እስራኤል ለመጀመርያ ጊዜ በጦር ቀጣናዎች በተፈጸመ ወሲባዊ ጥቃት ስሟ በመንግሥታቱ ድርጅት ዝርዝር ውስጥ ተካተተ

በጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ የሚገነው ስዴ ቴይማን እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ወታደር ከጋዛ ተወስዶ በስዴ ቴይማን ማቆያ ውስጥ የታሰረ ፍልስጤማዊ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ሊፈጽም ሲል በደህንነት ካሜራ ታይቷል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል ለመጀመርያ ጊዜ በጦር ቀጣናዎች በተፈጸመ ወሲባዊ ጥቃት ስሟ በተባበሩት መንግሥታት ጥቁር መዝገብ ዝርዝር ውስጥ ተካተተ።

የአንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቢሮ እንዳስታወቀው የመንግሥታቱ ድርጅት ባለፈው ዓመት 31 በእስራኤል ወታደሮች በጋዛ እና ዌስት ባንክ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን አጣርቷል። 13ቱ ወንጀሎች የተፈጸሙት እአአ በ2025 ሲሆን 18ቱ ደግሞ ከዚያ በፊት ባሉት ሁለት ዓመት የደረሱ ናቸው።

የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርቱ እንደ አጠቃላይ ሳይሆን "የክስተቶቸ እና ሁኔታዎች አመለካች" ተደርገው መታየት አለባቸው ብሏል።

እስራኤል የወሲባዊ ጥቃት ውንጀላውን ውድቅ ማድረጓን ገልጻ ከመንግሥታቱ ድርጅት ኃላፊ ቢሮ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ ማሰቧን አስታውቃለች።

በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ሐሙስ ዕለት ጉቴሬዝን "ፀረ ሴማዊ ውሸቶችን" በማሰራጨት ከስሰዋል። የእስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ የመንግሥታቱ ድርጅት ኃላፊ ሆነው እስካገለገሉ ድረስ ከቢሯቸው ጋር ግንኙነት እንደማይቀጥል አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ጾታዊ ጥቃቶቹ በ14 ወንዶች፣ በሰባት ሴቶች፣ በዘጠኝ ታዳጊ ወንዶች እና በአንዲት ሴት ልጅ ላይ የተፈጸሙ መሆናቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።

ጥሰቶቹ አስገድዶ መድፈር፣ በቡድን አስገድዶ መድፈር፣ በግዳጅ እርቃን ማድረግ እና በእስራኤል ጦር፣ የፖሊስ እና የማረሚያ ቤት አገልግሎት መኮንኖች የመራቢያ አካላት ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ያካትታሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ለመመርመር የሚያደርገው ሙከራ በእስራኤል መንግሥት እና የደረሰባቸው ጥቃትን እንዳይናገሩ በእስረኞች ላይ የደረሱ ማስፈራሪያዎች እንቅፋት እንደሆኑበት አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ዓመት ሐማስ ከዚህ ቀደም በነበረው "ከግጭት ጋር የተያያዘ የወሲብ ጥቃት" ሪፖርት ውስጥ ስሙ ተካትቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው ከዚህ ቀደም በጋዛ ሐማስ አግቷቸው የነበሩ እና የተለቀቁ 12 ሰዎች የጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የእስራኤል መንግሥት የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ወደ ስፍራው በመሄድ ምርመራ እንዳያደርጉ በመከልከሉ ዘገባዎቹን ማረጋገጥ አልቻለም።

ጉቴሬዝ በወቅቱ በርካታ ክሶችን ለመመርመር እና የፍልስጤማውያንን የእስር ሁኔታ ለማሻሻል እርምጃዎችን እንድትወስድ ለእስራኤል "ማሳሰቢያ" መስጠታቸውን ተናግረዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጉዳዮች በፍልስጤማውያን ታሳሪዎች ላይ የፆታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን አመልክተዋል።

በበርካታ መገናኛ ብዙኃን የተዘገበው እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተመለከቱት አንድ ክስ አምስት የእስራኤል ወታደሮች በሴዴ ቴይማን እስር ቤት ውስጥ ከጋዛ የመጣ እስረኛ ላይ ጾታዊ ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳይ በደህንነት ካሜራ የተቀረጸ ምስል ሾልኮ ወጥቷል።

