አሜሪካ ከ30 ዓመት በፊት ከተከሰከሱ ሁለት አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ የቀድሞ የኩባ መሪ ላይ ክስ ከፈተች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ከ30 ዓመት በፊት በኩባ እና በፍሎሪዳ መካከል ተመተትተው ከወደቁ ሁለት አውሮፕላኖችን ጋር በተያያዘ የቀድሞው የኩባ መሪ ራውል ካስትሮ ላይ የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል ማሴር እና ሌሎች ወንጀሎችን የያዘ ክስ መሠረተች።
ረቡዕ ዕለት ይፋ የተደረገው ክስ ካስትሮ እና ሌሎች አምስት ሰዎች ንብረትነቱ "ብራዘርስ ቱ ዘ ሬስኪው' የተባለው የኩባ አሜሪካውያን ቡድን የሆነ አውሮፕላንን መትተዋል ይላል። በዚህም ሦስት አሜሪካውያንን ጨምሮ የአራት ሰዎች ገድለዋል በማለት ይወነጅላል።
በወቅቱ የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች መሪ የነበሩት የአሁኑ የ94 ዓመት አዛውንት ካስትሮ፤ የአውሮፕላኖቹን መከስከስ ተከትሎ ዓለም አቀፍ ውግዘት አስተናግደው ነበር።
የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል፤ አሜሪካ በአገሪቱ ኮሚኒስት መንግሥት ላይ የምታሳድረውን ጫና እየጨመረች ባለችበት በዚህ ወቅት የቀረበውን ይህንን ክስ "ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው ፖለቲካዊ እርምጃ" ሲሉ ጠርተውታል።
የአሜሪካ ጊዜያዊ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቶድ ብላንች በሰጡት መግለጫ፤ የቀድሞው የኩባ መሪ ላይ አውሮፕላኖችን የማውደም እና አራት የተናጠል ግድያ ክሶች እንደሚመሠረቱ ተናግረዋል።
አቃቤ ሕጓ "አሜሪካ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዜጎቻቸውን ፈጽሞ አይረሱም፤ ወደፊትም አያደርጉትም" ብለዋል።
እነዚህ ክሶች ፍርድ ቤት ውስጥ ክርክር የሚደረግባቸው ሲሆን አንዳንዶቹም እስከ ዕድሜ ልክ ሊያስፈርዱ ይችላሉ። እያንዳንዱ የግድያ ክስ የሞት ቅጣት ወይም የዕድሜ ልክ እስራት ያስወስናሉ።
አሜሪካ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ በምትመራው ኩባ ውስጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ከፍተኛ ጫና እያደረገች ባለችበት በዚህ ወቅት የፍትሕ መስሪያ ቤቱ ያቀረባቸው አዲስ ክሶች፤ የአገሪቱን ኮሚኒስት መንግሥት ቁልፍ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ነው።
በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ የላቲን አሜሪካ ፖለቲካ ባለሙያ የሆኑት ዊሊያም ሊዮግራንድ፤ "እንደሚመስለኝ ስትራቴጂው የኩባ መንግሥት በድርድር ጠረጴዛው ላይ ተስፋ እስኪቆርጥ እና እጅ እስከሚሰጥ ድረስ ጫናውን በሂደት መጨመር ነው" ሲሉ ስለ አሜሪካ እርምጃ ተናግረዋል።
አሜሪካ አገሪቱ ላይ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ ወደ ኩባ ነዳጅ እንዳይገባ አግዳለች። በዚህም ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ እና የምግብ እጥረት ተፈጥሯል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ረቡዕ ዕለት ለኩባ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ እና በአዲሷ ኩባ መካከል አዲስ የትብብር መንገድ እየጠረጉ ነው" ብለዋል።
የኩባ ጦር 'ጂኤኢኤስኤ' የተባለ ግዙፍ ኩባንያ እንደሚመራ ለደሴቷ አገር ዜጎች የተናገሩት ሩቢዮ፤ አገሪቱ እያጋጠማት ላለው የኃይል መቋረጥ እና የምግብ እጥረት ዋነኛ ተጠያቂ ይህ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
'ጂኤኢኤስኤ' በኩባ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ አብዛኛዎቹን የንግድ ሥራዎች የሚያከናውን ሲሆን ወደቦች፣ የነዳጅ ማደያዎች እና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎችን ጭምር ያስተዳድራል።
የኩባው ፕሬዝዳንት ለማርኮ ሩቢዮ መልዕክት በሰጡትት ምላሽ አሜሪካ እየዋሸች እና በኩባ ሕዝብ ላይ የጅምላ ቅጣት እያደረሰች ነው የሚል ክስ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ዲያዝ ካኔል፤ ካስትሮ ላይ የቀረበው ክስ "ኩባ ላይ ለሚፈጸም ወታደራዊ ትንኮሳ" ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ሲሉም ተናግረዋል። አሜሪካ ከአውሮፕላኑ መከስከስ ጋር የተያያዘ እውነታዎችን እያዛባች እንደሆነ በማንሳትም ከስሰዋል።















