ምግብ አመላላሹ ሹፌር በቻይና ትልቁን የሥነ ጽሑፍ ሽልማት አሸነፈ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ምግብ አመላላሹ ሹፌር (ፉድ ደሊቨሪ ራይደር) ዋንግ ጂቢንግ በግጥም ስብስብ ሥራዎቹ በቻይና ትልቅ የሆነውን ሽልማት አሸነፈ።

ሉ ዡን የተባለውን የሥነ ጽሑፍ ሽልማት የተቀዳጀው 'ሎው ፍላይት' የግጥም ስብስብ መጽሐፉ ሲሆን ምግብ ከምግብ ቤቶች ወደ ግለሰቦች ቤት የሚያመላልሱ አሽከርካሪዎች በሚገጥማቸው የዕለት ተዕለት ተግዳሮት መነሻነት የተጻፈ ነው።

ሉ ዡን ሽልማት የ20ኛው ክፍለ ዘመን የቻይና ሥነ ጽሑፍ አባት ተብለው በሚታወቁት ደራሲ ስም የተሰየመ ነው።

ደራሲው ባህላዊ የሆነውን የቻይና ማኅበረሰብ በሚተቹ ልብ ወለድ መጽሐፎች በይበልጥ ይታወቃሉ።

የ56 ዓመቱ ዋንግ፣ በምግብ ማድረስ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማራው ከሰባት ዓመታት በፊት ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚያጋራቸው ግጥሞቹ እና ዝርው ጽሑፎቹ ተወዳጅነትን ማትረፍ ችሏል።

ዋንግ የሥነ ጽሑፍ ሽልማቱን ያገኘው አስቸጋሪ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ውስጥ አስርት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ነው።

"ማሸነፌ ይፋ ሲሆን፣ በደስታ ትንፋሸን አጥሮኝ ነበር፤ አሁን ሁሉም ነገር ተስተካክሏል" ሲል ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን - ግሎባል ታይምስ ገልጿል።

ሽልማቱን የማሸነፉ ዜና ከወጣ በኋላ ሚዲያዎች ትኩረታቸውን በእርሱ ላይ በማድረጋቸው ተጨናንቆ እንደነበር ተናግሯል።

የሥነ ጽሑፍ ሽልማቱ ምን እንደሆነ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም።

ሆኖም በ2014 በነበረው ሽልማት አሸናፊዎች 100 ሺህ የቻይና ዩዋን ወይም (14 ሺህ ዶላር) ተበርክቶላቸዋል።

በጂያንግሱ ግዛት የተወለደው ዋንግ፣ በገንዘብ ችግር ምክንያት ትምህርቱን ያቋረጠው በታዳጊነቱ ነበር።

ዋንግ ምግብ አመላላሽ ከመሆኑ አስቀድሞም በግንባታ ሥራ እንዲሁም ከቆሻሻ ውስጥ እቃዎችን በመሰብሰብ እና በመንገድ ላይ ንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ነበር።

መጽሐፍ የማንበብና የመጻፍ ፍቅሩ ግን አልተለወጠም።

ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥም ግጥሞቹን እና ሌሎች ዝርው ጽሑፎቹን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲያጋራ ቆይቷል።

ከአራት ዓመታት በፊት የጻፈው 'ማን ኢን ኤ ሃሪ' የተሰኘው ግጥሙም ተወዳጅነትን አትርፎ ነበር።

ይህን ግጥሙን የጻፈው ከሰባት ዓመታት በፊት ባጋጠመውና ደንበኛው የተሳሳተ አድራሻ በማስገባቱ ምግቡን ለማድረስ ያሳለፋቸውን አስጨናቂ ሰዓታት መነሻ በማድረግ ነበር።

ከዚያም በ2003 ' ማን ኢን ኤ ሃሪ፡ ፖይም ኦፍ ኤ ፉድ ደሊቨሪ ራይደር' የሚለውን የመጀመሪያውን የግጥም ስብስቦቹን አሳትሟል።

ዋንግ ሽልማቱን ቢያሸንፍም ሥራውን ማቆም እንደማይፈልግና እስከ 60 ዓመቱ ድረስ ሥራውን የመቀጠል እቅድ እንዳለው ለሚዲያው ተናግሯል።

"ለገንዘብ ይህንን ሥራ መሥራት አልፈልግም፤ ግን የሥራውን ድባብ እወደዋለሁ፤ በአካል ብቁ እንድሆንም አድርጎኛል" ብሏል።

"በጣም ትህትና የተሞላበት ሕይወት መኖር እፈልጋለሁ ፤ ሽልማቱ ይህን ማንነቴን በፍፁም አይለውጠውም።"

በ2024 ያሳተመው 'ሎው ፍላይት' የግጥም ስብስቦቹም የተፃፉት ዋንግ ወደ 200 ለሚጠጉ ምግብ አድራሾች ባደረገው ቃለ መጠይቅ እና ጥናት መነሻነት ነው።

በዚህ ሙያ ላይ የተሰማራው ደራሲ ዋንግ ብቻ አይደለም።

የቀድሞው ምግብ አመላላሽ ሁ አንያን በ2023 ያሳተመው 'አይ ደሊቨር ፓርስልስ ኢን ቤይጂንግ' የተባለው የግል ማስታወሻ በቻይና በብዛት ከተሸጡ መጻሕፍት አንዱ ሲሆን ከአገር ውጭም የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችሏል።

መጽሐፉ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ባለፈው ዓመት ለንባብ በቅቷል።