ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ከፌደራል ተቋማት ጋር ከታክስ ኦዲት ነጻ ለመሆን የገቡት ስምምነት በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፌደራል ኤጀንሲዎች ጋር ከታክስ ኦዲት ነጻ እንዲሆኑ እና በመንግሥት ተቋማት ጉዳት ደርሶብኛል ለሚሉ ግለሰቦች አስተዳደራቸው 1.8 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ የገቡት ስምምነት በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ።
የትራምፕ አስተዳደር 1.8 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ገንዘብ መድቦ የነበረው በመንግሥት አካላት ያለ አግባብ ዒላማ ተደርገናል ብለው አቤቱታ ለሚያቀርቡ ሰዎች በካሳ መልክ እንዲከፈል ነበር።
ነገር ግን በግንቦት ወር ላይ ፕሬዚዳንቱ ከመንግሥት ኤጀንሲዎች ጋር ይህንን ስምምነት የደረሱት የአገር ውስጥ ገቢ ያቀረበባቸውን የ10 ቢሊዮን ዶላር ክስ ውድቅ እንዲያደርግላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ነገር ግን ሰኞ ዕለት በአሜሪካ የዲስትሪክት ዳኛ የሆኑት ካትሊን ዊሊያምስ ለተገቢው ጉዳይ የቀረበ ክስ አይደለም በሚል ውድቅ አድርገውታል።
ዳኛዋ ባለሥልጣናቱ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን መጣሳቸውን እና በሥነምግባር ግድፈት መታየት ይኖርበት እንደሆን እንዲያብራሩ የትራምፕ ጠበቃን ጠይቀዋል።
ትራምፕ ያቀረቡትን ክስ ዳኛዋ እርሳቸው እና ሁለት ልጆቻቸው ከትራምፕ ድርጅቶች ጋር በመሆን እአአ በ2026 ያቀረቡት ክስ በሁለት ተከራካሪ ወገኖች መካከል ካለ ክርክር በእጅጉ የራቀ ነው ብለዋል።
ከዚያ ይልቅ ከትራምፕ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላቸው ጠበቆች እና መንግሥት ዒላማ አድርጎናል በሚሉ ሰዎች የቀረበ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ዊሊያምስ ክሱ "የቀረበው የሕግ መፍትሄ በሚፈልግ ወይም ትክክለኛ አለመግባባት በገጠመው ወገን አይደለም" ከዚያ ይልቅ በትራምፕ እና በሚቆጣጠሩት ተቋም፣ በአይአርኤስ መካከል የቀረበ ነው ብለዋል።
ዳኛ ዊሊያምስ ክሱ ፍትሃዊ ያልሆነን ስምምነት ሕጋዊ ለማስመሰል የቀረበ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ከሆነ ክሱ "ትራምፕን እና ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ከሕጋዊ እርምጃ ለመከላከል የቀረበ እና በመንግሥት ላይ ቅሬታ ላላቸው እና ቅሬታቸው በሕግ ላልተደገፈ ሰዎች በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የታክስ ከፋይ ገንዘብን ለመመደብ ያሰበ ነው" ብለዋል።
አክለውም ትራምፕ እና ልጆቹን እንዲሁም ሌሎች በዚህ ክስ ላይ የተሳተፉ ዳግመኛ በሌሎችየሕግ ክርክሮች ውስጥ ይህንን አቤቱታ እንዳይጠቅሱ ውሳኔው እንደሚከለክል ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህ ውሳኔ መሠረትም የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም ጀምሮት የነበረውን የትራምፕ የታክስ ኦዲት መቀጠል ይችላል።
ትራምፕ በመጀመርያው ክሳቸው ላይ መንግሥት የቀድሞ የአገር ውስጥ ገቢ ባለሙያ የግል የታክስ መረጃቸውን እንዳያሾልክ መከላከል አልቻለም ብለው ነበር።
ትራምፕ በተሸነፉበት ከ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጥቂት ቀደም ብሎ ሾልኮ የወጣ የታክስ መረጃ በኒውዮርክ ታይምስ ታትሟል።
በዚህ ዘገባ መሠረት ትራምፕ በተመረጡበት እአአ በ2016 ለፌደራል መንግሥቱ የከፈሉት የገቢ ግብር 750 ዶላር ብቻ ነው።
ከዚያ በፊት ባሉ 15 ዓመታት ውስጥ በአስሩ ምንም ዓይነት ታክስ አለመክፈላቸውን ዘገባው ይፋ አድርጓል።