የፍርድ ቤት ውሳኔን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ከሥልጣን እንዲለቅቁ ተጠየቀ

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአውሮፓውያኑ 2022 የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዳይከሰሱ የጣለው እግድ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የጣሰ እንደሆነ በፍርድ ቤት መወሰኑን ተከትሎ፤ ቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲለቅቁ ጠየቁ።

የጁሊየስ ማሌማ ፓርቲ የሆነው 'ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ' (ኢኤፍኤፍ) እንዲሁም ሌሎች አካላት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደዋል።

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረትም ራማፎሳ ሊከሰሱ ይችላሉ። ራማፎሳ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ጽሕፈት ቤታቸው ገልጿል።

በደቡብ አፍሪካ ገጠራማ አካባቢ ከሚገኝ የራማፎሳ መኖሪያ ቤት ሶፋ ሥር የተደበቀ 580,000 ዶላር መሰረቁ የተገጸው በ2022 ነበር። ዝርፊያውን ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ ጥያቄዎች ሊቀርቡላቸው እንደሚገባ ገለልተኛ ቡድን አስታውቋል።

ፕሬዝዳንቱ ከቤታቸው የተዘረፈው ገንዘብ ከየት እንደተገኘ አለማሳወቃቸው ውዝግብ አስነስቷል። ራማፎሳ ግን ያልተገባ ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ራማፎሳ ላይ ክስ ለመመሥረት የቀረበውን ሐሳብ የአገሪቱ ምክር ቤት በሰጠው ድምጽ ውድቅ አድርጎታል። ራማፎሳ የሚመሩት 'አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ' (ኤኤንሲ) የተባለው ፓርቲ በወቅቱ በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ አግኝቶ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2024 የተደረገውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ኤኤንሲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጥምረት ያስተዳድራል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተሰማ በኋላ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት "ራማፎሳ ለሕገ መንግሥቱ፣ ለገለልተኛ የፍትሕ አካል እና ለሕግ የበላይነት ታማኝነታቸውን ያረጋግጣሉ" የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ጉዳዩን በተመለከተ ለሚደረግ ምርመራ ፕሬዝዳንቱ "ሙሉ ትብብር" እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

መግለጫ አክሎም "ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ማንም ሰው ከሕግ በላይ እንዳልሆነ ያምናሉ። ማንኛውም ክስ ያለ ፍርሃት፣ ወገንተኝነት እና መድልዎ ሊመረመር ይገባል" ይላል።

ኤኤንሲ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ "ውሳኔው፤ በደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት እና ዴሞክራሲ ውስጥ ተቋማት በገለልተኛነት እንዲሠሩ የመፈቀዱ ውጤት ነው" ብሏል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ማሌማ በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቅቁ ጠይቀዋል።

"ሥልጣን ለቅቀው ክሱ ላይ ማተኮር አለባቸው። ክሱ ስለ እሳቸው ብዙ ይናገራል" ብለዋል። ፕሬዝዳንት መሆን እና ክስን መከታተል ጎን ለጎን እንደማይሄዱም አክለዋል።

ማሌማ ሕገ ወጥ ሽጉጥ ታጥቆ በሕዝብ ፊት በመተኮስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የአምስት ዓመታት እስር የተፈረደባቸው በቅርቡ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ጥምር መንግሥት ውስጥ ሁለተኛው ትልቁ ፓርቲ የሆነው ዴሞክራቲክ አሊያንስ መሪ ጎርደን ሂል-ልዊስ ፖለቲከኞች "የሕግ የበላይነትን ማስከበር አለባቸው" ብለዋል።

በራማፎሳ ላይ ውሳኔ የሰጠው የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ሥራውን "በምክንያታዊነት፣ በፍትሐዊነት እና ሕገ መንግሥትን ተከትሎ" ማከናወን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

ከራማፎሳ ቤት የተሰረቀው ገንዘብ ያስነሳው ውዝግብ በደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን "Farmgate" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ይዞ መገኘትን በተመለከተ ጥብቅ ድንጋጌዎች ወጥተዋል። የውጭ ምንዛሬ በ30 ቀናት ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ገቢ መደረግ አለበት።

ከራማፎሳ መኖሪያ ቤት ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ሦስት ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።