የአፋር ግመሎችን ጨምሮ የአፍሪካ 'የበርሃ መርከቦች' ሙቀቱን መቋቋም አልቻሉም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግመሎች በተምዶ የበርሃ መርከቦች በሚል ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ ሙቀት ተቋቋሚዎቹ እንስሳት በአፍሪካ እየጨመረ ያለውን ሙቀት ሊወጡት አልቻሉም።
የኢትዮጵያው አፋር ክልል በዓለም እጅግ ሙቀታማ እና ደረቀ ከሚባሉ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው። በአካባቢው አርብቶ አደሮች በአብዛኛው ጨው የጫኑ ግመሎቻቸውን በበርሃው ይመራሉ።
በሰመራ የሚገኙት ባለ ግመሉ አሊ ዑመር "በከፍተኛ ሙቀቱ ግመሎቼ ሲሰቃዩ ማየት እችላለሁ" ብለዋል ለቢቢሲ።
"እግራቸው መግል ይይዛል፤ ዓይናቸው እንባ ያይዛል እና ሞቃታማው አሸዋ ቆዳቸውን ያቃጥላቸዋል፤ ሲቀመጡ ቆዳቸውን ይበላዋል" ሲሉ 500 ግመሎች ገደማ ያሏቸው የ40 ዓመቱ አሊ ዑመር ተናግረዋል።
"ባለፈው አንድ ወር በከፍተኛ ሙቀቱ ምክንያት ስምንት የግመል ጥጃዎችን አጥቻለሁ። በጣም ከባድ እና አስቸጋሪ እየሆነ ነው።
"ቀዝቃዛ አየር ያመጣ የነበረው ነፋስ አንኳ አሁን ሙቀት ይዞ ነው የሚመጣው" ብለዋል። እንዲህ አይነቶችን በሙቀት ላይ የታዩትን ከባድ ለውጦች በቅርብ ዓመታት መመልከታቸውን ተናግሯል።
አሊ ዑመር እንዲህ ዓይነት ከባድ ለውጦችን የተመለከቱ ብቸኛ ሠው አይደሉም። ተመራማሪዎች፣ የእስንስሳት ደኅንነት ሠራተኞች እና በርካታ ጥናቶች ሁሉም የከፍተኛ ሙቀቱን ቀጥተኛ ተፅዕኖ ጭንቀት፣ ድካም፣ የውሃ እጦት፣ በሽታ አለመቻል እያሉ ይጠቅሳሉ።
ከፍተኛ ሙቀት በተዘዋዋሪ ደግሞ ግመሎች ከፍተኛ የውሃ፣ የእፀዋት እጦት እንዲከሰት የሚያደርግ እና የጥላ ቦታዎችንም ይቀንሳል።

የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images
ሰሜን አፍሪካ እና ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ 80 በመቶው የዓለም ግመል መገኛ ናቸው።
በዚህ ቀጣና የሚኖሩ አርሶ አደሮች እና የግመል አርቢዎች በእንስሳቱ ሙቀት ቻይነታቸው እና በድርቅ ሁኔታዎች ምክንያት ወደ እነዚህ እንስሳት ተሸጋግረዋል።
ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ2025 የግመል አርቢዎች አዝማሚያ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ላይ የታተመ ጥናት ከፍተኛ ሙቀት እና የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭነት በግመሎች ጤና ላይ ጎጂ ተፅፅኖ ማድረሱን ያሳያል።
"ተሳታፊዎች [የግመል አርቢዎች] የአየር ንብረት ለውጥ እና መለዋወጥ የግመሎችን ጤና፣ ምርት እና ተዋልዶ ላይ ተፅዕኖ እንዳደረሰ ሪፖርት አድርገዋል" ይላል።
የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሶማሊያ ሁኔታው የከፋ ይመስላል። ባለፈው ሰኔ የታተመ ጥናት ከድርቅ ጋር የታያያዘ የግመሎች ሞት ሰፊ ቀውስ መሆኑን አሳይቷል። ቀውሱ 46 በመቶዎችን የግመል ባለቤቶችን የጎዳ ነው።
ጥናቱ ስድስት ሺ የሚጠጉ የግመል ባለቤቶችን ያካተተ ሲሆን አብዛኛው የግመል ሞት የተመዘገበው በሰሜን ግዛቶች ነው። "73 በመቶ አስደንጋጭ የሞት ምጣኔ ታይቷል።"
ከፍተኛ ሙቀት በክልሉ ላለው ድርቅ ምልንያት ቢሆንም በቂ የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት አለመኖር እና የእንስሳት አስተዳደር ሁኔታዎች ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል ይላሉ ባለሙያዎች።
