ባለቤቱን እና ሁለት ሴት ልጆቹን በመግደል የተጠረጠረ ግለሰብ መያዙን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አስታወቀ

የ42 ዓመቷ ኖታቦ ዛንዲሌ ቱሹማ፣ የ15 ዓመቷ ናታሊ እና የአምስት ዓመቷ ናላ

የፎቶው ባለመብት, Bedfordshire Police

የምስሉ መግለጫ, የ42 ዓመቷ ኖታቦ ዛንዲሌ ቱሹማ፣ የ15 ዓመቷ ናታሊ እና የአምስት ዓመቷ ናላ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ባለቤቱን እና ሁለት ሴት ልጆቹን በመግደል የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ገለጸ።

ቤድፎርድ በተባለ የአገሪቱ ክፍል በሚገኝ መኖሪያ ቤት የ42 ዓመቷ ኖታቦ ዛንዲሌ ቱሹማ፣ የ15 ዓመቷ ናታሊ እና የአምስት ዓመቷ ናላ ሞተው ተገኝተዋል።

የዚምባብዌ ዜጋ የሆነው ተጠርጣሪ ንዶዳና ምካሄይሲ ቱሹማ በእንግሊዝ ፓስፖርት በሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል መውጣቱ ተገልጿል።

የ45 ዓመቱ ግለሰብ ኪንግስተን፣ ጆሀንስበርግ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ ዩናይትድ ኪንግደም በሦስት የግድያ ወንጀሎች እንደሚከሰስ አስታውቃለች።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ቃል አቀባይ አታሌንዳ ሜቴ ተጠርጣሪው መያዙ "አገሪቱ ለወንጀለኞች መደበቂያ እንዳልሆነች" እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

"አሳድደን እንይዛችኋለን፤ በቁጥጥር ሥር እናውላችኋለን" ሲሉም ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ሰኞ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ እና ለዩናይትድ ኪንግደም ተላልፎ የሚሰጥበት ሕጋዊ ሒደት እንደሚጀመር ቃል አቀባዩ አክለዋል።

የቤድፎርድሺር ፖሊስ ኃላፊ ኢንስፔክተር ሊ ማርቲን "ምርመራው በፍጥነት እየተከናወነ ነው። ብሔራዊ የወንጀል ምርመራ፣ ዓለም አቀፍ የፖሊስ መረብ እንዲሁም የዚምባብዌ እና ደቡብ አፍሪካን ፖሊሶች አሳትፏል" ብለዋል።

ተጠርጣሪው በፍጥነት በቁጥጥር ሥር እንዲውል "ያለመታከት የሠሩ" ባልደረቦቻቸውን አመስግነዋል።

የዩኬ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊት ኤማ ዴቪስ "የቤድፎርድሺር ፖሊስ ያቀረባቸው ማስረጃዎች በጥንቃቄ ከተመረመሩ በኋላ" ክሱ እንደሚመሠረት ገልጸዋል።

"ለኖታቦ፣ ናታሊ እና ናላ ቤተሰቦች መጽናናትን እንመኛለን" ብለዋል።

እናት እና ልጆቿ ለቀናት አለመታየታቸው ያጠራጠራቸው ጎረቤቶች ጥቆማ ሰጥተው ነበር።

ፖሊስ ይፋ ያደረገው የቤተሰባቸው መግለጫ "በዚህ ከፍተኛ የሐዘን ወቅት ያጽናናችሁን፣ የደገፋችሁን እና የፀለያችሁልንን ሰዎች ለማመስገን እንወዳለን" ይላል።

የቤተሰቡ መግለጫ አክሎም "ደግነታችሁ እና ርህራሄያችሁ ለቤተሰባችን ጥንካሬ ሰጥቷል" ይላል።

አምስት ዓመቷ ናላ ትማርበት የነበረው መዋዕለ ሕጻናት ኃላፊ "የፀሐይ ነጸብራቅ የነበረች ልጅ" ሲሉ ገልጸዋታል።

የ15 ዓመቷ ናታሊ የትምህርት ቤት ጓደኞች ደግሞ "ብሩህ እና ስኬታማ" ብለዋታል።

ናታሊ ስፖርተኛ፣ ዳንሰኛ እና ሙዚቀኛ ነበረች።