በጃፓን ወንዶች ቢሮ ውስጥ ቁምጣ እንዲለብሱ መፈቀዱን ሴቶች "ፍትሐዊ አይደለም" ብለው ተቃወሙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በጃፓን የበጋው ሙቀት በመባባሱ ምክንያት ወንዶች ቁምጣ ለብሰው ሥራ እየገቡ ነው።

የቶኪዮ ከተማ መስተዳድር፤ መሥሪያ ቤቶች ወንዶች ሱፍ እንዲለብሱ ያወጡትን ሕግ እንዲያላሉ ጫና እያሳደረ ይገኛል። በሱፍ እና ከረቫት ምትክ ቁምጣ እና ካናቴራ መልበስን እንደ አማራጭ አቅርቧል።

የከተማው ከንቲባ ዩሪኮ ኪይኪ መጋቢት ላይ ይፋ ያደረጉት አለባበስ ለበጋው ፀሐይ ተስማሚ የሆነ ነው።

ባለፉት አራት ወራት የወንዶች ለቀቅ ያለ አለባበስ የተለያዩ አስተያየቶች አስተናግዷል።

አንዳንዶች ነጻነት የተሞላውን አለባበስ አድንቀዋል። ሥራ ለማከናወን ምቹ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሴቶች እግራቸውን የሚያሳይ ልብስ ሲያደርጉ ታይት ከውስጥ እንዲለብሱ መገደዳቸው ፍትሐዊ አይደለም የሚል ትችት ተሰንዝሯል።

አንዳንድ ሴቶች የወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸውን የእግር ፀጉር ለማየት መገደዳቸውን ተናግረዋል። "የእግር ፀጉር ለማየት የመገደድ ትንኮሳ" እየደረሰብን ነው ሲሉም ተችተዋል።

የቶኪዮ ከተማ መስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ኖቦሩ ዋታናቤ "በዚህ ከባድ ሙቀት ወቅት ሰዎች የልብስ አማራጭ እንዲኖራቸው ማድረግ እንፈልጋል። የሥራ ቦታ አለባበስ ማንንም እስካላስቀየመ ድረስ ችግር አያመጣም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጎሪላ ክሊኒክ ሰኔ ላይ በሠራው የዳሰሳ ጥናት መሠረት በበጋ ወቅት 53.5% ያህል ሰዎች ቢሮ ውስጥ ቁምጣ መልበስን ሲቃወሙ፣ 46.5% የሚሆኑት ይደግፋሉ።

አለባበሱን የሚቃወሙ ሰዎች ዋነኛ ጥያቄያቸው በወንዶችም ይሁን በሴቶች ላይ ካለው የሰውነት ቅርጽ እና የእግር ፀጉር ጋር የተያያዘ ነው።

በተለይም ሴቶች የወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸውን እግር ማየት አይፈልጉም።

በቅርብ ዓመታት በተለይ በቴክኖሎጂ ተቋማት መደበኛ ያልሆነ አለባበስ እየተዘወተረ ነው።

ዘንድሮ ግን የቶኪዮ ከተማ አስተዳደር ቀላል አለባበስ ማኅበረሰባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጓል። በእርግጥ ወንዶች እግራቸውን ማሳየት እምብዛም ምቶች አይሰጣቸውም።

የጎሪላ ክሊኒክ ኃላፊ አኪፉሚ ፉናትሱ እንደሚናገው ብዙዎች ቁምጣ ሲለብሱ "ማኅበረሰባዊ ተቀባይነት" ያለው መንገድ መከተል ይፈልጋሉ።

ወንዶች "አነስተኛ የእግር ፀጉር ሊኖራቸው ይገባል" ብለው ሴቶች እንደሚያምኑም ያስረዳል።

በዚህም ምክንያት ወንዶች ወደ ክሊኒካቸው በመሄድ የእግር ፀጉራቸውን ያስነሳሉ።

የቶኪዮ ከንቲባ ለመጀመሪያ ጊዜ የአለባበስ ለውጥ እንዲኖር የወሰኑት በአውሮፓውያኑ 2005 ነበር።

ተቋማት አጠር ያለ ካናቴራ መልበስን እንዲፈቅዱ የሚጠይቅ ብሔራዊ ንቅናቄም ጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጁኒቺሮ ከይዙሚን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከረቫት ባለማሰር ቀለል ያለ አለባበስ እንዲለመድ ለማድረግ ሞክረዋል።

በ2011 የቶሆኩ ርዕደ መሬት መነሳቱን ተከትሎ የተጀመረው ብሔራዊ የኃይል ቁጠባ ንቅናቄ በቤት ውስጥ እና በመሥሪያ ቤትም የሚገተበር ሆኗል።

ጃፓን ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ሙቀት አስመዝግባለች። በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ምክንያት የኃይል አቅርቦት ውድነትም እየፈተናት ይገኛል።

የጃፓን የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪሴንቲ ግሬድ በላይ በመሆኑ የአገሪቱ የሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ከፍተኛ ሙቀት የሚመዘገብባቸውን ቀናት በመተመለከተ ለሕዝብ ግንዛቤ ይሰጣል።

በቅርብ ሳምንታት የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሰባት ሰዎች በሙቀት ምክንያት ሞተዋል። ባለፉት ቀናት 4,580 ሰዎች ሆስፒታል ገብተዋል።

ከውሃ መጠጣት እና ሙቀትን የሚከላከሉ መሣሪያዎች ከመጠቀም በተጨማሪ ወበቅን የሚከላከል መሣሪያ የተገጠመላቸው ልብሶች ማድረግን መንግሥት ያበረታታል።

አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም የሚሰጡ እርጥብ ፎጣዎች መጠቀም እንዲሁም የፀሐይ ጨረርን የሚቋቋሙ ዣንጥላዎች መያዝም እየተለመዱ መጥተዋል።

በጃፓን ከፍተኛ ወበቅ ስላለ ሰውነት በላብ አማካኝት ራሱን ለማቀዝቀዝም እንደሚቸገር ባለሙያዎች ይናገራሉ።