ተመራማሪዎች በክልሉ ያለው ከፍተኛ ሙቀት ከ2021 እስከ 2022 ለነበረው ድርቅ ስረ መሠረት ነው። ከፍተኛ ሙቀት ከመሬት እና ከረግረጋማ ቦታዎች ውሃ እንዲተን እና እፀዋት የሚለቁት ውሃ ወደ አየር እንዲተን ያደርጋል።
የእንስሳት ሐኪሞች የታመሙ ግመሎች ቁጥር እንደጨመረ እና በከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ሞት እያዩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያን በሚጎራበተው የኬንያ መርሳቤት ግዛት የእንስሳት ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ሀሰን ኑያ ጉዮ ለቢቢሲ "በግመሎች ከባድ ሙቀት (ሀይፐርተርሚያ) በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እያየን ነው። በዚህ ምክንያት በተለያዩ ኢንፌክሺኖች [በሽታዎች] ይታመማሉ" ብለዋል።
"ባለፉት ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ሙቀት በአገራችን የግመሎች ሞት ከ15 በመቶ በላይ መጨመሩን አይተናል።"
በግመሎች የበሽታ ሥርጭት እና የወተት ምርት መቀነስ የአየር ንብረት መለወጥ ውጤቶች ናቸው ይላል በአፍሪካ ቀንድ የተሰራ ሌላ ጥናት።
ተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜን አፍሪካ እየታየ ነው። በአልጄሪያ ባለፈው ዓመት የተሰራ አንድ ጥናት በበጋ የሙቀት ማዕበሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግመሎች እየሞቱ እንደሆነ አሳይቷል።
"የጊዜ ትንታኔዎች በወቅቶች ጉልህ የሆነ የሞት አዝማሚያ ያሳያሉ፤ ስለዚህም ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው እንደ የበጋ ወራት ያሉ ወቅቶችን ዒላማ ያደረገ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ስልታዊ የሆነ የውሃ አቅርቦት፣ የምገባ ድጋፍ እና የሽታዎችን ቅኝት መጨመር" ይላሉ።
የዓለም የሜትሪዮሎጂ ኤጄንሲ ከፍተኛ ሙቀት በበርካታ የሰሜን አፍሪካ አገራት መደበኛ ሁኔታ ሆኗል ይላል። የሙቀት ሞገድ ከእ.አ.አ ከ1981 ወዲህ ወደ ላይ እያሻቀበ ነው።
በቀጣናው እና በመካከለኛው ምሥራቅ በርካታ አገራት በ2024 ከ50 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት ሪፖርት አድርገዋል ብሏል።
ባለሙያዎች ግመሎች ለ40 ድግሪ ገደማ ሙቀት የተመቻቹ እንደሆኑ ሲገልፁ እንስሳቱ የውጫዊ ሙቀቱን ለመከላከል የሰውነታቸውን ሙቀት በተለያዩ ድግሪዎች መለዋወት ይችላሉ።
ይህን በማድረግ ላብ እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። የተጠራቀመ የሽንት እና ደረቅ ሰገራ ጋር ተዳምሮ የውሃ ብክነትን ለመቀነስ ይረዳቸዋል። ወፍራም የቆዳ መሸፈኛቸው ደግሞ የፀሐይ ጨረርን ለመከላከል ይረዳቸዋል።
የዓለም የምግብ እና ግብርና ድርጅት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሞሐመድ ብንጉሚ በግመል ጤና ላይ አተኩረው የሚሰሩ ናቸው። " ይሁን አንጂ ግመሎች አየሩ ከምቾት ደረጃቸው በላይ ሲጨመር የሙቀት ድካም ያሳያሉ" ይላሉ።
