቢት ወር ወዲህ "ከኢትዮጵያ ባሕር ዳር አየር ማረፊያ የተነሱ ሦስት ድሮኖች ዋይት ናይል፣ ብሉ ናይል፣ ሰሜን ኮርዶፋን እና ደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶች ውስጥ" ጥቃት እንደፈጸሙ በመጥቀስ ከስሰዋል።

ከእነዚህ ድሮኖች አንዱ መጋቢት 8/2018 ዓ.ም. "በአየር መከላከያ ተመትቶ መውደቁን" የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ የሰው አልባ አውሮፕላኑ "መረጃ መተንተኑን እና ለአምራቹ ተቋም ጥያቄ መቅረቡን" ገልጸዋል።

በሁለቱ መንገዶች አማካኝነት ድሮኑ "የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ንብረት መሆኑን እና በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ከባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል" ማለታቸውን የሱና ዘገባ ያመለክታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በኻርቱም አየር ማረፊያ ላይ የደረሰው ጥቃት "የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ የተሳሳተ መንገድ መምረጣቸውን" ያሳያል ብለዋል።

ሱዳን "አዲሱን ማስረጃ እና ማረጋገጫዎች" በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላይ ባቀረበችው አቤቱታ ላይ እንደምታካትት አረስድተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙት የሱዳን አምባሳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚደረግ ምክክር ወደ አገራቸው መጠራታቸውንም ገልጸዋል።

ሚኒስተሩ አክለውም "ሱዳንም በመረጠችው መልኩ እና መንገድ ለተሰነዘረባት ጥቃት ምላሽ የመስጠት ሕጋዊ መብት እንዳላት" በአጽንኦት ማንሳታቸውን ሱና ገልጿል።

የጦሩ ቃል አቀባይም በተመሳሳይ "የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ ሱዳን ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ፈጽመዋል፤ በዝምታ አይታለፍም" ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ የሚነሱ ድሮኖች በግዛቷ ውስጥ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን በመጥቀስ ክስ ስታቀርብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

የአልቡርሃን መንግሥት የካቲት ላይ ባወጣው መግለጫ "ለዚህ ዓይነት ጥቃቶች በሁሉም መንገዶች ምላሽ የመስጠት መብት እንዳለው" በመግለጽ "የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን" አስጠንቅቆ ነበር።

ቢቢሲ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም የቀረቡ ክሶችንም ይሁን አሁኑን በተመለከተ በይፋ ምላሽ አልሰጠም። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በበኩሏ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ ታደርጋለች በሚል የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።