አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ልታነሳ መሆኑ ተዘገበ

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ በቀይ ባሕር ዳርቻ ቁልፍ ቦታ ላይ በምትገኘው በኤርትራ ላይ የጣለቸቻውን ማዕቀቦች ልታነሳ መሆኗን የሚያመለክት የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰነድን መመልከቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ከአሥመራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እና ጎረቤት አገር ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት እንዳትገባ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው ሲሉ ተንታኞች መናገራቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

አሜሪካ ከኢራን ጋር በገባቸው ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ ከእስያ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ለሚደረገው የባሕር ላይ ንግድ በቀይ ባሕር ላይ የሚኖርን ቁጥጥር አስፈላጊነትን አጉልቶታል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በጠላትነት የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸው ተሻሽሎ ነበር።

የሁለቱ አገራት ወታደሮች ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በአንድ ጎራ ተሰልፈው ተዋግተዋል።

ጦርነቱ አሜሪካ ዋነኛ ተሳታፊ በነበረችበት የፕሪቶሪያ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረው ወዳጅነት ተቀዛቅዞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በይፋ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትን መናገር ከጀመሩ በኋላ ወደ ጠላትነት ተሸጋግሯል።

አሁን አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች የምታነሳ ከሆነ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ልትወስድ የምትችለውን የትኛውንም ዓይነት የኃይል እርምጃ እንደማትደግፈው መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ዲፕሎማታችን መናጋረቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል።

የዜና ወኪሉ የጠቀሰው የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰንድም "የባሕር በር በኃይል ለማግኘት የሚደረግን የትኛውንም ዓይነት ሙከራ እንደምንቃወም ለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አሳውቀናል" ይላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንዳቸው በሌላኛቸው ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው "አለመረጋጋትን በሚፈጥር ተሳትፎ" የተነሳ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአንድ ሳምንት በፊት ዎል ስትሪት ጆርናል የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እያሰበች መሆኑን የአገሪቱ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

ጨምሮም የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች የማንሳት ሂደት ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው እና አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ግምገማ እደያረገች መሆኑን ጋዜጣው አመልክቶ ነበር።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ከነበራት ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ከአምስት ዓመት በፊት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባለሥልናት ላይ ዕቀባ መጣላቸው ይታወሳል።

ሮይተርስ ተመለከትኩት ያለው የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰነድ በርካታ አገራት የሚመለከቱ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች እና ማዕቀቦች በቀናት ውስጥ እንደሚነሱ አመልክቷል።

ነገር ግን ኤርትራን ጨምሮ በሌሎች አገራት ላይ የተጣሉት ዕቀባዎች መነሳታቸው መቼ እንደሚገለጽ የተባለ ነገር የለም።

ሮይተርስ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ እና የገንዘብ ሚኒስቴሮች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለማግኘት ያቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

በተጨማሪም ሮይተርስ ከኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል እና ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም አስተያየታቸውን ጠይቆ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።

የአሜሪካውን ታዋቂ ጋዜጣ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባን ተከትሎ በኤርትራ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና በቀጣናው በሚካሄዱ ግጭቶች ውስጥ ባላት ሚና የተነሳ የተለያዩ ወገኖች አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ማሰቧን የሚቃወሙ ትችቶች ተሰንዝረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በዋሽንግተን የሚገኘው የኤርትራ ኢምባሲ፣ በአሜሪካ እና በኤርትራ መካከል ባለው ግንኙነት መሻሻል ላይ የሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶችን የሚተች መግለጫ አውጥቷል።