"በበርካታ የሰሃራ አካባቢዎች የበጋ ሙቀት አሁን ከ50 ድግሪ በላይ አልፏል፤ ይህም የከፍተኛ ሙቀት የድካም ስጋትን ይጨምራል። በዋናነት የዕፀዋት ሽፋን መቀነስ፣ የውሃ እጥረት እና የጥላ እጦት ሲጨመርበት ከፍ ይላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Nuya Guyo
በአልጄሪያ ጋራዳይ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አብደልመጂድ ቸማ ተመሳሳይ ድምዳሜ አላቸው።
"ሥራችን ረጅም የቀን እና የምሽት ሙቀት ከ41 እስከ 45 ድግሪ በቀጥታ ህዋሳቸውን ይጎዳል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በሽታ የመከላከል አቅማቸው ይጉዳል። ምክንያቱም እንዲህ አይነት የሙቀት ደረጃ ቀይ የደም ህዋሳቸውን እና ሌሎችንም ይጎዳል። የደም ህዋሶች ራሳቸውን ለመጠገን ይቸገራሉ እና ራሳቸውን ይጎዳሉ።"
ለግመሎች ሙቀቱ ሲበረታባቸው ሰውነታቸው ውስጣዊ ሙቀት ማመንጨቱን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ ምግብ መውሰዳቸውን በመቀነስ አደገኛ ሁኔታ እና አጠቃላይ ድካም ይሰማቸዋል።
ይህ ደግሞ የወተት ምርታቸው እንዲቀንስ እና የስነ ተዋልዶ መዛባት እንዲከሰት ያደርጋል።
በሞሮኮ ካዛብላንካ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ሃይድሮባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሞሐመድ ኤል ካሲሚ የሙቀት ጭንቀት ተፅዕኖዎችን በሚመለከት ረጅም ዝርዝሮች አሏቸቸው።
የክብደት መቀነስ፣ እብጠት፣ ጡንቻ እና የአጥንት ህመም፣ በኩላሊት በአግባቡ አለመስራት የኬሚካል ሚዛን መዛባት፣ በተህዋሲያን የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች ከዝርዝሮች ውስጥ ይገኙበታል ይላሉ።
የዚህ ሁሉ ጦስ ከፍተኛ ሙቀት ቢሆንም ተፅዕኖው እንደ የእፀዋት እና ውሃ እጦት፣ የጥላ ቦታዎች ማጣት እና በቂ የሕክም አገልግሎት አለማግኘት ሲጨመሩበት እጅግ ከባድ ይሆናል ይላሉ ባለሙያዎች።
ለዚህም ነው በርካታ የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን ከታሪካዊ መገኛቸው ከሰሜን ኢትዮጵያ ውሃ እና እፀዋት በተሻለ መልኩ ወደሚያገኙበት ደቡብ ኢትዮጵያ እንዲያዘዋወሩ የተገደዱት።
የቪዢን ዩኒቨርስቲ የአርብቶ አደሮች ልማት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳንኤል ገላን " ይህ የአርብቶ አደሮች ወቅታዊ ዝውውር አይደለም" ይላሉ።
"ሰሜናዊ ክልሉን ለመጨረሻ ጊዜ እየለቀቁ ነው። ምክንያቱም በከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ በአካባቢው ግመልን ማርባት ከዚህ በኋላ ባለመቻላቸው ነው" ብለዋል ለቢቢሲ።
የአፍሪካ ቀንድ ከ2020 እስከ 2023 ከተከሰተው ረጅም እና በጣም ከባድ ድርቅ እያገገመ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ረድኤት ድርጅቱ ኦክስፋም አሁንም ሌላ ዙር ከባድ ሁኔታ እየጋጠመው ነው።
በድርቁ ምክንያት በአንዳንድ የሶማሊያ ክፍሎች የውሃ ዋጋ በሁለት ሺ በመቶ ከፍ እንዳለ ገልጿል።
የአፋሩ አርብቶ አደር አሊ ዑመር በሽታ ተቀስቅሶ ግመሎቹ በማንኛውም ጊዜ ሊገድል እንደሚችል ስጋት አድሮባቸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ቸካ ከሆነ ስጋታቸው እውነት ነው።
የግመሎች ታሪካዊ ሙቀት ተቋቋሚነት ለበረሃማ አካባቢዎች ዋነኛ ተፈላጊ ቢያደርጋቸውም አሁን የአየር ንበረት ሰለብተኞች ሆነዋል ብለዋል።