ግለሰቡን የመረመረው ዶክተር በፊንጢጣው ላይ ቁስሎች መኖራቸውን አረጋግጧል። ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረት ቢስብም የእስራኤል ከፍተኛ ወታደራዊ ጠበቃ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር በጠባቂዎቹ ላይ የቀረቡትን ክሶች አቋርጧል።

ባለፈው ታሕሳስ ሁለት ፍልስጤማውያን ወንዶች በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ሳሉ ሲፈጸምባቸው በነበረው ማሰቃየት ውስጥ የጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእስራኤል ማረሚያ ቤቶች አገልግሎት በወቅቱ "ሕጉን ሙሉ በሙሉ በሚያከብር መልኩ" እንደሚሰራ ለቢቢሲ ተናግሮ ስለቀረቡት ውንጀላዎች እንደማያውቅ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸረ ማሰቃየት ኮሚቴ በኅዳር ወር በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ "በተደራጀና በስፋት በሚፈጸም ማሰቃየትና በደል" በሚመለከት የሚደርሱት ሪፖርቶች በጣም እንደሚያሳስበው ተናግሯል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፍቶ በርካቶችን አግቶ ከወሰደ በኋላ እንዲህ ዓይነት ክሶች "ተጠናክረዋል" ተብሏል።

በቅርቡ ደግሞ በኒውዮርክ ታይምስ የታተመ ከወሲብ ጥቃት የተረፉ 14 ፍልስጤማውያን ምስክርነት የእስራኤል መንግሥት ቁጣን ቀስቅሷል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሰዓር በጋራ ባወጡት መግለጫ በጋዜጣው ላይ የስም ማጥፋት ክስ እየመሰረቱ መሆኑን በመግለጽ ዘገባውን "በዘመናዊው ፕሬስ ውስጥ በእስራኤል መንግሥት ላይ ከታተሙት እጅግ አስከፊ እና የተዛቡ ውሸቶች አንዱ" ሲሉ ጠርተውታል።

በጋዛ በተካሄደው ጦርነት ወቅት በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የእስራኤል ወታደሮች ለፈጸሙት በደል ተጠያቂ አለመሆን እና አለመከሰስን በማንሳት ተችተዋል።

ባለፈው ዓመት አክሽን ኦን አርምድ ቫዮለንስ የተሰኘው የምርምር ድርጅት እንዳመለከተው፣ ከጋዛ ጦርነት መጀመሪያ ጀምሮ የእስራኤል ወታደሮች በፈጸሙት ወንጀል ላይ ከተደረጉት 10 ምርመራዎች ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑት ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸው ሳይረጋገጥ ወይም መፍትሄ ሳያገኙ ተዘግተዋል። ከተጠኑት 52 ጉዳዮች ውስጥ አንድ ክስ ብቻ የእስር ቅጣት ተፈጽሞበት ማግኘቱን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

የእስራኤል ጦር ለሪፖርቱ ምላሽ ሲሰጥ "በዘመቻ ወቅት የተከሰቱትን እና ሕግ መጣሱን የሚያሳዩ ጥርጣሬዎች ሲኖሩ ምርመራ እናካሄዳለን" ብሏል።

"በእስራኤል ሕግ እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ባለው ግዴታ መሠረት" ወንጀል ስለመፈጸሙ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር የወንጀል ምርመራ እንደሚጀመር አክሏል።

የሩሲያ ወታደሮች ስማቸው ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፈረ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ጦር እና የጸጥታ ኃይሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በዩክሬን ጦርነት ወቅት በጦር እስረኞች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመው የጾታ ጥቃት ምክንያት ስማቸው በጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍሯል።

ጉታሬዝ ባለፈው ዓመት ለሩሲያ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።

በሩሲያ እና በሩሲያ በተያዙ የዩክሬን ግዛቶች የተፈጸሙ አስገድዶ መድፈር እና የብልት መቆረጥን ጨምሮ ከግጭት ጋር የተያያዙ 310 የወሲብ ጥቃቶችን መለየቱን አስታውቋል። ይህም 280 ወንዶችን፣ 26 ሴቶችን እና አራት ታዳጊ ሴቶች ላይ የደረሰ መሆኑን አመልክቷል።

በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ጦርነቱ የተጀመረው እአአ በ2022 የካቲት ወር ነው።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ ሪፖርቱን በደስታ ተቀብለው "ወደ እውነት እና ተጠያቂነት ለሚወስደው መንገድ ወሳኝ እርምጃ ነው" ብለዋል።

ሩሲያ ስለውንጀላው በይፋ አስተያየት አልሰጠችም።