አሜሪካ በኤርትራ ላይ ጥላቸው የቆዩ ማዕቀቦች የትኞቹ ናቸው? በተለይ እነማንን ይመለከታሉ?

አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ልታነሳ እንደሆነ የሚገልጽ የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰነድ መመልከቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል አስታውቋል።
የአሜሪካ ውሳኔ ከአሥመራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እና ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት እንዳትገባ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው ሲሉ ተንታኞች መናገራቸውን የዜና ወኪሉ ዘገባ ያመለክታል።
አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች የምታነሳ ከሆነ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ልትወስድ የምትችለውን የኃይል እርምጃ እንደማትደግፍ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ዲፕሎማቶች መናገራቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል።
አሜሪካ እና ኤርትራ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረቱት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ማወጇን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1993 ገደማ ነበር።
በኤርትራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ የነጻ መገናኛ ብዙኃን አፈና፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች የሚገጥማቸው ጫና እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የዋሽንግተን እና የአሥመራን ግንኙነት እንዳሻከሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በድረ ገጹ አስፍሯል።
በትግራይ ጦርነት የኤርትራ ወታደሮች የፈጸሟቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ እንዳሻከሩትም ድረ ገጹ ያትታል።
ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት እልባት እንዲያገኝ ከፍተኛውን ድርሻ ከተወጡት መካከል አሜሪካ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።
ለአስርታት በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከፍተኛ ለውጥ ቢያሳይም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተበላሽቶ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄ በማንሳቷ የሁለቱ አገራት ውጥረት ተባብሷል።
በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን አሜሪካ ስታሞገስ ነበር።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ ግን የሁለቱ አገራት መቃቃር የጦርነት ስጋትን እስከማጫር የደረሰ ሆኗል።
ሮይተርስ ያወጣው ዘገባ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንዳቸው በሌላኛቸው ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ባላቸው "አለመረጋጋትን የሚፈጥር ተሳትፎ" የተነሳ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ይጠቁማል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ዎል ስትሪት ጆርናል የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እያሰበች መሆኑን የአገሪቱን ባለሥልጣናት ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
ዋሽንግተን በአሥመራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች የማንሳት ሂደት ለመጀመር ፍላጎት እንዳላት እንዲሁም የአገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ግምገማ እደያረገች እንደሆነ ዘገባው አትቷል።
የአሜሪካ እና የኤርትራ ግንኙነት
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኤርትራ በትግራይ ጦርነት ከነበራት ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ከአምስት ዓመት በፊት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ከሰሞኑ ሮይተርስ የተመለከተው የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰነድ ኤርትራን ጨምሮ በርካታ አገራትን የሚመለከቱ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች እና ማዕቀቦች በቀናት ውስጥ እንደሚነሱ አመልክቷል።
በኢራን ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ከእስያ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ለሚደረገው የባሕር ላይ ንግድ አሜሪካ በቀይ ባሕር ላይ የሚኖራት ቁጥጥር ጉልህ ሥፍራ የሚኖረው ይሆናል።
አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያው ግንኙነት በማደስ በቀጣናው "ስትራቴጂክ አጋር" የማድረግ ፍላጎት እንዳላትም ተመልክቷል።
አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸው ማዕቀቦች መነሳት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ነቀፌታ አስከትሏል።
የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባን ተከትሎ በኤርትራ ባለው የሰብአዊ መብት አያያዝ እና በቀጣናው በሚካሄዱ ግጭቶች ውስጥ ባላት ሚና የተነሳ የተለያዩ ወገኖች አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ማሰቧን የሚቃወሙ ትችቶች ተሰንዝረዋል።
ይህንንም ተከትሎ በዋሽንግተን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ፣ በአሜሪካ እና በኤርትራ መካከል ባለው ግንኙነት መሻሻል ላይ የሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶችን የሚተች መግለጫ አውጥቷል።
ከዚህ ቀደም ግን የኤርትራ መንግሥት አሜሪካን በጽኑ በመተቸት እና በማውገዝ ይታወቃል።
በአውሮፓውያኑ 1995 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ሲያስተናግዱ "በአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ተስፋ ከተጣለባቸው መሪዎች አንዱ" ሲሉ ነበር የገለጿቸው።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ የአሜሪካ እና ኤርትራ ግንኙነት ሻክሯል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስን የተቃወሙ እና የተቹ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እና ጋዜጠኞች መታሰር የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ አጠልሽቷል።
በአውሮፓውያኑ 2001 በአሥመራ ሁለት ኤርትራውያን የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች መታሰራቸው ደግሞ መቃቃሩን አባብሶታል።
አሜሪካ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት በማስቆም እንዲሁም በአልጀርስ ስምምነት ጉልህ ድርሻ የነበራት አገር ብትሆንም የአሥመራ እና የዋሽንግንተን ግንኙነት ለዓመታት ሳይሻሻል ዘልቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸው ማዕቀቦች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ መሠረት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በአውሮፓውያኑ 2021 በኤርትራ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ማዕቀቦች ተጥለዋል።
ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ (E.O.) 13818 እና 14046 በተሰኙ ትዕዛዞች አማካኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ማዕቀቦች መጣላቸው ተገልጿል።
የአሜሪካ ፍላጎት "ኤርትራ ቀጣናዊ መረጋጋትን እንዳታውክ መከላከል፣ አገሪቷ ዴሞክራሲን ወዳማከለ የፖለቲካ ሥርዓት እንድትሻገር ማስቻል፣ የሃይማኖት ነጻነትን ጨምሮ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር እንዲሁም የምጣኔ ሃብት እድገትን ማረጋገጥ" እንደሆነ ድረ ገጹ ከአራት ዓመታት በፊት ያወጣው ጽሑፍ ይጠቁማል።
በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2021 የአሜሪካ መንግሥት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (ህግዴፍ) እንዲሁም ከፓርቲው ጋር ትስስር ባላቸው ህድሪ ትረስት እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ላይ ማዕቀብ ጥሏል። በተጨማሪም በኤርትራ መከላከያ ኃይል እና በሁለት ከፍተኛ የኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ ዕቀባ ተጥሏል።
ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ህድሪ ትረስት (ህድሪ) የተባለው ድርጅት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህግዴፍ የተመሠረቱ ሁሉንም የንግድ ተቋማት በሥሩ ያቀፈ ነው።
በማዕቀብ ውሳኔው ውስጥ የተካተተውም የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ አንድ ክፍል ወይም መጠቀሚያ በመሆን በኤርትራ መንግሥት ወይም በፓርቲው የባለቤትነት ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ነው።
ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን የህግዴፍን ንብረቶችና ገንዘብ የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ለፓርቲው ገንዘብ የሚያቀርብ እና የንግድ ድጋፍ የሚሰጥም ነው።
ኮርፖሬሽኑ ማዕቀብ ውስጥ የተካተተው በኤርትራ ገዢ ፓርቲ (ህግዴፍ) የምጣኔ ሀብት አማካሪ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን (ገብረሕይወት) ባለቤትነት ወይም ቁጥጥር ሥር ያለ በመሆኑ ነው።
በአውሮፓውያኑ ግንቦት 2021 ላይ የአሜሪካ መንግሥት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ሥልጣን ላይ ያሉ እና ቀድሞ ባለሥልጣን የነበሩ ኤርትራውያን ላይ የቪዛ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታውቋል።
በተበባሩት መንግሥታት የኤርትራ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም ማዕቀቡን "ሕገ ወጥ" እና "ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው" ሲሉ ኮንነውት ነበር።
የአሜሪካ ዕቀባ ያነጣጠረባቸው እነማን ናቸው?
የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ የጣለው በአራት የኤርትራ ተቋማት እና በሁለት ኤርትራውያን ባለሥልጣናት ላይ ነው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት በወቅቱ በድረ ገጹ ባወጣው ጽሑፍ ላይ እንደሰፈረው በፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ (E.O.) 14046 አማካኝነት ኤርትራውያኑ ተቋማት እና ግለሰቦች ማዕቀብ የተጣለባቸው "ለኢትዮጵያ ደኅንነት እና አንድነት ስጋት በመደቀናቸው" ነው።
ባለሥልጣናቱ የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አብርሃ ካሳ ነማርያም (ካሳ) እና የኤርትራ ገዢ ፓርቲ የምጣኔ ሃብት አማካሪ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን ናቸው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት በአውሮፓውያኑ 2021 ባወጣው ጽሑፍ ማዕቀቡ "በቀጣናው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀውስ ውስጥ የከተቱ አካላትን ዒላማ እንዳደረገ" አስታውቋል።
በጽሑፉ ላይ "የኤርትራ ኃይሎች በግጭቱ ውስጥ በኢትዮጵያ በጭፍጨፋ፣ በዝርፊያ እና በወሲባዊ ጥቃት ተጠያቂ ናቸው" ብሏል።
የኤርትራ መከላከያ ኃይል ላይ ማዕቀብ የተጣለው "ከዝርፊያ፣ ከወሲባዊ ጥቃት፣ ከንጹኃን ግድያ እና ሰብአዊ እርዳታን ከማስተጓጎል" ጋር በተያያዙ ክሶች መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት የኤርትራ ብቸኛው ፓርቲ የሆነው ገዢው ፓርቲ ማዕቀብ የተጣለበት "በቀጥታ ለመከላከያ ኃይሉ በሚያስተላልፋቸው ትዕዛዞች" ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።
የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አብርሃ ካሳ ነማርያም ባላቸው የከፍተኛ ኃላፊነት "በሰሜን ኢትዮጵያው ቀውስ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ" ባላቸው ድርሻ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው የአሜሪካ ግምጃ ቤት መረጃ ይጠቁማል።
የኤርትራ ገዢ ፓርቲ የምጣኔ ሃብት አማካሪ እንዲሁም የሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን ላይ ማዕቀብ የተጣለው ለፓርቲው ከተሰጠ "የፋይናንስ ግብዓት እና የቴክኒክ ድጋፍ" ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆነው ህድሪ ትረስት እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽንም በማዕቀቡ ውስጥ ተካተዋል።
በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2021 ላይ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ የኤርትራ ጦር ኃይል ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊልጶስ ወልደዮሐንስ "የጅምላ ግድያ፣ ዝርፊያ እና ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ" ማዕቀብ እንደተጣለባቸው አስታውቋል።
ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ በአሜሪካ ውስጥ ባላቸው ንብረት እና ገንዘብ ላይ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ዕቀባ መጣሉ ይታወሳል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ
በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 23/ 2009 የተባበሩት መንግሥታት ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ (Resolution 1907) መሠረት ኤርትራ በሶማሊያ አል-ሻባብን በመደገፍ ተከስሳ ማዕቀቦች ተጥለውባታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን ሐሳብ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) መደገፋቸውን ተከትሎ የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን አጽድቋል።
በወቅቱ በመንግሥታቱ ድርጅት የኤርትራ ተወካይ የነበሩት አምባሳደር አርአያ ደስታ ውሳኔውን "በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መንግሥታት የተቀነባበረ ውሸተኛ እና አሳፋሪ" ሲሉ ኮንነውት ነበር።
በሶማሊያ እና ኤርትራ ለዓመታት ምርመራ ከተካሄደ በኋላ አሥመራ ለአል-ሻባብ ታጣቂዎች ድጋፍ መስጠቷን የሚያሳይ እርግጠኛ መረጃ አልተገኘም። ተመድ የጣለው ማዕቀብ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ (በአውሮፓውያኑ 2018) ተነስቷል።













