ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመቶዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ከቦኮ ሃራም እገታ ነፃ ወጡ
ባለፈው መጋቢት ከናይጀሪያ ሰሜን ምሥራቅ ግዛት ቦርኖ በአብዛኛው ሙስሊም ከሆነ ማኅበረሰብ በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ቦኮ ሃራም ታግተው ተወስደው የነበሩ 360 ሰዎች ተለቀቁ።
ታጋቾቹ የተለቀቁበት መንገድ ግን እያከራከረ ነው።
የአገሪቱ ጦር ለሳምንታት ዕቅድ ነድፎ በደኅንነት መረጃዎች የተመራ እና ታይቶ በማይታወቅ ተልዕኮ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ላይ ሳያስበው እርምጃ መውሰዱን ተናግሯል።
ይሁን እንጂ 'ቦርኖ ሳውዝ ዩዝ ኢንሸቲፍ' የተባለ የአካባቢው ቡድን ነፃ የወጡትን ሰዎች ቁጥር 416 በማድረስ በሽምግልና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስለቀቁን ገልጿል።
ባለፉት ዓመታት በናይጄሪያ ለገንዘብ ተብሎ በታጣቂዎች የሚደረግ እገታ መደበኛ እየሆነ መጥቷል። ምንም እንኳ በአገሪቱ ሕግ የማስለቀቂያ ገንዘብ መክፈል ሕገ ወጥ ቢሆንም።
ቦኮ ሀራም እ.አ.አ በ2014 ቺቡክ ከተባለ መንደር 200 የሚሆኑ ሴት ተማሪዎችን በማገት በሰፊው ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ 90 የሚሆኑት አሁንም ድረስ ያሉበት አይታወቅም።
ቡድኑ አልፎ አልፎ አግቶ የወሰዳቸውን ሴቶች ለወሲብ ባርነት፣ ለቤት ውስጥ የግዳጅ ሥራ እና ለአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ እንደሚጠቀምባቸው ይነገራል።
ነገር ግን በርካታ ቡድኖች በመላው ናይጀሪያ እገታን ገንዘብ ማግኛ መንገድ በማድረግ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች እና የገጠር መንደሮችን ዒላማ ያደርጋሉ።
ተንታኞች እንደሚሉት ቤተሰቦች፣ አሸማጋዮች አንዳንዴ ደግሞ ባለሥልጣናት የሚከፍሉት የማስለቀቂያ ገንዘብ እገታን እያባባሰው ነው።
የናይጀሪያ ጦር ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ሀሩና ኤም ሳኒ ቦኮ ሀራም በሚደበቅበት ማንዳራ ተራራ የተወሰደውን ጥቃት "በጨለማ ሽፋን የተደረገ" ያሉ ሲሆን፤ በሰሜን ምሥራቅ ጦሩ ያደረገው "ትልቁ ታጋቾችን የማስለቀቅ ተልዕኮ" ብለውታል።
"ፈጣን፣ ዒላማውን በትክክል የለየ እና ከፍተኛ ኃይል" የወረደባቸው ታጣቂዎች ይዞታቸውን ለቀው በተራራማው አካባቢ መሸሸቸውን እና ሌሎች ደግሞ እጅ መስጠታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ታጋቾቹ የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ልዩ አማካሪ ዳንኤል ባውላ በኤክስ ገፃቸው "በሚያሰዝን ሁኔታ ለረጅም ጊዜ በመያዛቸው እና በከባድ ሁኔታ ውስጥ በመዳከማቸው ሁለት ሕፃናት ሕይወታቸው አልፏል" ብለዋል።
በመላው ናይጀሪያ በሰፊ የደኅንነት ስጋት ከባድ ወቀሳ ውስጥ የገባው መንግሥት ወታደሮችን አመስግኗል።
ታጋቶቹ ከካሜሩን ድንበር አቅራቢያ ከሚገኘው ናጎሼ ከተባለ አካባቢ በአብዛኛው ሙስሊም ከሆነው ማኅበረሰብ የተወሰዱ ናቸው።
ባለው መጋቢት የአካባቢው ነዋሪዎች የረመዳንን ፆም እየፈቱ ባለበት ወቅት አካባቢው በቦኮ ሀራም ታጣቂዎች ጥቃት ተፈፅሞበታል።
የ'ቦርኖ ሳውዝ ዩዝ አሊያንስ' ፕሬዝዳንት ሳሚላ ሊጋማ ለጋዜጠኞች ቡድናቸው ታጋቾች እንዲለቀቁ ሲወተውት እንደነበር እና ከታጣቂው ጋር እየተነጋገረ እንደነበር ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ የጥረታችንን እውቅና ነጥቅውናል ያሏቸውን የመንሥትት ወታደሮችም ተችተዋል።
እሑድ ጠዋት ታጣቂ ቡድኑ የለቀቃቸውን ታጋቾች ምሥል አጋርቷል።
ቦኮ ሀራም በሰሜናዊ ናይጀሪያ እስላማዊ ሕግጋትን ለመትከል ወታደራዊ ዘመቻውን የጀመረው እ.አ.አ በ2009 ነው። ከዚህ ቀደም ይዞት የነበረውን ግዝፍ ግዛት አሁን የማይቆጣጠር ቢሆንም፤ ሌሎች ተሰንጣቂ ቡድኖች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን አደገኛ እንደሆኑም ይነገራል።
በዚህ ዓመት አጋማሽ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ ወታዶች የናይጀሪያን ወታደሮች ለማሰልጠን እና የደኅንነት ስጋቱን ለመዋጋት ለድጋፍ ዘምተዋል።