የአርቲመስ 2 ጠፈርተኞች ታሪካዊ የጨረቃ ተልዕኳቸውን አጠናቀው ወደ ምድር ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, NASA
የአርቲመስ 2 የጠፈርተኞች ቡድን ታሪካዊ የዘጠኝ ቀን የጨረቃ ተልዕኮውን አጠናቆ በሰላም ወደ ምድር ተመልሷል።
ጠፈርተኞቹ በፓራሹት ተወንጭፈው ፓስፊክ ውቅያኖስ ውሃን ሲነኩ ኮማንደር ሪድ ዋይስማን የቡድኑ አባላት ጤነኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የቡድኑ አባላት ወደ ምድር ከተመለሱ ከ14 ደቂቃ በኋላ በአሜሪካ ምዕራብ ዳርቻ በሚገኘው የፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ አርፈዋል።
ባለሙያዎቹ ከ10 ቀን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመንኮራኩር ወጥተው በጀልባ ተወስደዋል።
በመላው ዓለም በርካቶች ተሰባስበው ይህን ታሪካዊ ክስተት በመመልከት የጉዞው አካል ሆነዋል።
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ናሳ "የሠው ልጅ በሕዋ ለሚያደርገው ምርምር የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ነው" ሲል የጠፈርተኞች ቡድኑ ከተመለሰ በኋላ በሰጠው ማብራሪያ ገልጿል።
የናሳ ኃላፊዎች ተልዕኮው በስኬት መጠናቀቁን ለማብሰር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አራቱም ጠፈርተኞች "ደስተኛ እና ጤነኛ" ናቸው ብለዋል።
የአርቲመስ 2 የጠፈርተኞች ቡድን ወደ መሬት ከባቢ ሲመለሰ የተለመደ ነገር ግን አስፈሪ የሆነ የስድስት ደቂቃ የግንኙነት መቋረጥ አስተናግዷል።
መጋቢት 28/2018 ዓ.ም. መንኮራኩሩ ከመሬት 406,771 ኪ.ሜ ርቀት በመጓዝ የሠው ልጅ በሕዋ ላይ ካደረገው የበለጠ ርቀት በመጓዝ ክብረ ወሰን መስበር ችሏል።
በሕዋ ላይ ጊዜ ማሳለፍ ለጠፈርተኞቹ አካላዊ ድካም የሚያሳድር ሲሆን ሁሉም የቡድኑ አባላት የሕክምና ምርመራ ማድረግ አለባቸው።
ከዚህ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የሚደረጉት ጠፈርተኞቹ፤ ወደ ዋይት ሐውስ እንደሚያቀኑም ይጠበቃል።
በተልዕኮው ወቅት ናሳ ከጨረቃ በጫፍ በኩል የተነሱ ምሥሎችን ይፋ አድርጓል።
በጣም አስደናቂ ከሆኑ ምሥሎች ውስጥ አንዱ ይህ ፎቶግራፍ ነው።

የፎቶው ባለመብት, NASA
ሌላኛው ምሥል ደግሞ ጨረቃ ፀሐይን ስትጋርዳት ያሳያል። ጨፈርተኞቹ ወደ ጨረቃ ሲያመሩ ይህን ግርዶሽ ለ54 ደቂቃ ያህል መመልከታቸውም አስደናቂ ተብሏል።
ከምሥሎቹ በተጨማሪ ጠፈርተኞቹ ትልቅ መረጃ ሰብስበው እንደተመለሱ የተገለጸ ሲሆን መረጃው በሚቀጥሉት ሳምንታት ይተነተናል ተብሏል።
ናሳ እ.አ.አ በ2028 ሁለት ጊዜ ጨረቃ ላይ ለማረፍ ዕቅድ ይዟል። ጠፈርተኞች የአርቲመስ ሁለት ተልዕኮ ሌሎች ስኬታማ ተልዕኮዎች መሻገር ያለባቸው ፈተና እንደሚሆን ከወዲሁ እየተናገሩ ነው።
ከአራት ዓመት በፊት ናሳ ከ2012 እስከ 2025 ባሉት ዓመታት ለአርቲመስ ተልዕኮ 93 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ገልፆ ነበር። ይሁን እንጂ በቅርብ የተደረጉ ስሌቶች ከዚህም በላይ ማውጣቱን ይጠቁማሉ።

የፎቶው ባለመብት, NASA















