ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ አሜሪካ የሚበር አውሮፕላን ኢቦላ ከተከሰተበት አካባቢ የመጣ ሰው 'በስህተት' በማሳፈሩ ወደ ካናዳ እንዲሄድ ተደረገ
ከፓሪስ ወደ ዲትሮይት የሚበር አውሮፕላን በኢቦላ ከተጠቃችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመጣ አንድ ተሳፋሪ "በስህተት" በአውሮፕላኑ በመሳፈሩ ወደ ካናዳ አቅጣጫ ለመቀየር ተገዷል ሲሉ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
አሜሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመገደብ ባወጣችው ገደቦች ምክንያት ተሳፋሪው በኤር ፍራንስ አውሮፕላን ላይ መጓዝ አልነበረበትም ሲል የአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ (ሲቢፒ) ኤጀንሲ ለቢቢሲ ገልጿል።
በመካከለኛው አፍሪካ በተፈጠረው ወረርሽኝ ወደ 140 የሚጠጉ ሰዎች በኢቦላ እንደሞቱ የሚታመን ሲሆን ከ600 በላይ የተጠረጠሩ ሰዎችም ተገኝተዋል።
ባለሥልጣናቱ ግለሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የነበረበትን ጊዜ አልገለጹም። የካናዳ የጤና ባለሥልጣናት ተሳፋሪው ምልክቶች እንዳላሳየ እና ተመልሶ ወደ ፈረንሳይ እንደተላከ ተናግረዋል።
"የካናዳ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ባለሙያዎች ተጓዡን መርምረው ምልክት እንደማያሳይ አረጋግጧል" ሲል የካናዳ ጤና ተቋም በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) መሠረት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ኢቦላን ሊያሰራጩ የሚችሉት ምልክቶቹ መታየት ከጀመሩ በኋላ ብቻ ነው። ምልክቶቹ ግለሰቦቹ ከተጋለጡ ከሁለት እስከ 21 ቀናት ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ።
አብራሪውን የጉዞ ለውጡን ካሳወቀ በኋላ ተሳፋሪዎቹ የፊት ጭምብል አጥልቀዋል ስትል በበረራው ላይ የነበረች አንዲት ተሳፋሪ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግራለች።
ተሳፋሪዎች ወደ ማረፊያ ከመድረሳቸው አራት ሰዓታት በፊት ስለ ለውጡ እንደተነገራቸው ዴቦራ ሚስተር ተናግረዋል። "ሰዎች ምን እየተከናወነ እንዳለ ሲጠይቁ ነበር ብዬ አስባለሁ ምክንያቱም ከ30 ደቂቃዎች በኋላ [አብራሪው] በአውሮፕላኑ ላይ ምንም ችግር እንደሌለ፣ ምንም የቴክኒክ ችግር አንዳላጋጠመ፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሜሪካ እንዳናርፍ ባለመፍቀዳቸው ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ እንደፈለገ ተናግሯል" ብላለች።
በራሱ አውሮፕላን መንገደኞቹ ወደ ዴትሮይት እንደበረሩ አክላለች።
ኤር ፍራንስ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንዳረጋገጠው "በአሜሪካ ባለሥልጣናት ጥያቄ መሠረት በአውሮፕላኑ ላይ የነበረ የኮንጎ ተሳፋሪ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ከተከለከለ በኋላ [በረራው] ወደ ሞንትሪያል አየር ማረፊያ ተዛወረ።"
የአሜሪካ የድንበር ኤጀንሲ ሲቢፒ "ኤር ፍራንስ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ አሜሪካ የሚበር አንድ መንገደኛን በስህተት አሳፍሯል" ብሏል።
ኤጀንሲው በዲትሮይት ሜትሮፖሊታን ዌይን ካውንቲ አየር ማረፊያ ላይ የሚያርፈውን አውሮፕላን ለማስቆም "ቆራጥ እርምጃ" እንደወሰደ ተናግሯል። ወደ ሞንትሪያል፣ ካናዳ አቅጣጫውን ቀይሮታል።
አሜሪካ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን ወይም ኡጋንዳ የነበሩ የአሜሪካ ፓስፖርት የሌላቸው ሰዎች ላይ የመግቢያ ገደብ እየጣለች ነው።
በእነዚያ አገሮች የነበሩ የአሜሪካ ፓስፖርት ያላቸው እና ቋሚ ነዋሪዎች የተሻለ ምርመራ ለማድረግ ቨርጂኒያ በሚገኘው ዋሽንግተን-ዳለስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ብቻ መግባት ይችላሉ።
የአሁኑ የኢቦላ ወረርሽኝ በዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ ስጋት የኅብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ተብሎ ታውጇል።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል፤ በሽታው ለአሜሪካ ያለው አደጋ በአንጻራዊነት ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቆ ነገር ግን በሽታው ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ለመከላከል እርምጃዎችን እንደሚወስድ ገልጿል።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከሚገኝ የሕክምና ቡድን ጋር ይሠራ የነበረ አንድ አሜሪካዊ በተደገለት ምርመራው ፖዘቲቭ ሆኖ ተገኝቷል። በጀርመን በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በልዩ የለይቶ ማቆያ ክፍል ውስጥ እየታከመ ይገኛል።