ግብፅ "ከበባ እና ትንኮሳ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ስትል ኢትዮጵያ ከሰሰች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው

የፎቶው ባለመብት, mofa/fb

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት አጀንዳዋን ይፋ ካደረገች በኋላ ግብፅ "ከበባ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ።

አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ሐሙስ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ካነሳች በኋላ ከግብፅ በኩል "ውጥረት፣ ትንኮሳ የሚመስሉ ነገሮች እየታዩ" መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች በኋላ ባሕር በር አልባ አገር ሆና የቆየችው ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመንግሥት ደረጃ የባሕር በር የማግኘት አጀንዳ በይፋ እየተራመደ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ተበላሽቶ ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል። በተጨማሪም በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ለዓመታት ተቃውሟዋን ስታሰማ የቆየችው ግብፅ ከኤርትራ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ፍላጎት በሚቃረን መልኩ እንቅስቃሴዎችን እና መግለጫዎችን ስታወጣ ቆይታለች።

ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነቢያት ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ባነሳች ጊዜ "ኢትዮጵያን ለማነቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የመጨመር እና የመጠናከር አካሄድ እናያለን" ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ይህ የግብፅ እርምጃ አዲስ እንዳልሆነ በመጥቀስ "ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት አጀንዳዋን" አጠናክራ እንደምትቀጥል በአጽንኦት ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ይህንን ያሉት ቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እና የወደብ ትስስርን በተመለከተ ግብፅ እና ኤርትራ ባለፈው ሳምንት ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።

ሁለቱ አገራት ስምምነቱን ከተፈራራሙ በኋላ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሚመለከተው "የቀይ ባሕር ጠረፍ አገራትን ብቻ" እንደሆነ ጠቅሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት አለመግባባት ውስጥ የገባችው ግብፅ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራለች።

የባሕር በር አጀንዳ በተለያዩ አካላት እና በሕዝቡ ተቀባይነትን ያገኘ ነው ያሉት አምባሳደር ነቢያት፣ ኢትዮጵያ አጀንዳውን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እንደምትቀጥል በተደጋጋሚ መግለጿን አስታውሰዋል።

ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ. ም. የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባድር አብዲላቲ እና የግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ከማል አልዋዚር ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባድር አብዲላቲ ከስምምነቱ በኋላ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ደኅንነት ጉዳይ በዋነኛነት የሚመለከተው የቀይ ባሕር አጎራባች አገራትን ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በተደጋጋሚ የአገራቸውን የባሕር መተላለፊያ የማግኘት ፍላጎት በንግግር እና በመግባባት የማስፈጸም ፍላጎትን አጽንኦት በመስጠት፣ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን በኃይል ለማስፈጸም ጦር እንደማትሰብቅ ተናግረዋል።

ኤርትራ ነጻ አገር ስትሆን ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ በምሥራቅ እና በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንዲሁም ሰፊ የቆዳ ስፍት ኖሯት የባሕር በር የሌላት ትልቋ አገር ከሆነች ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሆኗታል።

አምባሳደር ነቢያት ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል በሳዑዲ አረቢያ እና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ይገኝበታል።

አምባሳደሩ በተለያዩ አገራት በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ጉዳዩን በማንሳት መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ከሳዑዲ አረቢያ ምከትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት በሳዑዲ አረቢያ ለኢትዮጵያውያን "ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ዕድሎች እንዲሰፉ" መጠያቃቸውን ተናግረዋል።

የሳዑዲ አረቢያው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሕጋዊነትን የተከተለ የሥራ ስምሪት በሳዑዲ አረቢያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ደኅንነት መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በኒው ዴልሂ በነበረው የብሪክስ ጉባዔ ወቅት ከደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ ጋር መወያየታቸውን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።

ውይይቱ በተለየ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን በጋራ መፍታት ላይ ያተኮረ እንደነበር አምባሳደር ነቢያት ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስቴር አምባሳዳር ብርሃኑ ፀጋዬ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እና ችግር አስመልክቶ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑትን የደቡብ አፍረካን አምባሳደር በጽህፈት ቤታቸው ማናገራቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ከሆኑት ኖንሴባ ሎሲ ጋር በተደረገው ውይይት በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ያሉ ድርጊቶች እንዲቆሙ በተለይም የደኅንነት ጥበቃ ማድረግ እና ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን መነጋገረቸውን ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም የደቡብ አፍሪካዋ አምባሳደር የአገራቸው መንግሥት የሁሉንም ዜጎች፣ የኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።

አክለውም አንድ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዞ በዚያ ከሚገኙ ከተለያዩ አካላት ጋር እንደሚወያይም ተናግረዋል።